ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ ወር ‘መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች’ ይከበሩ ዘንድ እንጸልይ አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ መልእክት ይፋ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ቅዱስነታቸው ለሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም እንዲሆን ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ በሁሉም የዓለም ክፍሎች የሰዎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ ለሚታገሉ ሁሉ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ እንዲጸልዩ ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ ድፍረት እና ቆራጥነት ይጠይቃል” በማለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገለጹ ሲሆን ይህን አስተያየት ከግምት ባስገባ መልኩ በሚያዝያ ወር ጸሎት እንዲደረግ ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አክለው እንደ ገለጹት ይህ ማለት ደግሞ “ድህነትን ፣ ያልተመጣጠነ እድገትን፣ የሥራ እጦትን ፣ የመሬትና የመኖሪያ ቤቶችን እጥረት፣ እንዲሁም ማህበራዊና የሠራተኛ መብቶችን ማስከበር” በተሰኙት ላይ በብቃት በመሥራት ላይ ያተኮረ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታር መሥሪያ ቤት የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት “ለመሰረታዊ መብቶች ሲታገሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ ለሚያጋልጡ” እንዲጸልዩ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሁሉ ጸሎት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል።

የገዛ ሕይወትን ለአደጋ በማጋለጥ ሌሎችን ከአደጋ መከላከል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት የሰብዓዊ መብቶች ብዙውን ጊዜ ለሁሉም በእኩልነት እየተዳረሱ አይደሉም በማለት የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም “የመጀመሪያ ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ የተሰጣቸው ሰዎች አሉ፣ እንዲሁም ከእዚህ በከፋ መልኩ የተገለሉ ሰዎች አሉ” በማለት ስለሁኔታው አሳሳቢነት አክለው ገለጸዋል።

ሆኖም መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች “ለሁሉም እኩል መሆን አለባቸው” በማለት በመልእክታቸው አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው “በአንዳንድ ስፍራዎች የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር ማስከበር ያለምንም ፍርድ ወደ ወህኒ ቤት መሄድ ማለት ሊሆን ይችላል። ወይም ስም ማጥፋት ማለት ሊሆን ይችላል” በማለት ስለሁኔታው አሳሳቢነት አክለው ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ምንም እንኳን አደጋ ቢኖረውም “እያንዳንዱ ሰው በተሟላ ሁኔታ የማደግ መብት አለው ፣ ይህ መሠረታዊ መብት በማንኛውም ሀገር ሊከለከል አይገባውም” በማለት አጽኖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዚህ ዓላማ ሁሉም ሰው በሚያዝያ ወር እንዲጸልዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በአምባገነኖች ፣ በአምባገነናዊ አገዛዞች እና በችግር ውስጥ ባሉ ዴሞክራሲዎች ውስጥ እንኳን ለመሰረታዊ መብቶች ሲታገሉ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ለጣሉ ሰዎች እንጸልይ ፣ መስዋእትነት ቢያስከፍልም ስራቸው የተትረፈረፈ ፍሬ ያፈራል የሚል ተስፋ እና እምነት አለኝ በማለት ቅዱስነታቸው በሚያዝያ ወር የጸሎት ሐሳብ ዙሪያ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ በጸሎት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

08 April 2021, 10:57