ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ አመጽ እና ጥላቻ የክርስትና እምነት ተቃራኒ መሆናቸውን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የአገሪቱ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ጋር በባግዳድ በሚገኘው የምሕረት እናት ቅድስት እመቤታችን ካቴድራል ውስጥ መገናኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ወቅት ለሁሉም አዲስ ተስፋ እንዲገኝ በወንድማማችነት አብሮ ለመኖር የሚያግዝ እርቅን መዝራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ከቤተክህነት ጋር የተገናኙበት በባግዳድ ከተማ የሚገኝ የምሕረት እናት እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል፣ እ.አ.አ በ2010 ዓ. ም. ሴቶችን እና ሕጻናትን ጨምሮ በቁጥር 48 ምዕመናን በአሸባሪዎች እጅ የተገደሉበት ቦታ መሆኑ ታውቋል። ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአሥር ዓመታት በኋላ፣ ቅዱስነታቸው በኢራቅ የመጀመሪያ የሆነውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ማድረጋቸው ታውቋል።

ተስፋ የመቁረጥ አደጋ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቴድራሉ ለተገኘው የቤተክህነት አባላት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ በዕለት ተዕለት ተግዳሮቶች ውስጥ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ቢሆን ሐዋርያዊ ቅንዓታቸውን በጭራሽ ማቋረጥ እንደማይገባ፣ ተስፋን የመቁረጥ አደጋ በቀላሉ ሊያጠቃ የሚችል ቢሆንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የምናሸንፍበት የዕለታዊ ጸሎት እና የሐዋርያዊ ሕይወት ታማኝነት መንገድ አሳይቶናል ብለዋል። በዚህ መንገድ በመመራት እንደ ደቀ መዛሙርት የወንጌልን ደስታ ከሌሎች ጋር በመጋራት የእግዚአብሔርን አለኝታ የምንመሰክርበት የቅድስና፣ የፍትህ እና የሰላም ምልክቶችን በተግባር መኖር እንችላለን ብለዋል።

በችግር መካከል መጽናት

ቅዱስነታቸው በማከልም ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ የኢራቅ ምዕመናንን በርካታ ችግሮች ያጋጠሟቸው መሆኑንም አስታውሰው፣ ጦርነት እና ስደት በአገሪቱ መሠረተ ልማቶች፣ ዘላቂ የኤኮኖሚ ጥረት እና ደህንነት ላይ አደጋን በመፍጠር ክርስቲያኖችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንዲሰደዱ ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል። የኢራቅ ካቶሊካዊ ማኅበረሰ በቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም ከሕዝባቸው ጎን በመሆን ሲያበረታቱ እና ሲያጽናኑ የቆዩ ብጹዓን ጳጳሳትን እና ካህናትን አመስገነው፣ በቁጥር ዝቅተኛ የሆነው የኢራቅ ካቶሊካዊ ምዕመናን የማኅበረሰባችውን ሕይወት ለመለወጥ ዛሬም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ወንድማዊ አንድነት

የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እያንዳንዱን የራስ ወዳድነት ስሜት ወይም ውድድርን ወደ ጎን እንድንል ይጠራናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለጋራ አንድነት በማነሳሳት የወንድማማችነት እና እህትማማችነት ሕብረትን በማሳደግ አንዱ ለሌላው እንድንጨነቅ ያደርገናል ብለዋል። ልዩነት በሚታይበት ዓለማችን ስለ ወንድማዊ አንድነት መመስከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቤተ ክህነት፣ በቁምስናዎች፣ በሀገረ ስብከቶች እና በመንፈሳዊ ተቋማት መካከል ድልድይን በመገንባት፣ በኢራቅ ቤተ ክርስቲያን መካከል አንድነትን በማምጣት ለኢየሱስ ክርስቶስ የአንድነት ጸሎት ፍሬያማ ውጤቶችን ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንቅፋቶችን ማስወገድ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቤተ ክህነቱ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ አንዱ ሌላውን በትክክል ካለመረዳት የተነሳ ውጥረቶች ሊፈጠር እንደሚችል ገልጸው፣ ይህም የወንድማማችነት ስሜት እንዳይታይ እንቅፋት እንደሚሆን አስረድተዋል። እነዚህ እንቅፋቶችን በልባችን ይዘናቸው እንጓዛለን ብለው፣ ይህን በማድረጋችን ኃጤተኞች ነን ብለዋል። እነዚህ እንቅፋቶች በእግዚአብሔር ጸጋ ሊወገዱ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ በፍቅር፣ በምሕረት፣ በወንድማዊ ውይይት፣ አንዱ የሌላውን ሸክም በመሸከም እና በፈተና እና በችግር ጊዜ አንዱ ሌላውን በማበረታታት ሊወገዱ እንደሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እውነተኛ አባቶች መሆን

ቅዱስነታቸው ወንድም ለሆኑት ብጹዓን ጳጳሳት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ብጹዓን ጳጳሳቱ ከካህናት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው አሳስበው፣ ጳጳሳት ለካህናት ሕይወት የሚጨነቁ፣ ልባቸውን በመክፈት እንደ እውነተኛ አባት የሚያበረታቱ መሆን ይገባል እንጂ እንደ አለቃ መታየት የለባቸውም ብለዋል።

መንጋዎን ይንከባከቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለካህናት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ካህነት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን እና የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ለምዕመናን ትኩረትን በመስጠት የተረሱትን በተለይም ለወጣቶች፣ ለአረጋዊያን፣ ለሕሙማን እና ድሆች እንክብካቤን ሊያደርጉላቸው እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ምዕመናንን በእግዚአብሔር ቃል የሚመግቡ እና የሚያገለግሉ እንጂ አዛዥ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

የጥቃት ሰለባዎች

ከአሥር ዓመታት በፊት በምሕረት እናት እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ በአሸባሪዎች በኩል በተከፈተው ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ወንድሞችን እና እህቶችን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለቅድስና የሚያበቃቸው የቤተክርስቲያን ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ሞታቸው ከጦርነት፣ ከአመጽ እና ደም ከማፍሰስ የበለጠ ኃይል እንዳለው እና ከእውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር የሚገናኝ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ መልዕክታቸው የሐይማኖት ልዩነት ሳይመለከቱ በሽብር ጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን እና ለስደት የተጋልጡትን በሙሉ አስታውሰዋል።

ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምሕረት እናት እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ የተገኙት በሙሉ በምዕመናን መካከል፣ በኢራቅ ማኅበረሰብ ዘንድ እና የተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ሰላምን ለማውረድ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፣ የዕርቅ እና በወንድማማችነት መንፈስ አብሮ መኖርን የሚያስችል ዘርን መዝራት በሁሉም ሰው ዘንድ አዲስ ተስፋ ዳግመኛ እንዲወለድ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የተስፋ ምልክት የሚታይባቸው የኢራቅ ወጣት ማኅበረሰብን አስታውሰዋል።

የእግዚአብሔር ተስፋ ምስክሮች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ያስተላለፉትን መልዕክት በደመደሙበት ወቅት እንደገለጹት፣ ቤተ ክህነቱ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ምስክሮች አካል መሆናቸውን ገልጸው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት ሊመሠርት የገባውን የአዲስ ሕይወት ቃል ኪዳን የሚፈጽም መሆኑን ከተናገሩ በኋላ፣ ምስክርነታቸው ቅራኔዎች ቢያጋጥሙትም በሰማዕታቱ ደም በመታገዝ አድጎ እና ጠንክሮ፣ በኢራቅ ሕዝብ መካከል የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለመመስከር የሚያግዝ ብርሃን እንዲበራ እና በእግዚአብሔር ደስ እንዲሰኙ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ቤተ ክህነቱን ተሰናብተው ከካቴድራሉ ከመሰናበታቸው በፊት በቀረበላቸው መዝገብ ላይ ባሰፈሩት ሃሳብ፣ በኢራቅ ውስጥ ሰላም እና እምነት እንዲበዛ ምሕረትን ለመለመን መምጣታቸውን አስታውሰው፣ በኢራቅ ሕዝብ መካከል ወንድማማችነትን ለማሳደግ እና አገሪቱን መልሶ መገንባት እንዲቻል የድንግል ማርያም አማላጅነት እና ብርታት በመለመን መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

06 March 2021, 14:07