ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ "ምስጢረ ንስሐ የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ምሕረት የሚገኝበት ነው" ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ የጸሎት ሐሳባቸውን በቪዲዮ መልዕክት አማካይነት ይፋ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ለመጋቢት ወር 2013 ዓ. ም. እንዲሆን በማለት ስለ ምሕረት ጸጋ በተናገሩት የጸሎት ሃስብ፣ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ስላለው የፍቅር እና የምሕረት ግንኙነት አስታውሰውናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅዱስነታቸው የጸሎት ሃሳብ ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እንዲደርስ የሚያደርገው፣ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽ/ቤት፣ በአውታ-ረመረቡ አማካይነት መሆኑ ይታወቃል። የተስፋ ሙላት ያለበት የቅዱስነታቸው የጸሎት ሃሳብ፣ ምስጢረ ንስሐ በሕይወታችን ውስጥ የሚያስገኝልንን የመታደስ ኃይል በድጋሚ እንድናውቅ ያግዘናል። አዲስ እና ጥልቅ በሆነ መንገድ ስለ እርቅ ምስጢር ምንነት በሚገባ በመገንዘብ የእግዚአብሔርን ይቅርታ እና ዘለዓለማዊ ምሕረቱን ቀምሰን እንድናይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠይቀውናል። የመጋቢት ወር የቪዲዮ መልዕክት የሚጀምረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በምስጢረ ንስሐ በኩል የነፍስ ፈውስ ለማግኘት ሲሄዱ በማሳየት ነው።

“ኢየሱስ ይጠብቀናል፣ ይሰማናል፣ ይቅር ይለናል”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ሃሳባቸውን በገለጹበት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ እግዚአብሔር ኃጢአቶቻችንን በሙሉ እንደሚያውቅ እና የእርሱ የፍቅር ኃይል ከእኛ ማንነት እና ሥራችን ሁሉ በላይ መሆኑን አስረድተዋል። የእግዚአብሔርን የምሕረት ምስጢር መቀበል ፍርድን ለመቀብል ወደ ዳኛ ፊት እንደመቅረብ ሳይሆን፣ በፍቅር ተቀብሎን ሁል ጊዜ ምህረቱን ወደሚሰጠን አባት ዘንድ መቅረብ ነው ብለዋል። ምስጢረ ንስሐ ማለት ከምንናዘዛቸው ኃጢአቶች ይልቅ ከእግዚአብሔር ለመቀበል የምንፈልገው መለኮታዊ ፍቅር ማለት እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅር ከኃጢአታችን፣ ከሕግጋት፣ ከፍርድ እና ከውድቀት ሁሉ የሚበልጥ እና ቀዳሚ መሆኑን ቅዱስነታቸው አክለው አስረድተዋል።        

መሐሪ ካህናት

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ የቅዱስነታቸውን ቪዲዮ መልዕክት አስመልክተው ባቀረቡት ሃሳብ፣ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኑ መሐሪ ካህናትን እንዲሰጠን እንጸልይ ብለው፣ በማከልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔር የመሐሪ ካህናት ጸጋን ከዚህ በፊት መለመናቸውን አስታውሰዋል። ካህን እንደ መልካም እረኛ የሕዝቦቹን ስቃይ፣ ኃጢአት እና ከምሕረት አገልጋዮች ጋር ለመገናኘት ፍላጎት እንዳላቸው ያውቃል። የምንገኝበት ጊዜ የምሕረት ጊዜ ነው። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “Misericordia et misera” ወይም “ርኅራኄ እና ጸጸት”  በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ልዩ የምሕረት ኢዮቤልዩ ዓመት መጨረሻ ላይ፣ ካህናት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በርኅራኄ እና በትዕግስት የተሞሉ እንዲሆኑ ጋብዘዋል። ይህም እያንዳንዱ ካህን ለውጥን የሚያገኝበት፣ አባታዊ ርኅራኄን የሚመሰክርበት፣ በአርቆ አስተዋይነት የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመስጠት ልግስናውን የሚያሳይበት መንገድ መሆኑን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የካህናት ልብ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ልብ እና ወደ ጸጋው የቀረበ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ የካቲት 7/2013 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት፣ ምስጢረ ንስሐን ለሚያስገቡ ለጋስ ካህናት አድናቆታቸውን ገልጸው ምስጋናቸውንም አቅርበውላቸዋል። እግዚአብሔር ምሕረቱን መስጠት አያቋርጥም። በመሆኑም በምስጢረ ንስሐ አማካይነት ይቅርታን እና የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ምሕረትን ማወቅ እንችል ዘንድ እንጸልይ በማለት የመጋቢት ወር የጸሎት ሃሳባቸውን አቅርበውልናል።

10 March 2021, 14:11