ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በማይናማር ሰልፈኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ የካቲት 24/2013 ዓ.ም በቫቲካን ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካጠናቀቁ በኋላ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ እየተወሰደ በሚገኘው ከፍተኛ የኃይል እርምጃ እንደ ሚቃወሙ የገለጹ ሲሆን ለማያንማር ሕዝብ ያላቸውን ድጋፍ አክለው ገልጸዋል።
የፀጥታ ኃይሎች የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሐገሪቷ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ቢያንስ 30 ሰዎችን ገድለዋል ፡፡
እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችለውን ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ በመቃወም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባስተላለፉት መልእክት ገዥው ወታደራዊ ጁንታ ሁከቱን እንዲያቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “በውይይት ጭቆናን፣ ቀርቦ በመነጋገር ደግሞ አለመግባባትን ማሸነፍ እንደ ሚቻል በማሳየት የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትን ትኩረት ለመሳብ እፈልጋለሁ” ብለዋል ፡፡
በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “የማይናማር ህዝብ ምኞት በሁከት እንዳይደናቀፍ እንዲያረጋግጥ” አሳስበዋል።
“በዚያች የተወደደች ሀገር ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ጥላቻ እና ኢፍትሃዊነት ለማስወገድ እና ለእርቅ መንገድ የሚፈጥሩበት የወደፊቱ ተስፋ ይኖራቸው ዘንድ መሥራት ይገባል” ብለዋል።
የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት
ታታማውዶ በመባል የሚታወቀው የማይናማር ወታደራዊ ኃይል እ.አ.አ በካቲት 01/2021 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት ስልጣንን ተቆጣጥሮ ብዙ የፖለቲካ መሪዎችን አስሯል ፡፡ በወቅቱ የአገሪቱ መሪ የነበሩ፣ ተጨባጭ መሪ እና የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ የሆኑት ኦንግ ሳን ሱ ኪይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው “ፍርሃት እና ስጋት” መፍጠሩ የሚታወስ ሲሆን በህገ-ወጥ መንገድ ከውጭ አገር የመጡ የመገናኛ መሣሪያዎችን ይዘው ተገኝተዋል የሚሉ በርካታ ክሶች ቀርበውባቸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት ጥር ወታደራዊው ጁንታ የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ እና ዴሞክራሲን ወደ ነበረበት ለመመለስ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።
“በመጨረሻም ከአንድ ወር በፊት የገለፅኩትን ምኞት ደግሜ እላለሁ ፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በማይናማር እየተደርገ የነበረው የዴሞክራሲ አቅጣጫ የመከተል ሂደት የታሰሩት የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች በሚለቀቁበት ተጨባጭ እንቅስቃሴ ሊቀጥል ይችላል” ብለዋል።
የኃይል እርምጃ
የሊቀ ጳጳሱ ጥሪ በቅርቡ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እየተወሰደ የሚገኘው ከባድ የኃይል እርምጃ ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ ሲሆን መፈንቅለ መንግስቱን በመቃወም ለአንድ ወር ያህል ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ከተካሄዱ በኋላ የፀጥታ ኃይሎች በሳምንቱ መጨረሻ በመላው አገሪቱ በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የቀጥታ ጥይት ተኩስ መጠቀም መጀመራቸው ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን ጥሪ ባቀረቡበት ረቡዕ የካቲት 24/2013 ዓ.ም በእዚህ ቀን ብቻ ፖሊሶች ዴሞክራሲን በሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በወሰዱት እርምጃ ቢያንስ 9 ሰዎችን ገድለዋል ፡፡