ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለባንግላዴሽ 50 ኛ ዓመት የነፃነት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ማስተላለፋቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአሁኑ ወቅት ሁለት ወሳኝ ልዩ በዓላትን በማክበር ላይ ለሚገኙ የባንግላዴሽ ሕዝቦች በቪዲዮ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ባንግላዴሽ ከቅኝ ግዛት ወጥታ ነጻነቷን የተጎናጸፈችበት 50ኛው አመት እና እንዲሁም የባንግላዴሽ “የአገሪቷ አባት” በመባል የሚታወቁ፣ አገሪቷ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ የአገሪቷ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉት ታዋቂው ሼክ ሙጂቡር ራህማን መቶኛ አመት የልደት በዓለ በመከበሩ ምክንያት ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል። 

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለት ታሪካዊ ልደቶችን በማክበር ላይ ለሚገኙ የባንግላዴሽ ሕዝቦች ረቡዕ ዕለት መጋቢት 15/2013 ዓ.ም በቪዲዮ መልእክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን የመጀመሪያው ክብረ በዓል ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው የሼክ ሙጂቡር ራህማን መቶኛ አመት የልደት በዓል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባንግላዴሽ ከቅኝ ግዛት ሥር ነፃ ወጥታ ነፃነቷን የተጎናጸፈችበት 50 ኛ ዓመት ምክንያት በማደረግ ነበር ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን ያስተላለፉት ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን የጀመሩት ለባንግላዴሽ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለተወዳጅ ለባንግላዴሽ ሕዝቦች ሁሉ “ከልብ የመነጨ ሰላምታዬ እና የመልካም ምኞቴ” ይድረሳችሁ በማለት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ለአገሪቷ እና ለአገሪቷ ሕዝቦች ሁሉ መልካም የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እንደ ሚመኙ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ገለጸዋል። “በእነዚህ ዓመታት ባንግላዴሽ ስለተቀበለቻቸው በርካታ በረከቶች እግዚአብሔርን ለማመስገን የምታደርጉትን ተግባራት እኔም ከእናንተ ጋር እቀላቀላለሁ” ብለዋል።

ሼክው ለአገሪቷ ያወረሱት ውርስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል “ባንግላዴሽ ‘ወርቃማው ባንግላ’ የሚል መጠሪያ ያላት፣ ልዩ የተፈጥሮ ውበት ያለባት ሀገር እና በውስጧ ያሉትን የተለያዩ ባህሎች እና ማህበረሰቦች በማክበር የቋንቋ እና የባህል አንድነት ለመቀላቀል የምትጥር ዘመናዊ ሀገር ናት” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው ይህም ሼክ ሙጂቡር ራህማን ለአገሪቷ ሕዝቦች ካወረሱዋቸው ቅርሶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ የሼክ ሙጂቡር ራህማን “በጥበብ ፣ በማስተዋል እና በራዕይ የተሞሉ፣ የውይይት ባህልን ማራመድ ተገቢ እንደ ሆነ ያስረዱ” ጥበበኛ ሰው እንደ ነበሩ ያስረዱ ሲሆን “እያንዳንዱ ሰው በነጻነት መኖር የሚችልው እንዲህ ባለ ብዝሃነት እና ሁሉን አቀፍ ማህበረሰብ ውስጥ ብቻ መሆኑን አስቀደመው ተረድተው ነበር” ያሉ ሲሆን ይበልጥ ፍትሃዊ እና በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ ዓለም መገንባት እንደሚቻል፣ በእዚህም መልኩ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንደ ሚችል አስመስክረዋል ብለዋል።

የባንግላዴሽ የመጀመሪያ ተሞክሮ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2017 ዓ.ም ወደ ባንግላዴሽ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ መልእክታቸውን የቀጠሉ ሲሆን ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ፈለግ በመከተል “የዚህ ባህላዊ ቅርስ እና ተፈጥሮአዊ የሆነ መልካም ተሞክሮ በአገሪቷ በነበራቸው ቆያት መመልከታቸውን” አክለው ገልጸዋል።

ባንግላዴሻዊያን  “ከመነሻው ጀምሮ ለህዝቦቻቸው አጋርነታቸውን የገለጹ ፣ የመጀመሪያዎቹን ችግሮች በማሸነፍ አብሮ ለመሄድ የሚሞክሩ እና በብሔራዊ ግንባታ ላይ ያተኮረ የልማት ተግባራት በመከናወናቸው፣ በእዚህ ረገድ እያደርጉ የሚገኙት ተግባር  የሊቃነ ጳጳሳት ልብ ውስጥ ሁል ጊዜ ልዩ ቦታ አላቸው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል “በቅድስት መንበር እና በባንግላዴሽ መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል” ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በተመሳሳይ መልኩም “እኔ በባንግላዴሽ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረኩበት ወቅት የተመለከትኩት በሃይማኖቶች መካከል ያለው የሃሳብና የውይይት ሁኔታ እያደገ መምጣቱ ምዕመናን ስለ ሕይወት ትርጉም እና ዓላማ ያላቸውን ጥልቅ እምነት በነፃነት እንዲገልጹ እና በዚህም አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉ እተማመናለሁ፣ለሰላማዊ እና ለፍትሃዊ ማሕበረሰብ አስተማማኝ መሠረት የሆኑትን መንፈሳዊ እሴቶችን ለማሳደግ የምታደርጉት ጥረት ከልብ አደንቃለሁ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ-የባንግላዴሽ ወዳጅ ናቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቪድዮ መልእክታቸውን ከማገባደዳቸው በፊት እንደ ተናገሩት “የባንግላዴሽ የፖለቲካ ሕይወት ከወደፊቱ የዴሞክራሲና የጤና ሁኔታ አኳያ በመሠረቱ ከምስረታው ራዕይ እና ከልብ በመነጨ መልኩ በሚደርግ ውይይት እና ብዝሃነት ሕጋዊ አክብሮት ከመስጠት ጋር የተቆራኘ ነው” የሚል ጽኑ እምነት እያደሱ እንደ መጡ የገለጹ ሲሆን የባንግላዴሽ ህዝብ በእነዚህ ዓመታት ሊያሳኩት የፈለጉት ተግባር እንደ ሆነ አክለው ገልጸዋል።

“እንደ ባንግላዴሽ ወዳጅ እያንዳንዳችሁ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለምትወክሉት ክቡር ህዝብ ሰላምና ብልጽግና እንድትሰሩ፣ እንደገና ራሳችሁን እንድትሰጡ አበረታታለሁ። እናም ሁላችሁም በእዚህ አግባብ እንድትቀጥሉ እጠይቃለሁ። ለስደተኞች ፣ ለድሆች ፣ ለችግረኞች እና ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ሁሉ ልግስና እና ሰብአዊ አገልግሎት መስጠታችሁን” እንድትቀጥሉ አደራ እላለሁ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ያስተላለፉትን መልእክት አጠናቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከሕዳር 26 እስከ ታኅሳስ 2/2017 ዓ.ም. ድረስ 21ኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝት በቅደም ተከተል በማያንማር (የቀደሞ ስሟ በርማ) እና በባንላዲሽ  ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በማያን ማር ያደርጉት ሐዋሪያዊ ጉብኝት “የሰላም ልዑክ” በሚል መሪ ቃል ያነገበ እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በመቀጠልም ቅዱስነታቸው በባንግላዲሽ አድርገውት ለነበረው  ሐዋርያዊ ጉብኝት ደግሞ የመረጡት መሪ ቃል “ሰላም እና ሕብረት” የሚል እንደ ነበረ መግለጻችን ይታወሳል። ባንግላዲሽ 166 ሚልዬን የሕዝብ ብዛት ያላት ሀገር ናት። ከጠቃላይ የሕዝብ ብዛቷ ውስጥ 350,000 የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የሚገኙባት አገር ስትሆን ይህም በመቶኛ ሲሰላ 0.24 % የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ናቸው። አብዛኛው የባንግላዲሽ ሕዝብ የሙስሊም እምነት ተከታትይ ሲሆን፣ የቡዳ እና የሌሎች ባሕላዊ እመነት ተከታዮችን መኖሪያ አገር ናት ባንግልዲሽ።

24 March 2021, 20:09