ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ውይይት እና ተስፋን የሚጨምር መሆኑ ተገለጸ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዚህ ታሪካዊ ጉብኝታቸው ወቅት በእስልምና ሐይማኖት ከሺአ እምነት መሪ ከሆኑት ታላቁ አያቶላ ሰይድ አሊ አል ሁሴን አል ሲስታኒ ጋር የግል ውይይት ማድረጋቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ አስታውሰዋል። በአብርም የትውልድ አገር ኡር ከሦስቱ ሐይምኖቶች፥ ከአይሁድ፣ ክርስትን እና እስልምና እምነቶች ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ያስታወሱት የእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ረዳት ዋና ጸሐፊ እና በጳጳሳቱ ጉባኤ የክርስቲያኖች አንድነት እና የሐይማኖቶች የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ቅዱስነታቸው በኢራቅ ከተለያዩ የሐይማኖት ተወካዮች ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ውይይቶቹ ከመንፈሳዊ እሴትነት በተጨማሪ ትልቅ ምሳሌያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።  

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ በማከልም፣ ርዕሠሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያገኟቸው የሐይማኖት ተወካዮች፣ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለጋራ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን የሚያምኑበት እና የሚመርጡት መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለኢራቅ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በሰላም እና በወንድማማችነት ፍቅር አብረው ለመኖር ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ አስረድተው፣ በሐይማኖቶች መካከል ለሚደረግ የጋራ ውይይት ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። 

የክርስቲያን ማህበረሰብ

በኢራቅ ውስጥ ለዓመታት የዘለቀው ጦርነት እና አመጽ በዚያች አገር ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ቁጥርን ከሃያ ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ1.5 ሚሊዮን ወደ 300,000 ድረስ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን አስታውሰዋል። በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት መልዕክቶች ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሙሉ እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተስፋ ምልክት

አራት ቀናትን የፈጀ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ጠንካራ ትዝታዎችን መፍጠሩን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርድ፣ በተለይም በሞሱል ተገኝተው ከፍተኛ ውድመት በደረሱባቸው ቤተ ክርስቲያናት ዘንድ ሄደው ያቀረቡት ጸሎት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ አገራቸው በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት ወደዚህ ደረጃ መድረሷን ማየታቸው ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ተስፋ የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናርድ አክለውም፣ ጦርነት እና አምጽ ያስከተሏቸው ጥፋቶች ረጅም ጊዜ የሚቆዩ እንደሆነ ገልጸው ውጤታቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚታዩ ናቸው ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ኢራቅ የተጓዙት በችግር ወቅት መሆኑ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርድ፣ ከችግሮቹ መካከል የጸጥታ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ይገኝባቸዋል ብለዋል። ያም ሆኖ ቅዱስነታቸው በኢራቅ ውስጥ ለሚገኙት ክርስትያን ማኅበረሰብ አንድነትን መግለጽ እንደ ቀዳሚ ርዕሠ ጉዳይ መመልከታቸው አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው ወደ ኢራቅ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በዚያች አገር የሚገኘውን የእምነት ታሪክ እንዲታወስ ማድረጋቸውን፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ አስታውሰዋል።        

09 March 2021, 15:55