ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  

ር.ሊ.ጳ ፍራነችስኮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡበት ስምንተኛ ዓመት ተከበረ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በመጋቢት 04/2013 ዓ.ም. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 266ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡበትን 8ኛ ዓመት አከበሩ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በታኅሳስ 17/1936 ዓ.ም የአርጀንቲና ዋና ከተማ በሆነችው በቦይነስ አይረስ መወለዳቸው የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የ84 ዓመት ባለጸጋ የሆኑ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።

የእዚህ ዘገባ አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ስምንት  ዓመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊ የሆነ ተግባሯን አጠናክራ እንድትቀጥል እና ለሁሉም የሰው ልጆች በቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ደስታ እንድታበስር፣ በማነኛውም የቅዱስ ወንጌል የማብሰር ሂደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ በመፍቀድ ማከናውን እንደ ሚገባው ቅዱስነታቸው አበክረው መናገራቸው እና አሁንም ቤተ ክርስቲያን በእዚሁ መንገድ እንድትቀጥል ማሳሰባቸውን በፍጹም አላቋረጡም።

ቅዱስነታቸው በእነዚህ ስምንት  ዓመታት ውስጥ በላቲን ቋንቋ Lumen fidei  በአማርኛው “የእመንት ብርሃን”  የተሰኘ እና በእምነት ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ ሐዋርያዊ መልእክት እንዲሁም Laudato si በአማርኛው “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በሚል አርእስት የጋራ የመኖሪያ ቤታችንን የመንከባከብ ኃላፊነት ሁላችንም እንዳለብን በማስመልከት የጻፉት ደግሞ ሁለተኛው ሐዋርያዊ መልእክታቸው እንደሆነ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእነዚህ ስምንት  የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ሦስት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህም በላቲን ቋንቋ Evangelii gaudium”  በአማርኛ ሲተረጎም “በወንጌል የሚገኝ ደስታ”  በሚል አርእስት እ.አ.አ በኅዳር 24/2013 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በእዚህም ቃለ ምዕዳን ቤተ ክርስቲያን በጉዞ ላይ መሆን እንዳለባት እና ቤተ ክርስቲያን ሐዋሪያዊ ተልዕኮዋን ለማከናወን እና ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር ለመመለስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ሕዝቡ መሄድ እንዳለባት የሚያሳስብ ቃለ ምዕዳን ነው።

በሁለተኛነት ደግሞ አሁንም በላቲን ቋንቋ Amoris Laetitia”  በአማርኛው “የፍቅር ሐሴት” በሚል አርእስት እ.አ.አ. በመጋቢት 19/2016 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ በቤተሰብ ውስጥ ስለሚታዩ ተግዳሮቶች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተሰብ ማድረግ ሰለሚጠበቅባቸው ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያወሳ ድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል። በእዚህ ቃለ ምዕዳን በተለይም የኃይማኖት አባቶች በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መልኩ፣ በጥንቃቄ በመመርመር በቤተሰብ ውስጥ የሚያግጥሙ ችግሮችን በችኮላ ከማውገዝ ይልቅ በእግዚአብሔር ምሕረታዊ ጸጋ በመታገዝ የመፍትሄ ሐሳቦችን መጠቆም እንደ ሚገባቸው እና ይህንንም ክህሎት ቀሳውስት ማዳበር እንዲችሉ ቤተሰብን የተመለከተ ትምህርቶች ከዘረዐ ክህነት ጀምሮ መስጠት አስፍላጊ መሆኑን የሚገልጽ ቃለ ምዕዳን ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእነዚህ ስምንት  የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እ.አ.አ በመጋቢት 19/2018 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ “Gaudete et Esultate” በአማርኛው “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” በሚል አርእስት ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን “በአሁኑ ዓለማችን ውስት የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ቅድስና መንገድ እንዲመለሱ የሚጋብዝ ጥሪ” የተካተተበት መልእክት ሲሆን በአሁኑ ዘመን በሚገኘው ዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን፣ የተለያዩ የሕይወት ተግዳሮቶች እየገጠሙዋችሁ የምትገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም አሁን ባለው ዓለማችን ውስጥ ያለውን መልካም እድል መጠቀም ያልቻላችሁ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ልጆቻችሁን በታላቅ ፍቅር ተንከባክባችሁ እያስደጋችሁ የምትገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለቤተሰባችሁ የሚሆን እንጀራ በዕየለቱ ለማግኘት የምትኳትኑ፣ የምትለፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ የምትሠሩ የማኅበረስብ ክፍሎች፣ በእድሜያችሁ ዘመኑ ሁሉ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰባችሁ ለአገራችሁ፣ በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ መልካም የሆነ ተግባር ያከናወናችሁ አረጋዊያን ሁላችሁ “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ነው። ይህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ቃለ ምዕዳን ሲሆን በምዕራፍ አንድ በአሁን ወቅት ባለው ዘመናዊ ዓለማችን ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች እግዚኣብሔር ለእነርሱ ስላቀረበው የቅድስና ጥሪ ያመለክታል። በምዕራፍ ሁለት ላይ ደግሞ ሁለት ቀንደኛ የቅድስና ጠላቶች የሚላቸውን ያትታል። በምዕራፍ ሦስት  በጌታ ብርሃን እይታ በሚል አርእስት ሰፊ ትንታኔ ተቀምጡዋል፣ በምዕራፍ አራት ላይ ደግሞ በዛሬው ዓለማችን ውስጥ የሚታዩ የቅድስና ምልክቶች የሚል አርእስት የተሰጠው ሲሆን በአምስተኛው እና በመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ መንፈሳዊ ውጊያ ማድረግ፣ ነቅቶ መጠበቅ እና በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ውሳኔ ማድረግ በሚል አርእስት ስፊ ትንታኔ ይዞ ቀርቡዋል። በአጠቃላይ ይህ “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” በሚል አርእስት ቅዱስነታቸው ለንባብ ያቀረቡት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይቅርታ፣ እባክህን እና አመሰግናለሁ የሚሉትን ሦስት በጣም ቀለል ያሉ ቃላትን በዕለታዊ ኑሮዋችን ውስጥ በመጠቀም ወደ ቅድስና የሚወስደውን መንገድ መጀመር እንደ ሚቻል በሰፊው የሚተነትን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ነው።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ ስምንት  የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው 27 የሚሆኑ በላቲን ቋንቋ “Motu proprio” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደራሴ በመሆኑ፣ በእዚህ በተሰጠው መንፈሳዊ ስልጣን በራሱ ተነሳሽነት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚጽፋቸው ሰነዶች፣ የሚያደርጋቸው ሹመቶች፣ ውሳኔዎች የተመለከቱ ጉዳዮችን ያመለክታል) በእዚህም መሠረት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ግላዊ ተነሳሽነት 27 መልእክቶች መጻፋቸው ይታወቃል። እነዚህ በእርሳቸው የግል ተነሳሽነት የተጻፉ 27 መልእክቶች ወይም በላቲን ቋንቋ  “motu proprio” ሞቱ ፕሮፕሪዮ መልእክታቸው “የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪዎች መማክርት ጥልቅ የሆነ ታሀድሶ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ መልእክቶች፣ በቅድስት መንበር ውስጥ በተለይም ደግሞ በፋይናንስ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያሳስቡ መልእክቶች፣ በአንድ ባል እና በአንድ ሚስት መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት ለመፍታት እንደ ሚቻል--ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥን የተመለከተ መልእክት፣ ለስርዓተ አምልኮ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ መንፈሳዊ መጽሐፍት በእየአንዳንዱ ሀገር ብጹዕን ጳጳሳት እውቅና አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚመጣጠን መልኩ ውጤታማ እንዲሆኑ ክለሳ እንዲደረግባቸው የሚጠይቅ መልእክት፣ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ አርእስቶችን ያቀፉ 27 ሞቱ ፕሮፕሪዮ በራሳቸው ተነሳሽነት በጣም ተጨባጭ እና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችን በማንሳት ለመፍትሄ ማቅረባቸው ያታወቃል።

ቅዱስነታቸው በእነዚህ ስምንት  የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ ቤተሰብን በተመለከተ ሁለት ጳጳሳዊ ሲኖዶሶች እንዲደረጉ ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በዚህም ወቅታዊ በሆነ መልኩ በቤተሰብ መካከል አሁን የሚታዩ ተግዳሮቶችን በማንሳት እና ትኩረት በመስጠት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በቤተሰብ ጉዳይ እንዲመክሩ በማድረግ ወቅታዊ ለሆኑ ችግሮች ወቅታዊ የሆነ ምላሽ በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚሰጥበትን የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀይስ በር መክፈታቸው ይታወሳል።

ከታኅሳስ 01/2008 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 11/2009 ዓ.ም. ድረስ ለ349 ቀናት ያህል የቆየው ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ኢዩቤልዩ ማወጃቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንን ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት በወቅቱ በክርስቲያኖች እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በተነሳው እርስ በእርስ ግጭት ተጎሳቁላ በነበረች ሀገር በመገኘት የሁለቱንም የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በአንድነት ፊት ለፊት አቀራርበው በማናጋገር እርቅ እንዲፈጥሩ መንገዱን በመክፈት በእዚያው በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብልክ በባንጉዊ ከተማ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል ተገኝተው ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ኢዩቤሊዪን ማስጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም 349 ቀናት ውስጥ ምዕመናን  መንፈሳዊ እና አካላዊ የምሕረት ተግባራት የሚፈጸሙበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፣ በእዚህ ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ክርስቲያኖች እርቅን እና ሰላምን ይፈጥሩ ዘንድ ማሳሰባቸው ይታወቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስምንት  ዓመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ከጣሊያን ውጭ 33 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በአፍሪካ አህጉር የሚገኙትን ኬኒያን፣ ዑጋንዳን እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ አንስቶ በኩባ በአሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ በምስራቅ አውሮፓ እና በኤሺያ አህጉር፣ በመካከለኛው አሜሪካ እና በተባበሩት የአረብ ሔምሬትስ ዋና ከተማ የሆነችውን አቡዳቢ፣ ኢራቅ ድረስ በመጓዝ የሰላም እና የአንድነት መልእክት ማስተላለፋቸው የሚታወቅ ሲሆን 900 የካቶሊክ ምዕመናን የሚገኙባትን አዛረበጃንን ጨምሮ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የእስልምና እምነት ተከታይ ወደ ሆኑባቸው ባንግላዲሽ እና የቡዳ እምነት ተከታይ ወደ ሚበዛባት ማያን ማር (የቀድሞ ስሟ በርማ) ድረስ በመሄድ፣ በቅርቡ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው አቡዳቢ በመሄድ የሰለም እና የአንድነት መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል። በጣሊያን ውስጥ ብቻ 17 ጣሊያን ግዛቶችን በተለይም ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ ለምሳሌም በርዕደ መሬት አደጋ ጉዳት የደረሱባቸውን እና ከአፍሪካ እና ከተለያዩ አገራት የተውጣቱ ስደተኞች ወደ አውሮፓ አህጉር መግቢያ በር አድርገው የሚጠቀሙበትን የላፓዱዛ ደሴትን ጭምር በመጎብኘት ለስደተኞች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር ለዓለም ድምጻቸውን ማሰማታቸው እና ዓለም ለስደተኞች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን ስደተኞችም በበኩላቸው በእንግድነት የሚቀበሉዋቸውን ሀገሮች ማሕበራዊ ሕግጋቶችን በማክበር እንዲኖሩ፣ በእንግድነት የተቀበላቸውን ማኅበረሰብ ወግ እና ባሕል እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ መስጠታቸውም ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእነዚህ ስምንት  የርዕሳነ ሊቃነ ጵጵስና አገልግሎታቸው ዘወትር ረቡዕ ዕለት ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ 10 ልዩ ልዩ አርእስቶችን በስፋት በመዳሰስ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማደረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በእነዚህ የጠቅላላ የትምህረተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የእመታችን መገለጫ ከሆነው የጸሎተ ኃይማኖት አንስተው ሰባቱን የቤተክርስቲያን ምስጢራት፣ የመንፍስ ቅዱስ ስጦታዎችን የተመለከቱ፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ቤተሰብን፣ ምሕረትን፣ የክርስቲያን ተስፋን እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ዙሪያ እና በቅርቡ “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ በተከታታይ እያደረጉት በሚገኘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ጉዞ በመንፈሳዊነት እንዲጓዙ የሚያበረታቱ አስተምህሮዎችን ማደርጋቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በስምንት  ዓመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤተ ባሳረጉዋቸው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከ650 በላይ ስብከቶችን ማደርጋቸው የሚታወስ ሲሆን የስብከታቸው አጠቃላይ ይዘት በእለቱ በሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ ባተኮረ መልኩ “ክርስትያኖች በሕይወት ጉዞዋቸው የሚያጋጥማቸውን ችግሮች መጋፈጥ እንጂ መሸሽ የለባቸውም” የሚል አጠቃላይ እንድምታ ያላቸው ስብከቶች እንደ ሆኑ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ at pontefix በተሰኘው የቲውተር ገጻቸው ላይ በእየ እለቱ በሚያስተላልፉት ምልእክት በዓለም ዙሪያ 46 ሚልዮን በላይ ተከታይ እንዳላቸው የሚያሳይ ሲሆን በተጨማሪም Instagram በተሰኘው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ 5 ሚልዮን ተከታዮች እንዳላቸው ይታወቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ተተኪ በመሆን የዛሬ ስምንት  አመት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 266ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው መመረጣቸው የሚታወቅ ሲሆን በትውልድ አርጄንቲናዊ የሆኑ የ83 አመት እድሜ ባለጸጋ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ምዕረጋቸውን ከመቀበላቸው በፊት የነበራቸውን ካርዲናል በርጎሊዮ የሚለውን የመጠሪያ ስማቸውን በመቀየር በ13ኛ ክፍለ ዘመን የኖረውን እና “የድሆች አባት” በመባል የሚታወቀውን የአዚዚውን የቅዱስ ፍራንቸስኮ ፈለግ ለመከተል በማሰብ የእርሱን የመጠሪያ ስም የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስናቸው ዘመን መጠሪያ እንዲሆን መምረጣቸው የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መስረት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም በሯን ክፍት ያደርገች፣ ለሁሉም የሰው ልጆች በቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ደስታ ማወጅ እና ማብሰር እንደ ሚገባት ምኞታቸው መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸው ይታወቃል።

“ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም የሰው ልጆች ማስተናገድ የሚትችል የሰው ልጆችን እንደ ሕይወታቸው ፈተና እና ድካም ቦታ ልትሰጣቸው የምትችል ቤተ ክርስቲያን እንደ ሚመኙ መግለጻቸው የሚታወቅ ሲሆን በጠቃላይ  ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም የሰው ልጆች ተደራሽ መሆን ይገባታል፣ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የሕይወት ጫናዎች ምክንያት ከቆሰሉ ሰዎች ጋር በመሆን የፈውስ ሂደት አካል ልትሆን ይገባታል የሚል ጽኑ አቋም እንደ ሚያንጸባርቁ ያታወቃል። “አንድ በምቾት ውስጥ ያለች ቤተ ክርስቲያን በራሷ ምቾት ብቻ ራሱና ቆልፋ የምትኖር ከሆነ ያቺ ቤተ ክርስቲያን ጤናማ ቤተ ክርስቲያን ልትባል አትችልም” በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህንን የመሳሰሉ አሉታዊ ባሕርይ ያልቸው አብያተ ክርስቲያናት ይህንን አፍራሽ የሆነ ባሕሪይ በማስወገድ ሰውን ከእግዚኣብሔር ለማገናኘት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመወጣት በእምነት የሚገኘውን ውበት እና ደስታ ለሰው ዘር በሙሉ ማሳየት እንደ ሚኖርባት ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ Evangelii gaudium  በአማሪኛ ሲተረጎም “በወንጌል የሚገኝ ደስታ”በሚል አትእስት በጻፉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በእዚህም ቃለ ምዕዳን ቤተ ክርስቲያን በጉዞ ላይ መሆን እንዳለባት እና ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለማከናወን እና ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር ለመመለስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ሕዝቡ መሄድ እንዳለባት የሚያሳስብ ቃለ ምዕዳን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን ቤተ ክርስቲያንን መንፈስ ቅዱስ እንድያስገርማት  መፈቅድ ይገባታል የሚል ጭብጥ ያዘለ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በቀጣይንት ድምጹዋን እንድታሰማ እና አዳዲስ ነገር በቤተ ክርስቲያን እንዲከሰት የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን እንድያንቀሳቅስ ልንፈቅድለት ይገባል የሚል አጠቃላይ የሆነ ምልእክት የያዘ ቃለ ምዕዳን ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእዚህ በስምንት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው በዋነኛነት እና በማዕከላዊነት “ምሕረት” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ መጠቀማቸው የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መሰረት “የሰማይ አባታችሁ መሐሪ እንደ ሆነ እናንተም ምሕረት አድራጊዎች ሁኑ” የሚለው የክርስቲያኖች የእለት ተእለት መፈክር ሊሆን ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ማስታወሳቸው ይታወሳል። ሁላችንም የመጨረሻ ቀን ፍርድ እንደ ሚጠብቀን በመጨረሻው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመለአክቱ ጋር በዙፋኑ ላይ ቁጭ ብሎ በጎቹን ከፊየሎቹ በመለየት በማቴዎስ ወንጌል 25 እንደ ተጠቀሰው “ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ ታርዤ አልብሳችሁኛል፣ እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል. . .” ወዘተ በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያቀርብልን ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ከአሁኑ መዘጋጀት ይኖርብናል በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በመጨረሻው ሰዓተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ፍርድ አሁን በሕይወት እያለን በምናከናውነው የምሕረት ወይም የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ በተመሰረተ መልኩ በመሆኑ ከአሁኑ በጎ ተግባራርትን ማከናወን ይኖርብናል በማለት መናገራቸውም ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእነዚህ ስምንት  አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው በቤተክርስቲያን የቀሳውስት ብቻ ሳትሆን መላው ምዕመን በተገቢው መልኩ ይሳተፍ ዘንድ መፍቀድ እንደ ሚገባ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው የሚታወቅ ሲሆን ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና በሚገባ እንዲወጡ ማስቻል ያስፈልጋል፣ በማነኛውም የቤተ ክርስቲያን ውሳኔዎች ውስጥ ምዕመናን በትኩረት እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል የሚል ጽኑ አቋም እንዳላቸው ይታወቃል። በተለይም ደግሞ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጾ ስላላቸው ይህንን አዎንታዊ የሆነ ሚና እንዲጫወቱ መፍቀድ ያስፈልጋል በማለት በተደጋጋሚ የተናገሩት ቅዱስነታቸው በእዚህ ረገድ ማርያም ከኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት በላይ እንደ ነበረች በማንሳት ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን ሊያበረክቱት የሚችሉትን ከፍተኛ አስተዋጾ ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ መገለጻቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእነዚሁ ስምንት አመታት የጵጵስናቸው ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን በማብሰር ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጾ መጫወት እንደ ሚገባቸው በመገለጽ ክርስቲያኖች በመንፍስ ቅዱስ በመሞላት ቅዱስ ወንጌልን “በድፍረት፣ ጮክ ብሎ እና በማነኛውም ጊዜ እና ቦታ ለማወጅ መዘጋጀት ይገባቸዋል ማለታቸውም የሚታወስ ሲሆን “በተለይም ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በስቃይ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ተጨባጭ በሆነ መልኩ በማገዝ፣ ተስፋ እንዳይቆርጡ በማድረግ ተስፋቸው እንዲለመልም የሚያደርጉ የምሕረት ተግባራትን ማከናወን ይገባል በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም ደረስ 33ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢራቅ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው በጦርነት የተጎሳቆለችውን አገር እና ሕዝብ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

13 March 2021, 11:55