ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሕጻን አላን አባት አብዱል ኩርዲ ጋር ሲነጋገሩ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሕጻን አላን አባት አብዱል ኩርዲ ጋር ሲነጋገሩ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከአላን አባት ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ተነገረ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ውስጥ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሦስተኛ ቀን በኤርቢል “ፍራንሶ ሐሪሪ” ተገኝተው ካቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመቀጠል፣ እ. አ. አ በመስከረም ወር 2015 ዓ. ም. ከወላጅ እናቱ ጋር በስደት ወደ አውሮፓ ሲጓዙ ባጋጠመው የባሕር ላይ አደጋ ሕይወቱን ያጣ የሦስት ዓመት ዕድሜ ሕጻን አባት ከሆኑት ከአብዱል ኩርዲ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው የአደጋው ሰለባ ከሆነው ሕጻን አባት ጋር ረዘም ያለ ጊዜን ወስደው መነጋገራቸው ታውቋል። በዚህ አደጋ ወቅት ሕጻን አላን ከወላጅ እናቱ እና ከወንድሙ ጋር በቱርክ በኩል በስደት ጉዞ የሜዲቴራኒያን ባሕር ለመሻገር በሚያደረጉት አደገኛ ጉዞ ወቅት ሦስቱም ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል። በባሕር ዳርቻ ግንባሩን በአሸዋ ውስጥ ቀብሮ የተነሳው የአላን ፎቶ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኩል በይፋ መታየቱ መላውን ዓለም እጅግ አስደንግጦ እንደነበር የሚታወስ ነው። የቅድስት መንበር እሑድ የካቲት 28/2013 ዓ. ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቅዱስነታቸው ከሕጻኑ አባት ከሆኑት ከአቶ ኩርዲ ጋር በአስተርጓሚ በኩል መነጋገራቸውን አስታውቋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ በማከልም ቅዱስነታቸው የአቶ ኩርዲን ሕመም እና ሐዘን መጋራታቸውን ገልጾ፣ እግዚአብሔር የሰው ልጅ ስቃይን የሚጋራ መሆኑን ቅዱስነታቸው መናገራቸውን በመግለጫው አስታውቋል። የሕጻኑ አላን አባት ክቡር አቶ ኩርዲ በበኩላቸው፣ ቅዱስነታቸው በአደጋው በማዘን ስላጽናኗቸው እና አገራቸውን ለቅቀው ለሚሰደዱ ሰዎች በሙሉ ሰላምን እና የእግዚአብሔርን ጥበቃ በመመኘት ብርታትን የሚሰጥ መልዕክት በማስተላለፋቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በባሕር ዳርቻ ወድቆ የታየው የልጃቸውን ምስል በስጦታ መልክ ለቅዱስነታቸው ማቅረባቸው ታውቋል።

በባሕር ዳርቻ ወድቆ የታየው የሕጻን አላን አስከሬን የሚያሳይ ምስል
በባሕር ዳርቻ ወድቆ የታየው የሕጻን አላን አስከሬን የሚያሳይ ምስል

የሶርያ ኩርዶች ዜግነት ያላቸው ሕጻን አላን፣ ወላጅ እናቱ እና ታላቅ ወንድሙን ጨምሮ በቁጥር 20 የሚሆኑ ስደተኞች በጀልባ ተሳፍረው ወደ አውሮፓ ሲጓዙ የግሪክ ደሴት በሆነችው ኩ አካባቢ በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት እ. አ. አ በመስከረም 2/2015 ዓ. ም. ሌሊት መሞታቸው ይታወሳል። የሕጻኑ አላን፣ የእናቱ እና የወንድሙ ጋሊብ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በቀጣዩ ዕለት መፈጸሙ ይታወሳል።   

08 March 2021, 13:09