ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ ወቅት ሕጻናትን ሲባርኩ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ ወቅት ሕጻናትን ሲባርኩ 

በማኅበራዊ ርቀት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሕዝብ አለኝታ መሆናቸው ተነገረ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን በተዛመተበት የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማቋረጥ ጥቂት የሚባሉ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ብቻ በማቅረብ፣ ነገር ግን ቫቲካን ውስጥ ከሚገኝ ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ሆነው ከበርካታ ክርስቲያን ምዕመና እና ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት መገናኘት መቻላቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከዚህ በፊት በዓለማችን የተለያዩ አገሮች በመሄድ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መሰረዛቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአውሮፓዊያኑ የበጋ ወራት በተከሰተው ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በየሳምንቱ የሚያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸዋንም በቁጥር ጥቂት ምዕመናን ብቻ የተከታተሏቸው መሆኑ ይታወሳል። ይህም የእርሳቸውን ሐዋርያዊ አስተምህሮ ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የሚገኙ ምዕመናን እና የአገር ጎብኝዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው እና ተቃቀፈው የሚገልጹት ደስታ እና በአደባባዩ ላይ የሚያደርጉት መንፈሳዊ ስብሰባ እንይዳታይ አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያዊ አስተምህሮአቸውን ከማጠቃለላቸው አስቀድመው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና አገር ጎብኝዎች የሚሰጡት ሐዋርያዊ ቡራኬም ጭምር ተቋርጦ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ቅዱስነታቸው በማኅበራዊ ሚዲያዎች በመታገዝ ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን እና የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን በመላው ዓለም ለሚገኙ ምዕመናን በቀጥታ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ይፋ ባደረገው “ኬሪዳ አማዞኒያ” ወይም “ውድ አማዞኒያ” በሚል ሰነድ ላይ ያስተነተኑበት ዓመት እንደነበር ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዚህ አስተንትኖአቸው የአማዞን አካባቢ ሕዝብ በዓለሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ተዘንግቶ በመቆየቱ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስበት እንደቆየ የሚገልጽ ነበር። ሰብዓዊ ስነ-ምሕዳር ለድሃ ማኅበረሰብ ሕይወት እና ለባሕላቸው ትኩረትን የሚሰጥ፣ ቤተ ክርስቲያን በአማዞን አካባቢ አገሮች የምታበረክተውን የሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎቶችዋን አሳድጋ እንድታበረክት የሚያግዛት ነበር። ቀጥሎም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለይ በጣሊያን ውስጥ የቀነሰ መስሎ በታየበት ወቅት ቅዱስነታቸው ለምዕመናን ማቅረብ በጀመሩት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ከኮቪድ-19 በኋላ ሊኖር ስለሚጋባ መቀራረብ አስመልክተው “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል አርዕስት አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። የዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ዋና ዓላማ፣ ዓለማች የተጨነቀው በኮቪ-19 ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች መካከል የሚከሰተው ጦርነት፣ ፍትህ ማጣት፣ ድህነት፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ ጥላቻ፣ አመጽ እና የብቸኝነት ስሜት ተወግዶ ወንድማማችነት እና ማኅበራዊ ወዳጅነት እንዲያድግ ለማድረግ ያለመ ነበር።

ያለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. በእያንዳንዳችን ልብ ጥሎብን የሄደው ነገር ቢኖር፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እ. አ. አ. መጋቢት 27/2020 ዓ. ም. የሰውን ልጅ እያጠቃ የሚገኝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከዓለማችን እንዲያስወግድልን በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ያቀረቡት ጸሎት ነበር። ቅዱስነታቸው ይህን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ባቀረቡበት ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል። 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እ. አ. አ. በ2020 ዓ. ም. ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በየቀኑ ጠዋት የሚያቀርቡትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፍ የቻሉበት ጠቃሚ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ነበር። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሦስት ወራት ያህል በሮቻችንን በማንኳኳት በተከታታይ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባቀረቡት ስብከት፣ አስገራሚ ንግግሮችን ከማድመጥ ይልቅ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንድናነብ፣ አጫጭር መንፈሳዊ ስብከቶችን እንድናዳምጥ እና የመስዋዕተ ቅዱሴን ጸሎት ከተካፈሉ በኋላ ለአጭር ጊዜ ያህል በቅዱስ ቁርባን ፊት ተንበርክከን ጸሎታችንን እንድናቀርብ መጠየቃቸው ይታወሳል። 

30 March 2021, 16:29