ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ እምነት በፊሊፒንስ የገባበትን 500ኛ አመት አከበሩ!

የካቶሊክ እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፊሊፒን አገር የገባበትን 500ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ትላንት መጋቢት 05/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን የካቶሊክ እምነት ወደ ፊሊፒን የገባው ታዋቂው ፖርቱጋላዊ የአገር አሳሽ፣ ፌርዲናንድ ማጂላን እ. አ. አ በ1521 ዓ. ም. ሰቡ የተባለች አውራጃን በጎበኛት ወቅት መሆኑ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ከዚህም ጋር ተያይዞ የክርስትና እምነትም ወደ ፊሊፒን የገባው ከ500 ዓመት በፊት መሆኑን በማስታወስ በፊሊፒን የሚገኙ ሁለቱ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች በዓሉ ከሚከበርበት ከሚያዝያ ወር አስቀድመው በተለያዩ ዝግጅቶች የደመቁ በዓላትን በማክበር ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የክርስትና እምነት ወደ ፊሊፒንስ የደረሰበትን 500 ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ባደረጉት ስብከት ፊሊፒናውያን እንደ ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት ለክርስቶስ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያድሱ አሳስበዋል።

በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገር በምትገኘው ፊሊፒንስ የክርስትና እምነት የደረሰበትን የ 500 ዓመታት ክርስትናን ለማስታወስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሁድ ዕለት ከፊሊፒንስ ቤተክርስቲያን ጋር ያላቸውን ሕብረት ገልጸዋል። ቀደም ሲል የማኒላ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግልን ጨምሮ በርካታ የፊሊፒንስ ቤተክርስቲያን ተወካዮችን በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ የተደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴ ተከታትለዋል።

ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ባደረጉት ስብከት ፊሊፒንስ ከግማሽ ሺህ ዓመት በፊት የወንጌልን ደስታ እንደተቀበለች “ይህ ደስታ በሕዝባችሁ ውስጥ ይታያል” ብለዋል። “በዓይኖቻችሁ፣ በፊቶቻችሁ፣ በመዝሙሮቻችሁ እና በጸሎቶቻችሁ ውስጥ ይህንን እምነት እናየዋለን” ብለዋል። ለመላው ዓለም እና ለክርስቲያን ማሕበረሰብ ስለምሰጡት ደስታ ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፊሊፒናዊያን “ልባም እና ታታሪ ሰራተኞች” መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን የሚሰጡትን የእምነት ምስክርነት በመቀጠል “በስብከተ ወንጌል ሥራ መጽናት” እንዳለባቸውም አሳስበዋል።ማንም እንዳይጠፋ የእግዚአብሔር ቅርበት የወንጌል መልእክት ያለማቋረጥ ለሌሎች ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።

በፊሊፒንስ ውስጥ ያለችው ቤተክርስቲያን የመወለዷን 500ኛ ዓመት በዓል ስታከብር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የፊሊፒንስ ካቶሊኮች በሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ጎዳና በድፍረት እንዲራመዱ አሳስበዋል።“ወንጌልን ለማወጅ ፣ ለማገልገል እና ለመውደድ በጭራሽ አትፍሩ” ብለዋል። “በደስታችሁ ሰዎች ስለቤተክርስቲያን በሚያስቡበት ወቅት ደስተኛ እንዲሆኑ እርዷቸው” በማለት አክለው ገለጸዋል።

የደስታችን ምንጭ ኢየሱስ ነው

ወደ በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ሐሳባቸውን በማዞር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ እንደ ገለጹት የቅዱስ ወንጌልን መልእክት ልብ የያዘ መሆኑን ጠቁመው “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ 3፡16) የሚለው የወንጌል መልእክት ሀሳብ ወይም አስተምህሮ ሳይሆን ራሱ ኢየሱስ መሆኑን አክለው ገለጸዋል።

የደስታችን ምንጭ የሚገኘው ደስታን እንዴት ማግኘት እንደ ሚቻል ከሚገልጽ ወይም ከሚያስተምር ፅንሰ-ሀሳብ ሳይሆን በሕይወት ጉዞ ሁሉ አብሮ የመኖር እና የመወደድ ትክክለኛው ተሞክሮ በሚገልጸው በኢየሱስ አማካይነት ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ ስለእለቱ የወንጌል ምንባብ ሁለት ገጽታዎች የተናገሩ ሲሆን “እግዚአብሔርም እንዲሁ ይወዳል” እና “እግዚአብሔር ሰጠ” በተሰኙት ፅንሰ-ሀሳቦች ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።

‘እግዚአብሔር እጅግ በጣም ወደደ’

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር በጣም ስለወደደ” እኛ በጠፋን ጊዜ እኛን ለመፈለግ እና እኛን ከፍ ለማድረግ እንደመጣ የተናገሩ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ “እርሱ ሁል ጊዜ በፍቅር ተመለከተን ፣ በእዚህ ፍቅር  የተነሳ ልጁ ሥጋ ለብሶ በእኛ መካከል እንዲመጣ አደረገ” ብለዋል። “በኢየሱስ ውስጥ እግዚአብሔር ስለ ህይወታችን ትክክለኛ ቃል ተናገረ -አልጠፋችሁም ፣ የተወደዳችሁ ናችሁ፣ ለዘላለም የተወደዳችሁ ናችሁ” የሚለውን ማረጋገጫ ሰጠን ብለዋል። ምንም እንኳን ቅዱስ ወንጌል “ልባችንን ያሰፋ እና የእግዚአብሔርን ፍቅር ትልቅነት እንድንገነዘብ የሚያደርገን ቢሆንም” አንዳንድ ጊዜ እኛ “መከራን ፣ ሀዘንን እና እራሳችንን ማዕከል ያደርገ ሃይማኖትን እንመርጣለን” ብለዋል።

‘እግዚአብሔር ሰጠ’

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ ስለ እግዚአብሔር የፍቅር ተግባር ድርጊት ላይ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “እግዚአብሔር አንዲያ ልጁን ለእኛ የሰጠው” እኛን ለማዳን ነው ብለዋል። ፍቅር ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳመለከቱት ፣ ከራሳችን ውስጥ እንድነወጣ ያደርገናል፣ እናም ፍቅር ሁል ጊዜ እራሱን ሙሉ በሙሉ ለመስጠት ይፈልጋል ብለዋል።

“ያ የፍቅር ኃይል ነው ፣ የራስ ወዳድነታችንን ቅርፊት ይሰብራል ፣ በጥንቃቄ ከተገነቡት የፀጥታ ዞኖቻችን ውስጥ እንድንወጣ ያደርገናል፣ ግድግዳዎችን ያፈራርሳል እንዲሁም ፍርሃትን ያሸንፋል ፣ እናም እራሱን በነፃ ለመስጠት” ዝግጁ የሆነ ነጻ ፍቅር ነው ብለዋል። የእግዚአብሔር ፍቅር በኢየሱስ ውስጥ ነው ለእኛ የተገለጸው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እርሱ ለእኛ ራሱን ስጦታ አድርጎ እንዳቀረበ” ገልጸዋል።

ራስን በመስጠት የሚገኝ ደስታ

እርስ በርሳቸው በሚዋደዱ እና ህይወታቸውን በፍቅር በሚካፈሉ ሰዎች ላይ እንደምናየው “በተወደድን መጠን መስጠት የመቻላችን መጠን እየጨመረ ይሄዳል” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አንዳንድ ጊዜ በክብር ህልሞች ወይም በቁሳዊ ሀብቶች የሐሰት ደህንነት ውስጥ ደስታን እንፈልጋለን ብለዋል። ሆኖም እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ሙሉ በሙሉ ራስን በመስጠት ብቻ ነው ፣ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በመስጠት እንደሚያሳየው እኛም እርስ በእርሳችን መሰጣጠት ይገባናል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ሕይወት የሚያስተምረን ደስታ የሚገኘው በነፃ በመወደዳችን የተነሳ መሆኑን  በመገንዘብ ብቻ እንደ ሆነ” የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም ሕልሞቻችንን በመጋራት እና የመርከብ መሰበር አደጋ ሲያጋጥመን የሚረዳን እና የሚመራን ሰው እንዳለ በማወቅ ጭምር” ሊሆን እንደ ሚገባው ከገለጹ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

14 March 2021, 11:43