ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ክርስትና ከሌሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር እና ደስተኛ መሆን ማለት ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በእለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሚያዝያ 10/2013 ዓ.ም ያደረጉት አስተንትኖ ከሉቃስ ወንጌል 24፡35-48 ላይ በተጠቀሰው ወደ ኢማሆስ በመሄድ ላይ የነበሩ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ለሌሎች ደቀ መዛሙርት እየተረኩላቸው በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ መገለጹን በሚያመለክተው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ እንደ ነበረ እየተገለጸ ሲሆን ክርስትና ማለት ከሌሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ እንክብካቤ ማደረግ እና ደስተኛ መሆን ማለት ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ በሦስተኛው የፋሲካ ሳምንት እሑድ (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ከፋሲካ በዓል በኋላ ያለውን እለተ ሰንበት ማለታቸው ነው) በሁለቱ የኤማሁስ ደቀ መዛሙርት ተመርተን በመንገድ ላይ የኢየሱስን ቃላት በከፍተኛ ስሜት አዳምጠው ከዚያ በኋላ “እንጀራውን በቆረሰ ጊዜ” እርሱን ያወቁት ሁለት የኤማሁስ ደቀ መዛሙርት ተመርተን ወደ ኢየሩሳሌም እንመለሳለን (ሉቃ 24 35)። አሁን በማዕከሉ ውስጥ ፣ የተነሳው ክርስቶስ በደቀ መዛሙርት ቡድን መካከል እራሱን አቅርቦ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” (ሉቃስ 24፡36) በማለት ሰላምታ ያቀርብላቸዋል። ነገር ግን እነሱ ይፈራሉ፣ እናም እነርሱ “መንፈስን ያዩ መስሎዋቸው ይደነግጣሉ” (ሉቃስ 24፡ 37) ቅዱስ ወንጌል እንደሚለው። ከዚያም ኢየሱስ በሰውነቱ ውስጥ ያሉትን ቁስሎች አሳያቸውና “እጆቼንና እግሮቼን እዩ” አላቸው - ቁስሎቹን አሳያቸው “እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና” (ሉቃስ 24፡39) ይላቸዋል። እነርሱም ከመገረማቸው እና ከመደነቃቸው የተነሳ አላመኑም ነበር፣ ነገር ኝ እርሱ “አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁ ወይ?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራሽ ሰጡት፤ እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። (ሉቃስ 24፡ 41-42)።

በዚህ አገላለጽ ውስጥ በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር አለ። የቅዱስ ወንጌል ቃል ሐዋርያት “አሁንም በደስታ ተውጠው ስለነበር  አላመኑም” ነበር ይላል። በነበራቸው ደስታ የተነሳ ይህ እውነት የሆነ ነገር ነው ብለው ማመን አቅቷቸው ነበር።  ሁለተኛው መገለጫ ደግሞ ግራ ተጋብተው እና ተደንቀው ነበር የሚለው ነው፤ ተገርመዋል ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ሁል ጊዜ ወደ አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ሊመራን ይችላል፣ ከመጓጓት ባሻገር ያለ ነገር ነው፣ ከደስታም ባሻገር የሚሄድ ገጠመኝ ነው፣ ሌላ አዲስ ተሞክሮ ነው። እናም እነሱ ደስተኞች ነበሩ ፣ ነገር ግን እንድያስቡ የሚያደርጋቸው ደስታ ነበር-የለም በፍጹም ይህ እውነት ሊሆን አይችልም! ... በማለት ይገረማሉ። የእግዚአብሔር መገኘት አስደንጋጭ ነው። በጣም ቆንጆ የሆነውን ይህን የአዕምሮ ማዕቀፍ አይርሱ።

በእዚህ ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ሶስት  ተጨባጭ የሆኑ ግሦች አሉ። በተወሰነ መልኩ እነሱ የእኛን ግለሰባዊ እና ማህበረሰብ ኑሮ የሚያንፀባርቁ ናቸው-መመልከት ፣ መንካት እና መብላት የተሰኙ ግሶች ናቸው። ከሕያው ኢየሱስ ጋር በእውነተኛ ገጠመኝ ደስታን የሚሰጡ ሦስት ድርጊቶች ናቸው።

ማየት። ኢየሱስ “እጆቼንና እግሮቼን እዩ” አለ ኢየሱስ። መመልከት ማለት ማየት ብቻ አይደለም ፣ ከእዚያ የበለጠ ነው፣ እንዲሁም ዓላማን ፣ ፈቃድን ያካትታል። በዚህ ምክንያት እሱ ከፍቅር ግሦች አንዱ ነው። እናት እና አባት ልጃቸውን ይመለከታሉ፣ አፍቃሪዎች እርስ በእርሳቸው ይተያያሉ፣ አንድ ጥሩ ሐኪም በሽተኛውን በጥንቃቄ ይመለከታል…. መመልከት ግድየለሽነትን ለመቃወም ፣ የሌሎችን ችግሮች እና መከራዎች ፊት ለፊት ለመመልከት ከሚደረገው ፈተና ጋር አብሮ የሚሄድ ነገር ነው። ማየት። ኢየሱስን አያለሁ ወይስ እመለከታለሁ?

ሁለተኛው ግስ መንካት የሚለው ነው። ደቀ መዛሙርቱን እንዲነኩ በመጋበዝ እርሱ መንፈስ አለመሆኑን ለይተው እንዲያጣሩ ንኩኝ ይላቸዋል። - ኢየሱስ ከእርሱ እና ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለው ግንኙነት “በርቀት” መሆን እንደ ሌለበት ለእነሱ እና ለእኛ አመልክቷል። ክርስትና በርቀት የሚኖር ነገር አይደለም። ክርስትና በመልክ ደረጃ ብቻ አይኖርም። ፍቅር መመልከትን ይጠይቃል፣ መመልከት ደግሞ እንዲሁም መቀራረብን ይጠይቃል፣ ግንኙነትን ፣ ሕይወትን መጋራት ይፈልጋል። ደጉ ሳምራዊ በመንገዱ ላይ ሊሞት ተቃርቦ የነበረውን ያንን ሰው በመመልከት ብቻ አልተገደበም፣ ቆመ ፣ ጎንበስ ብሎ ቁስሉን አከመ፣ ዳሰሰው ፣ እርሱ ይዝበት በነበረው አህያ ጭኖ ወደ ማረፊያ ቤቱ ወሰደው። እናም ይህ ተግባር ከእራሱ ከኢየሱስ ጋር ተመሳሳይ ነው፣ እርሱን መውደድ ማለት ወደ ሕይወት ህብረት መግባት ፣ ከእርሱ ጋር ህብረት ማድረግ ማለት ነው።

እናም መብላት ወደ ተሰኘው ሦስተኛው ግስ አሁን መጥተናል፣ እሱም በጣም በተፈጥሮአዊ ድህነቱ ውስጥ ሰብአዊነታችንን በግልጽ የሚገልጽ ማለትም ፣ ለመኖር እራሳችንን የመመገብ ፍላጎታችን የሚያሳይ ነው። ነገር ግን መብላት ፣ በቤተሰብ ወይም በጓደኞች መካከል አብረን ስንሠራ እንዲሁ የፍቅር መግለጫ ፣ የኅብረት መግለጫ ፣ የበዓላት መግለጫ ይሆናል… ወንጌላውያን ኢየሱስ ይህንን የመሳሰሉ የአብሮነት መገለጫ የሆኑ ነገሮችን ለእኛ ብዙ ጊዜ አቅርበዋል። ከሙታን የተነሳው ጌታ በደቀ መዛሙርቱ ፊት ተቀብሎ እንደ በላ ያሳዩናል። የቅዱስ ቁርባን ግብዣው የክርስቲያን ማኅበረሰብ አርማ ምልክት እንደ ሆነ ያሳዩናል። የክርስቶስን አካል አንድ ላይ መብላት-ይህ የክርስቲያን ሕይወት ዋና ምልክት ነው።

ወንድሞች እና እህቶች ፣ ይህ የወንጌል ክፍል ኢየሱስ “መንፈስ” እንዳልሆነ ይነግረናል ፣ ነገር ግን ህያው አካል እንደ ሆነ ያሳየናል፣ ኢየሱስ ወደ እኛ በሚቀርብበት ጊዜ ማመን እስክያዳግተን ድረስ በደስታ እንደሚሞላን እና የእግዚአብሔር ህላዌ ብቻ በሚሰጠን በዚያ መደነቅ ግራ ተጋብተን እንደ ማይትወን ያሳየናል፣  ምክንያቱም ኢየሱስ ህያው አካል ነው።

ክርስቲያን መሆን በመጀመሪያ ደረጃ ዶክትሪን ወይም ሥነ ምግባራዊ ነገሮችን ማክበር ብቻ ማለት አይደለም። ከርሱ ከተነሳው ጌታ ጋር ህያው ግንኙነት መፍጠር ማለት ነው። እርሱን እንመለከተዋለን ፣ እንነካዋለን ፣ በእርሱ ተመግበናል እናም በፍቅሩ ተለውጠናል ፣ ሌሎችን እንደ ወንድም እና እህቶች እንመለከታቸዋለን ፣ እንነካቸዋለን እንዲሁም ከእነርሱ ጋር አብረን እንመግባለን። ይህንን የመሰለ የጸጋ ተሞክሮ እንድንኖር ድንግል ማርያም ሁላችንንም በአማላጅነቷ ትርዳን።

 

18 April 2021, 12:56