ፈልግ

የከለዳውያን አገር ኡር፣ የአብርሐም አገር የከለዳውያን አገር ኡር፣ የአብርሐም አገር  

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በአብርሐም ምድር ኡር የሚጀምር መሆኑ ተነገረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተመኝተው የነበረውን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያሟላ እንደሚሆን ይነገራል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ የእምነታችን አባት የሆነው የአብርሐም ምድር፣ ኡርንም እንደሚጎበኙ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያስረዳል። ይህ ሥፍራ የሦስቱ ሐይማኖቶች ማለትም የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነቶች የጋራ ሃብት ሲሆን፣ ቅዱስነታቸው በዚህ ሥፍራ ተገኝተው ከሐይማኖት መሪዎቹ ጋር የሰላም፣ የተስፋ እና የወንድማማችነት ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር መሠረት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ. ም. በኡር በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በናይፍ የሚገኙትን ታላቁ አያቶላ ሰይድ አሊ አል ሁሴን አል ሲስታንን ከጎበኟቸው በኋላ በባግዳድ በሚገኝ ቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት የሚያቀርቡ መሆናቸው ታውቋል። የእምነታቸው አባት የአብርሐም ምድር ኡር፣ ሦስቱም ሐይማኖቶች እንደ ጋራ ምድር የሚመለከቱት ምድር በመሆኑ በሐይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ የሚመቸ ሥፍራ እንደሆነ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የእኛ ዘመን በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በቁ. 3 ላይ ገልጸውታል። እ.አ.አ በ2000 ዓ. ም. የተከበረውን የኢዮቤልዩ ዓመት ምክንያት በማድረግ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ቢመኙም ጊዜው በኢራቅ ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ የነበረበት በመሆኑ ሳይጎብኙት ቀርተዋል። ከሃያ ዓመታት ቆይታ በኋላ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚጎበኙት ኢራቅ፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንዱም ያልጎበኙት መሆኑ ታውቋል።

የአርኪዮሎጂ ጥናት ማዕከል እና የባሕል ታላቅነት የሚታይበት

ከኤፍራጥስ በ15 ኪ. ሜ. ርቀት የምትገኝ ጥንታዊት የኡር ከተማ፣ ባሁኑ ጊዜ በአረብኛ “ተል አል ሙቃያር” ሲተረጎም “የጥድ ጉብታ” እየተባለ የሚጠራው ስፍራ፣ በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኡር የሚል ስያሜ እንደተሰጠው እና በተጨማሪም “የከለዳውያን አገር ኡር” ተብሎ በመጠራት የአብርሐም አገር እንደሆነ ሲነገር መቆየቱን ጥንታው መዛግብት ያረጋግጣሉ። የአርኪዮሎጂ ተመራማሪ የነበሩት ሄንሪ ሪጅናል ሆላንድ ሃል እ.አ.አ በ1919 ዓ. ም. ባካሄዱት ጥናት የቅድመ-ታሪክ አስደናቂ ቅሪቶች ማግኘታቸው ይታወሳል። በኡር አካባቢ የሚገኝ ዲ ቃር የተባለ ሌላው አካባቢ በአርኪዮሎጂ ጥናት ዘርፍ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሌሎች 47 ስፍራዎችን የያዘ መሆኑ ታውቋል። በመሆኑም በኡር የሚገኑ ታሪካዊ ቦታዎች በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት ተመዝግቦ ያለ እና ባሁኑ ጊዜ ለአገሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ እገዛን በማድረግ ላይ የሚገኝ ታሪካዊ ሥፍራ ነው።

እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጣቀሻነት

በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ከለዳዊያን አገር ኡር የሚናገር እና ከአብርሐም ጋር የሚዛመዱ ታሪኮች በሁለት ምዕራፎች ላይ ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። እንደዚሁም በነህምያ ጸሎት ውስጥ በዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ ኡር ስለተባለ ስፍራ መጠቀሱን እንመለከታለን። ከኡር ምድር እግዚአብሔር አብርሐምን እንዲወጣ አዘዘው። አብርሐምም ከሌሎች ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ የሚኖሩት ሕዝቦች አማልዕክት በመራቅ የእግዚአብሔርን ጥሪ እና ትዕዛዝ አክብሮ ተገኘ። በጣሊያን ውስጥ በቬሮና ከተማ በሚገኘው የሃይማኖት እና ሳይንስ ጥናት ተቋም፣ የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር-እህት ፓፖላ እንደሚናገሩት፣ በኡር ይኖሩ የነበሩት ከለዳዊያን በብልይ ኪዳን በመጠቀሱ ከመንፈሳዊ ታሪክነት ሌላ ታሪካዊ ገጽታን ማግኘት አይቻልም ብለው፣ ከክርስቶስ ልደት 900 ዓመት በፊት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ከለዳዊያን ስለመሆናቸው በመጽሐፍ ብቻ ተጠቅሶ እናገኛለን ብለዋል።

የኡር ስነ-መለኮታዊ ትርጉሙ

የእምነታችን አባት የሆነው አብርሐም ከኡር ተነስቶ ወደ ከነዓን መሄዱን፣ በከነዓን ምድር ከቆየ በኋላ ከከነዓን ተነስቶ ወደ ሌላ ሥፍራ ይጓዝ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በዚህ ሁኔታ በዘመናችን ስለ አብርሐም ታሪክ ሲነገር፣ ከሁሉ አስቀድሞ ከድነታችን ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያብራራ እና እግዚአብሔር በአብርሐም በኩል ከለዳዊያንን ከሚደርስባቸው መከራ ማዳኑ በዘመኑ የእስራኤል ሕዝብንም ለማዳን ላደረገውን ጥረት ስነ-መለኮታዊ ትርጉም መስጠት እንደሚቻል፣ በቬሮና ከተማ በሚገኘው የሃይማኖት እና ሳይንስ ጥናት ተቋም፣ የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፓፖላ ተናግረዋል።

03 March 2021, 15:47