የሆሳህና በዓል በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተከበረበት ወቅት የሆሳህና በዓል በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተከበረበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኢየሱስ ሕይወት መገረም እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እግዚሐብሔር እንለምነው አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 19/2013 ዓ.ም ኢየሱስ መከራውን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም በታላቅ ክብር የገባበት የሆሳህና በዓል ተክብሮ ማለፉ ይታወቃል፣ በእለቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት በኢየሱስ ሕይወት መደነቅ ብቻ ሳይሆን መገረም እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራና እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

በየአመቱ የሚካሄደው ይህ የስርዓተ አምልኮ ሥነ-ስርዓት ያስደንቀናል-ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በደስታ ከመቀበል አንስቶ ሞት የተፈረደበትንና ከዚያ በኋላ የተሰቀለውን ኢየሱስ መመልከት ሐዘን ውስጥ ይከተናል። ያ ውስጣዊ የመደነቅ ስሜት በሕማማት ሳምንት ውስጥ በሙሉ ከእኛ ጋር ይቆያል። በእሱ ላይ በይበልጥ በጥልቀት እናሰላስል።

ከመጀመሪያው አንስቶ ኢየሱስ እኛን አግራሞት ውስጥ ከቶናል። የእሱ ሰዎች ታላቅ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ሆኖም ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ተራ በሆነ መንገድ ነበር። የእርሱ የራሱ ሰዎች በፋሲካ በዓል ላይ አንድ ኃይለኛ የሆነ ነፃ አውጪ ሰው እንደ ሚመጣ እየተጠባበቁ ነበር፣ ሆኖም እሱ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ፋሲካውን ወደ ፍጻሜ ለማምጣት ይመጣል። የእሱ ሰዎች ሮማውያንን በሰይፍ ለማሸነፍ ተስፋ ያደርጋሉ ፣ ነገር ግን ኢየሱስ የመጣው በመስቀል በኩል የእግዚአብሔርን ድል ለማክበር ነው። በጥቂት ቀናት ልዩነት ጊዜ ውስጥ “ሆሳዕና” ከሚለው ጩኸት ወደ “ስቀለው” ወደ ሚለው ጩኸት የሄዱ ሰዎች ምን ሆኑ? እነሱ ከመሲሑ ይልቅ ስለ መሲሑ በመነዛት ላይ ያለውን ሀሳብ እየተከተሉ ነበር። ኢየሱስን ያደንቁ ነበር ነገር ግን በእርሱ እንዲገረሙ አልፈቀዱም። መደነቅ ከመገረም ጋር አንድ አይደለም። አድናቆት የራሱ ጣዕም እና የሚጠብቀውን ነገር ስለሚከተል ዓለማዊ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል መገረም ለሌሎች እና ለሚያመጣው አዲስነት ራሱን ክፍት አድርጎ ይቆያል። ዛሬም ቢሆን ኢየሱስን የሚያደንቁ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ውብ ነገሮችን ተናግሯል፣ እርሱ በፍቅር እና በይቅርታ የተሞላ ነው፣ የእሱ ምሳሌ ታሪክን የቀየረ ነው… ወዘተ እያሉ እሱን ያደንቁታል፣ ህይወታቸው ግን አልተለወጠም። ኢየሱስን ማድነቅ ብቻ በቂ አይደለም። እኛ የእርሱን ፈለግ መከተል አለብን ፣ ከአድናቆት ወደ መገረም እንድንሻገር እርሱ እንዲገዳደረን መፍቀድ አለብን።

ስለ ጌታ እና ስለ ፋሲካው በጣም የሚያስደንቀው ነገር ምንድን ነው? በውርደት ክብርን ማግኘቱ እውነታ ነው። እርሱ በአድናቆት እና በስኬት ጥረታችን የምንመርጠው ነገር መከራን እና ሞትን በመቀበል ድል ያደርጋል። ኢየሱስ - ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን - “ራሱን ባዶ አደረገ… ራሱን አዋረደ” (ፊል 2 7.8)። ሁሉን ቻይ የሆነው እርሱ ወደ ባዶነት መቀየሩ ማየት በራሱ ይህ አስገራሚ  ነገር ነው። ሁሉን የሚያውቅ ቃል የነበረ እርሱን አሻግሮ ከፍ ካለው መስቀል ላይ እርሱን መመልከት በራሱ በፀጥታ ያስተምረናል። የነገሥታት ንጉስ የሆነውን እርሱን ከተሰቀለበት ከፍታ ላይ ሆኖ እርሱን መመልከት ያስፈልጋል። የአጽናፈ ዓለሙ አምላክ የሆነው እርሱ  ሁሉንም ነገር ሲገፈፍ እና በክብር ፋንታ የእሾህ አክሊል ሲደፋበት መመልከት በራሱ የሚያስተምረን ነገር አለ።     በጎነት የተመሰለውን ፣ የተሰደበውን ፣ የተገረፈውን ማየት የሚያስተምረን ነገር አለ። ይህ ሁሉ ውርደት ለምን? ጌታ ሆይ ለምን ይህን ሁሉ መቀበል ፈለክ?

ኢየሱስ ለእኛ ብሎ ይህንን ያደረገው የሰው ልጆች ልምዶች ጥልቀት ፣ አጠቃላይ ህልውናችንን ፣ ክፋታችንን ሁሉ ለመግራት ነው። እኛን ለማግለል ሳይሆን፣ ነገር ግን ወደ እኛ ለመቅረብ በሞታችን እና በመከራችን እኛን አልተወንም። እርሱ የእኛን ጥልቅ ሐዘን ተጋርቷል፣ ኢየሱስ ወደ እኛ መከራ አዘቅት ለመውረድ በመስቀል ላይ ከፍ ብሎ ተሰቅሏል፣  በጣም ጥልቅ የሆኑ ሐዘኖቻችንን ተመልክቷል - ውድቀት ፣ ሁሉንም ነገር ማጣት ፣ በጓደኛ መካድን፣ በእግዚአብሔርም ሳይቀር መተውን ጨምሮ ሁሉን ነገር ተመልክቷል። ጥልቅ ተጋድሎዎቻችንን እና ግጭቶቻችንን በሥጋ ተጨባጭ በሆነ መንገድ በመለማመድ ፣ ቤዛ አድርጎ ቀይሯቸዋል።  በፍቅሩ ወደ ደካማነታችን ይቀርባል ፤ በጣም የምናፍርባቸውን ነገሮች እንኳን ሳይቀር በፍቅሩ ይነካቸዋል። እኛ ግን ብቻችንን እንዳልሆንን አሁን እናውቃለን፣ እግዚአብሔር በመከራ ሁሉ ፣ በፍርሃት ሁሉ ከእኛ ጋር ነው ፣ ክፋት እና ምንም ዓይነት ኃጢአት በራሱ የመጨረሻ ቃል አይኖረውም። እግዚአብሔር ያሸንፋል ፣ ነገር ግን የሆሳህና ድል በመስቀሉ እንጨት በኩል ያልፋል። ሆሳህና እና መስቀሉ የማይነጣጠሉ ናቸውና።

በእዚህ በከፍተኛ ሁኔታ መገረም እንችል ዘንድ ጸጋውን እንጠይቅ። ያለ መገረም ክርስቲያናዊ ሕይወት ደረቅ  እና አስፈሪ ይሆናል። ይቅርታን እና አዲስ ጅምርን በሚያመጣልን ፍቅሩ በየቀኑ ካልተደነቅን እና ካልተገረምን በስተቀር ስለ በኢየሱስ ስለሚገኘው ደስታ እንዴት ማውራት እንችላለን? እምነት ከአሁን በኋላ በመገረም ካልታጀበ በስተቀር አሰልቺ ይሆናል፣ ጸጋውን እንዳንመለከት ዕውር ያደርገናል፣ የሕይወትን እንጀራ ጣዕም መለየት እና ቃሉን በሚገባ መስማት ያዳግተናል፣ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ውበት እና የፍጥረትን ስጦታ ከእንግዲህ ማስተዋል ያዳግተናል ማለት ነው።

በእዚህ ቅዱስ በሆነው በሕማማት ሳምንት ወቅት የመገረምን ጸጋ ለመቀበል ዓይኖቻችንን ወደ መስቀሉ እናንሳ። የዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ በተሰቀለው ጌታ ላይ ሲያሰላስል የእርሱ ወንድሞች መስቀሉን አይተው ለምን እንዳላለቀሱ ተመልክቶ ተገረመ። እኛስ? አሁንም በእግዚአብሔር ፍቅር መንቀሳቀስ እንችላለን? በእርሱ የመደነቅ ችሎታ አጥተናል ወይ? ምናልባት እምነታችን ከልምድ አኳያ ሲታይ አሰልቺ ሊሆን ይችላል። ምናልባት በጸጸታችን ውስጥ ገብተን ተይዘን በመቆየታችን እንድንከሽፍ አድርጎን ሊሆን ይችላል። ምናልባት ሁሉንም መተማመናችንን አጥተናል ወይም ዋጋ እንደሌለን ሆኖ ይሰማናል። ነገር ግን ምናልባት ከእነዚህ ሁሉ “ምን አልባቶች” በስተጀርባ የመገረም ጸጋን ለሚሰጠን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ክፍት አለመሆናችን ያመጣው ውጤት ይሆናል።

ከመገረማችን እንጀምር። በመስቀል ላይ ያለውን ኢየሱስን ተመልክተንና “ጌታ ሆይ ፣ ምን ያህል ትወደኛለህ! እኔ ለአንተ ምን ያህል ውድ ነኝ! ” ብለን እንጠይቅ። የሕይወት ታላቅነት በንብረቶች እና ማስተዋወቂያዎች ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን እኛ እንደምንወደድ በመገንዘብ እና ሌሎችን የመውደድ ውበት በመለማመድ ላይ ስለሆነ ዳግመኛ መኖር እንድንጀምር በኢየሱስ እንገረም፣ እንደነቅ። በተሰቀለው ኢየሱስ ውስጥ ፣ እግዚአብሔር ተዋረደ ፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሲባረር እና ሲጣል እናያለን። እናም በአግራሞት ጸጋ የተባረሩትን እና የተወገዱትን በመቀበል ፣ በሕይወት ከተጎዱ ሰዎች ጋር በመቀራረብ ኢየሱስን እንደምንወደው እንገነዘባለን። እሱ የሆነውን የሆነው በእዚህ ምክንያት ስለሆነ ነው፤ አቅመ ደካማ እና የተረሱ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በመንከባከብ እርሱን ሕያው ለማደረግ እንችላለን።

የዛሬ ቅዱስ ወንጌል እንደሚያሳየን ከኢየሱስ ሞት በኋላ ወዲያውኑ ፣ የመገረም ስሜትን እንመለከታለን። ኢየሱስ መሞቱን ባየ ጊዜ “በእውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” ያለውን የመቶ አለቃው መመልከት ተገቢ ነው (ማርቆስ 15፡39)። ኢየሱስ ሲሞት እንዴት ነበር የተመለከተው? በፍቅር ሲሞት ነበር የተመለከተው። ኢየሱስ ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶበታል ፣ ነገር ግን መውደዱን አላቆመም። ሞትን እንኳን በፍቅር ሊሞላ በሚችለው በእግዚአብሔር ፊት መገረም ማለት ይህ ነው። በዚያ ውዝግብ እና ታይቶ በማይታወቅ ፍቅር አረማዊው መቶ አለቃ እግዚአብሔርን መገናኘት ችሎ ነበር።  በእውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነበር! የሚሉት ቃላት የሕማማቱን ታሪካ ትረካ ላይ የመደምደሚያ “ማኅተም” አድርጓል። ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን ከርሱ በፊት የነበሩ ሌሎች ብዙዎች ኢየሱስን በተአምራቱ እና ድንቅ ሥራዎቹ አድናቆት አሳይተው ነበር እንጂ በእውነት  የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ብዙም ግድ አልሰጣቸው ነበር።  ነገር ግን አሁን ክርስቶስ በእዚህ ረገድ ዝም እንዲሉ በማደረግ ከመደነቅ ወደ መገረም እንዲሻገሩ ፈልጎ ስለነበረ በነበሩበት የማድነቅ ሐስብ ብቻ ተጠፍረው በዓለማዊ ሐሳብ እና አድናቆት ደረጃ ላይ ብቻ በመቆየት አደጋ እንዳለው ለመግለጽ አስቦ የተጠቀመው ነው።  አሁን እንደዚያ ሊሆን አይችልም፣ በመስቀሉ ስር ምንም ስህተት ሊኖር አይችልምና: - እግዚአብሄር እራሱን ገልጧል የሚነግሰውም በተፈታ እና ትጥቅ በሚፈታ ኃይል ብቻ ነው።

ዛሬም እግዚአብሔር አእምሮአችንን እና ልባችንን በአግራሞት መሙላቱን ቀጥሏል። የተሰቀለውን ጌታ ስናይ በዚያ መደነቅ እንሞላ። እኛም እንናገር: - “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ። አንተ አምላኬ ነህ ” እንበለው።

28 March 2021, 21:07