ሴቶች በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው ሴቶች በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሥራ አጥ ቁጥርን የሚቀንስ ኤኮኖሚያዊ ተሃድሶ ሊደረግ ይገባል አሉ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐሙስ ሰኔ 10/2013 ዓ. ም በአውታረ መረብ አማካይነት በጀኔቭ ለተካሄደው 109ኛ ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ጉባኤ የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልዕክታቸው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመውጣት የሚደረገው ጥረት እንዲቀጥል አሳስበዋል። ከወረርሽኙ በኋላ የሚከሰተውን ገደብ-አልባ የፍጆታ ዕቃዎች አጠቃቀምን በማስቀረት፣ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ የሚያስችል ኤኮኖሚያዊ ተሃድሶ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰራተኛ ማኅበራት መደራጀት የሰዎች መብት መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረው፣ ሰራተኞች መብታቸውን በማስከበር ለጠቅላላ የጋራ ጥቅም መቆም እንደሚያስፈልግ እና የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ የሚያስችል ኤኮኖሚያዊ ተሃድሶ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። የሥራ ዕድል መመቻቸት ውሳኝ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስረድተው፣ ለቀን ሠራተኞች፣ ለስደተኞች እና ከሁሉም በላይ ለሴቶች የሥራ ዕድል መከፈቱ አስፈላጊ መሆኑን በጀኔቭ ለ109ኛ ጊዜ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ጉባኤ በላኩት የቪዲዮ መልዕታቸው አስታውቀዋል።

ከሥራ የተገለሉትን ማገዝ ያስፈልጋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ሥራ ያቋረጡ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ ለእነዚህ ሰዎች ማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ስደተኞች እና ከሥራ የተገለሉ ቤተሰቦች ብሔራዊ የጤና አገልግሎትን እና ማኅበራዊ ድጋፍን እንዳያገኙ የተደረጉ መሆናቸውን በመልዕክታቸው አስረድተዋል። በችግር እና በድህነት ምክንያት ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ የተደረጉ ስደተኞች እና  ጥገኝነት ጠያቂዎች  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምርመራ ማድረግ አለመቻላቸው ቫይረሱ በሕዝቦች መካከል የበለጠ እንዲሰራጭ አጋጣሚን ይጨምራል ብለዋል።

ሥራ አጥነት፣ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያስከተላቸውን ቀውሶች የዘረዘሩት ቅዱስነታቸው፣ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል ትክክለኛ እርምጃን ካለመውሰድ የተነሳ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መጨመር፣ በቂ የዕለት ምግብ አለመገኘት፣ በሕመም ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆኑት እና አረጋዊያን በተላላፊ በሽታ በቀላሉ መጠቃት የሚሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።         

የመልካም ሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲቆም እና ወደ መደበኛ የሥራ ገበታ ሲመለስ ሊከሰት የሚችለውን የትርፍ መሰብሰብ እና ብሔራዊ ጥቅምን ብቻ በመመልከት የሚደረግ ራስ ወዳድነትን መከላከል እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበው፣ ከወረርሽኙ በኋላ የሚከሰተውን ገደብ-አልባ የፍጆታ ዕቃዎች አጠቃቀምን ማስቀረት፣ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚያስችል ኤኮኖሚያዊ ተሃድሶ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በወጣቶች፣ በምርት ተቋማት እና በሠራተኞች መካከል ውይይት ሊኖር ይገባል።

በማኅበረሰብ መካከል ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው የተለያዩ ክፍሎች መኖራቸውን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከእነዚህም መካከል ወጣቶች፣ ስደተኞች እና ድሃ ማኅበረሰብ በጋራ በሚያደርጉት ውይይት ተዘንግተው መቅረት እንደሌለባቸው አሳስበው ውይይቱ መንግሥታትን እና የማምረቻ ተቋማትን የሚያሳትፍ መሆን ይገባል ብለዋል። ቤተክህነትን ጨምሮ ሁሉን የማኅበረሰብ ክፍል በማሳተፍ ዘላቂነት ባለው የጋራ ውይይት ወደ ፊት ጠንካራ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መገንባት ይቻላል ብለው፣ ሁሉን የማኅበረሰብ ክፍል የሚያሳትፍ የጋራ ውይይት መብትን እና ግዴታን መሰረት ያደረገ መሆን ይገባል ብለዋል።

19 June 2021, 16:43