ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቃራቆሽ ኢራቃዊያን የህብረተሰብ ትስስር እንደገና እንዲገነቡ ጥሪ አቀረቡ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም ደረስ 33ኛውን ሐዋርያዊ ግጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢራቅ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው የነበራቸውን የሶስተኛውን ቀን ጉብኝት በየካቲት 28/2013 ዓ.ም ሲጀምሩ ወደ ኤርቢል በመጓዝ ሲሆን በኤርቢል የነበራቸውን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ ቅዱስነታቸው በተመሳሳይ ቀን ቃራቆሽ በመባል ወደ ምትታወቀው ከተማ አቅንተዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ክርስቲያኖች በይቅርታ እና በወንድማማችነት ላይ ተመስርተው ማህበረሰባቸውን እንደገና እንዲገነቡ ለቃራቆሽ ሕዝቦች ባስተላለፉት መልእክት ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት እሁድ ዕለት በቃራቆሽ በሚገኘው “ያለ አዳም አጢአት የተጸነሰች እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” የሚል መጠሪያ በተሰጠው ቤተክርስቲያ ውስጥ ከክርስቲያኖች ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኢራቅ ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በዚሁ በሦስተኛው ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ሲቀጥሉ በሰሜናዊ ኢራቋ የምትገኘውን የቃራቆሽ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን “ያለ አዳም አጢአት የተጸነሰች እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ቤተክርስቲያ ጎብኝተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ለምዕመናን ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት ከቃራቆሽ ምእመናን መካከል የመገኘት እድል ስለሰጠኝ እግዚአብሔርን አመስግናለሁ ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በወቅቱ ላስተላለፉት የሶርያ ካቶሊኮች የአንጾኪያ ፓትርያርክ ኢግናሴ ዮሱፍ ዮዋንንም ቅዱስነታቸው አመስግነዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ወስጥ በተገኙበት ወቅት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ወስጥ በተገኙበት ወቅት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ወደ አንተ ስመለከት ፣ የቃራቆሽ ህዝብ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ብዝሃነት ይታየኛል ፣ ይህ ደግሞ መላው ክልሉ ለወደፊቱ የሚጠብቀውን ውበት የሚያሳይ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው “እዚህ መገኘታችሁ ውበት አንድ ወጥ ብቻ የሆነ ነገር ሳይሆን ነገር ግን በልዩነት ውስጥ የሚበራ መብራት እንደ ሆነ እንገነዘባለን” ብለዋል።

ቃራቆሽ

በአራማይክ ቋንቋ ባኪዲዳ ተብሎ የሚጠራው ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን የሚገኝበት ስፍራ ነው። ይህች ከተማ በነነዌ መስተዳድር ሥር ከምትገኝ ከሞሱል ደቡብ ምስራቅ 32 ኪ.ሜ እና ከኤርቢል በስተ ምዕራብ 60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ የአሦራውያን ከተማ ናት። በቁጥር እጅግ ብዙ የክርስቲያን ማሕበረሰብ የሚኖርባት ከተማ ስትሆን፣ ቃራቆሽ እ.አ.አ በ 2014 ዓ.ም እስላማዊ መንግስት በሚባል አገዛዝ ወረራ የተፈጸመባት ከተማ ስትሆን በወቅቱ በርካታ ሰዎች ተገድለው፣ በንብረት ላይ ውድመት ያስከተለ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን ለማትረፍ ከተማዋን ጥለው መሰደዳቸው ይታወሳል። ከተማዋ ነፃ በወጣች እ.አ.አ በ 2016 ዓ.ም ከቤተክርስቲያኗ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተደረገ ድጋፍ ህዝቧ ወደ ቤታቸው እንዲመለስ ለማበረታታት የመልሶ ግንባታ ስራዎች ተደርገዋል።

በተጨማሪም “አል-ታሂራ” በመባል የሚታወቅ ቤተክርስቲያን በስፍራው የሚገኝ ሲሆን የተገነባውም እ.አ.አ ከ 1932 እስከ 1948 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተገነባው የሶሪያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቃራቆሽ ውስጥ የሚገኝ ትልቁ ቤተክርስቲያን ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2014 ዓ.ም ቤተክርስቲያኗ እስላማዊ መንግሥት እገነባለሁ ብሎ በተነሳው በአይ ኤስ ሚሊሻዎች ቤተክርስቲያኑ እንዲረክስ ተደርጎ፣ ፈርሶ፣ ተደምስሳ ተቃጥሎ ወደ ምሽግነት ተቀይሮ የነበረ ሲሆን ሆኖም ስፍራው ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ከወጣ በኋላ ቤተክርስቲያኑ ተጠግኖ ወደ ቅዱስ ስፍራነት ተመልሷል።

በሞት ላይ የሕይወት ድል ይጎናጸፋል

የክልሉን አስቸጋሪ ታሪክ በማስታወስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የጥቃት ፣ የጥላቻ እና የጦርነት አጥፊ ኃይል” ምልክቶችን በመጥቀስ ምን ያህል አገሪቷን እንዳፈራረሰ እና ምን ያህል እንደገና መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ በምሬት” ተናግረዋል። ሆኖም የህብረተሰቡ መሰብሰብ ሽብርተኝነት እና ሞት የመጨረሻ ቃል እንደሌላቸው የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

“የመጨረሻው ቃል የእግዚአብሔር እና በኃጢአትንና በሞት ላይ ድል አድራጊ የሆነው የልጁ ነው” በማለት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሽብርተኝነት እና በጦርነት ውድመት መካከል እንኳን በእምነት ዐይን የሞትን የሕይወት ድልን ማየት እንችላለን” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አረጋግጠዋል።

በመቀጠልም “በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን አመስገኑ” እና “በጸጋው እኛን የሚጠብቀን እና ፈጽሞ በማያሳዝነንን” በአምላክ በመታመን በእምነት ላይ የነበሩትን የአባቶቻቸውን እና እናቶቻቸውን ምሳሌነት እና ትሩፋትን ማስታወስ ይገባል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ወስጥ በተገኙበት ወቅት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ወስጥ በተገኙበት ወቅት

“ይህንን ውርስ አጥብቃችሁ ያዙ! እሱ የእናንተ ጥንካሬ ምንጭ ነው! ” በማለት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ  "አናንተ ብቻችሁን አይደላችሁም! መላው ቤተክርስቲያን በጸሎት እና ተጨባጭ በሆነ መልኩ ድጋፉን ለእናንተ ያቀርባል። እናም በዚህ ክልል ውስጥ ብዙ ሰዎች በችግራቸው ጊዜ እንኳን ሳይቀር በሮቻቸውን ለሌሎች ክፍት አድርገዋል” ብለዋል።

ለወጣቶች እና ለአዛውንቶች መልሶ ለመገንባት የቀረበ ጥሪ

በተጨማሪም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሁሉም ህዝቦች ዕጣ ፈንታ በሚመራው የእግዚአብሔር ጸጋ ላይ በመመስረት በአዲስ መልክ ለመጀመር ጊዜው አሁን እንደ ሆነ አስፈላጊነቱ ለምዕመናኑ ገልጸዋል። “ውድ ጓደኞች ፣ ይህ ህንፃዎችን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቦችን እና ቤተሰቦችን ፣ ወጣቶችን እና አዛውንቶችን አንድ የሚያደርጋቸውን የህብረተሰብ ትስስር ወደ ነበረበት ለመመለስ የምንሰራበት ወቅት ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።

የነቢዩ ኢዩኤልን ቃል በመጥቀስ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽ ይተነብያሉ ፣ ሽማግሌዎችሽም ሕልምን ያልማሉ፣ ወጣት ወንዶችም ራእይ ያያሉ” (ኢዩኤል 3፡1)  የሚለውን በመጥቀስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ገለጹት ወጣቶች እና አዛውንቶች ማሕበርሰቡን በመገንባት ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። አንድ ላይ ሆነው ወጣቶች እና አረጋውያን አሮጌ ሕልሞች ፣ ትንቢቶችን ወስደው እውን ማድረግ ይችላሉ በማለት የተናገሩ ሲሆን በዚያ መንገድ እግዚአብሔር የሚሰጠንን ስጦታዎች ጠብቀን እናስተላልፋለን እናም ልጆች መሬት ፣ ባህልና ወግ ብቻ ሳይሆን ህያው የእምነት ፍሬዎችን እንደሚወርሱ እናውቃለን ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ “ስለዚህ እኔ አበረታታችኋለሁ” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን  “ማን እንደሆናችሁ እና ከየት እንደመጣችሁ አትርሱ! እርስ በእርስ የሚያስተሳስራችሁን ማሰሪያዎችን አትርሱ! ስር መሰረቶቻችሁን ጠብቃችሁ መኖር አትዘጉ” ብለዋል።

በጦርነቱ ጨለማ ቀናት እና በዓለም አቀፍ የጤና ድንገተኛ ሁኔታ ውስጥም ጨምሮ በአስቸጋሪ ጊዜያት እንኳን ኢየሱስ ከጎናችን ነው ብለዋል። በተጨማሪም ምድሪቱ የተባረከችላቸው ብዙ ቅዱሳን በቅርቡ በሚገኙት ጎረቤት አገሮች እንደ ሚገኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው በመካከላችን የሚኖሩትም የእግዚአብሔርን መገኘት የሚያንፀባርቁ ናቸው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ወስጥ በተገኙበት ወቅት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ወስጥ በተገኙበት ወቅት

የይቅርታ እና የምስጋና አስፈላጊነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የልጃቸውን ገዳዮች ይቅር ያሉትን ወይዘሮ ዶሃ ሳባህ አብደላ እና በክልሉ የተፈጸሙ ግፍ የመጀመሪያ የዐይን ምስክር የነበሩ አባ አማር ያኮ ምስክርነትን በመጥቀስ የተናገሩት ቅዱስነታቸው በሕይወት ሂደት ውስጥ ለሚፈጸሙብን በደሎች ይቅርታ ማደረግ ይገባል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የወይዘሮ ዶሃን ቃል በመያዝ “ከአሸባሪዎች ጥቃት በሕይወት የተረፉት ሰዎች ይቅርታ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው” በድጋሚ አረጋግጠዋል። ይህ ይቅር ባይነት ቅዱስ አባታችን እንደ ገለጹት ከሆነ “በፍቅር ለመቆየት እና ክርስቲያናዊ ሆኖ ለመቀጠል አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አክለውም ይቅር ለማለት መቻል እና ተስፋ ላለመቁረጥ ድፍረትን እና ብርታትን ለማግኘት በፍቅር ጎዳና ላይ ለመራመድ አሁንም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ፣ ነገር ግን አሁንም በእግዚአብሔር በኩል እና በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ጋር “እንብይ ለሽብርተኝነት፣ በሃይማኖት ስም ማጭበርበር ” ይቅር ማለት እንደ ሚገባ አክለው ገልጸዋል።

ከዚያ በኋላ የአባ አማር ምስክርነትን በመጥቀስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ተናገሩት በመልካምም ሆነ በክፉ ጊዜያት ሁል ጊዜ በደስታ የሚሞላውን ጌታ አመሰገኑ ያሉ ሲሆን አክለውም “ምስጋና የእግዚአብሔርን ስጦታዎች እና ተስፋዎች ስናስታውስ የተወለደ እና የሚያድግ ነው” ያለፉ ትዝታዎች የአሁኑን ሁኔታ ቅርፅ እንዲይዝ በማደረግ ወደ ፊት ይመሩናል ብለዋል።

ለጸሎት የቀረበ ጥሪ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ልብን ለመለወጥ እና ልብን ለማደስ እንዲሁም የሕይወት ባህል ድል እንዲመጣ ፣ በሁሉም ወንዶችና ሴቶች መካከል እርቅ እና በሁሉም ዘንድ የወንድማማችነት ፍቅር እንዲኖር፣ ልዩነቶችን እና ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ባህሎችን በማክበር ይቻል ዘንድ ሁሉም እንዲጸልዩ” ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም “ጥፋቶች እና ጉዳቶች ቢኖሩም ህይወትን መስጠት ለሚቀጥሉ” የአገሪቱ እናቶች እና ሴቶች ሁሉ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ እንዲከበሩ ፣ እንዲጠበቁ እና እድሎች እንዲሰጧቸውም አሳስበዋል።

በማጠቃለያ ንግግራቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ገለጹት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የተማፀኑ ሲሆን ምንም እንኳን በቃራቆሽ “ያለ አዳም አጢአት የተጸነሰች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን አናት ላይ ያለው ሐውልት በተፈጸመበት ጥቃት በደል የደረሰበት እና አክብሮት የጎደለው የነበረ ቢሆንም የእግዚአብሔር እናት ግንባር በፍቅር እኛን እያየች እንደቀጠለች አስገንዝበዋል። ምክንያቱም እናቶች የሚያደርጉት እንደዚህ ነው-ያጽናናሉ ፣ ያጽናናሉ ሕይወትም ይሰጣሉ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጉብኝታቸው ማብቂያ ላይ በክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ያሳረፉ ሲሆን

“ለቃራቆሽ እና ለመላው ኢራቅ የተስፋ ምልክት ከሆነችው ከዚህ የፈረሰች እና እንደገና ከተገነባችው ቤተክርስቲያን የሰላም ስጦታ በሆነችው በድንግል ማርያም አማላጅነት የእግዚአብሔርን ጥበቃ እማጸናለሁ” የሚል ጹሑፍ ማስፈራቸው ተገልጿል።

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ ቃርቆሽ “ያለ አዳም ኃጥአት የተጸነሰች” እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመባል የሚታወቀው ቤተክርስቲያን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት
07 March 2021, 13:20