ፈልግ

የር. ሊ. ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ የር. ሊ. ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ 

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ይፋ መሆኑ ተነገረ። ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ናያፍ፣ ኡር፣ ኤርቢል፣ ሞሱል እና ካራኮሽን መጎብኘታቸውን የሐዋርያዊ ጉዞአቸው መርሃ ግብር አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው በጎበኟቸው ክፍላተ ሃገራት ሐዋርያዊ መልዕክቶችን፣ ከምዕመናኑ ጋር በኅብረት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን እና በጦርነት ሕይወታቸውን ያጡትንም በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑ ተገልጿል። “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” የሚል መሪ ቃልን ጨምሮ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አርማም መዘጋጀቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን መጋቢት 26/2013 ዓ. ም. የሚጀምሩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” የሚለውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን መሪ ቃል ይዘው የሚሄዱ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከጣሊያን ፉሚቺኖ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስተው በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ በሚገኘው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊ ሲደርሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስጣናት ተገኝተው ይፋዊ አቀባበል የሚያደርጉላቸው መሆኑ ታውቋል። ቀጥለውም ይፋዊ የእንኳን ደህና መጡ ሥነ-ስርዓት ወደሚካሄድበት ቤተመንግስት የሚያመሩ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከሥነ-ሥርዓቱ በመቀጠል በቤተመንግሥቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የአገሪቱ ፕሬዚደንት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች እና የውጭ አገር ዲፕሎማቶች በተገኙበት ቦታ ደርሰው ንግግር የሚያደርጉ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከኢራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በባግዳድ ከተማ በሚገኝ የድነታችን ምንጭ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ በመገናኘት የመጀመሪያ ቀን ጉብኝታቸውን የሚያጠቃልሉ መሆናቸውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሁለተኛው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ቀን ናያፍን፣ ናሲሪያን እና ኡር ክፍለ ሀገራትን የሚጎበኙ ሲሆን ቅዳሜ መጋቢት 27/2013 ዓ. ም. የደቡባዊ ኢራቅ ክፍለ ሀገር ከተማ እና በሺአ እስልምና እምነት እጅግ ቅዱስ ከሆኑ ቦታዎች አንዱ የሆነውን ናያፍን የሚጎበኙ መሆኑ ታውቋል። ወደዚህ ከተማ ሲደርሱ ታላቁ አያቶላህ ሰይድ አሊ አል-ሁሰሚ አል-ሲስታኒን ከጎበኟቸው በኋላ በኤፍጥራሲ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኝ ናሲሪያ ከተማ ደርሰው ከልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር የሚገናኙ መሆኑ ታውቋል። ከዚህ ጉብኝታቸው በመቀጠል ወደ ባግዳድ ከተማ ተመልሰው በአገሪቱ ከሚገኙ አስራ አንድ ካቴድራሎች መካከል አንዱ በሆነው በቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ መጋቢት 28/2013 ዓ. ም. በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የኢራቅ ኩርዲስታን ግዛት ወደ ሆነው የነነዌ ክፍለ ሃገርን የሚጎበኙ ሲሆን ከኤርቢል አየር ማረፊ ተነስተው የኢራቅ ራስ ገዝ ወደ ሆነው የኢራቅ ኩርዲስታን ክፍለ ሀገር ሲደርሱ በከፍተኛ የእምነትት መሪዎች እና በአካባቢው ሕዝብ ተወካዮች አቀባበል የሚደረግላቸው መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ለዓመታት ያህል በእስላማዊ መንግሥት ሲተዳደር በቆየው ሞሱል ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆሽ አል ቤያ አደባባይ ላይ በመገኘት  ሕይወታቸውን በጦርነት ያጡትን በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ከሞሱል በቅርብ ርቀት ወደምትገኝ እና እ.አ.አ እስከ 2016 ዓ. ም. ድረስ በእስላማዊ መንግስት ስትተዳደር የቆየችውን ካራካሽ ከተማን የሚጎበኟት መሆኑ ታውቋል። ወደዚች ከተማ ከደረሱ በኋላ ወደ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ማርያም ቤተክርስቲያን በመሄድ ለአካባቢው ነዋሪዎች ንግግር ካደረጉ በኋላ ከምዕመናን ጋር በኅብረት የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔርን ጸሎት የሚደግሙ መሆኑ ታውቋል። ከዚህ መልስ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ኤርቢል በመመለስ ከሰዓት በኋላ በከተማዋ በሚገኝ “ፍራንሶ ሃሪሪ” ስታዲዬም የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚያቀርቡ መሆኑ ታውቋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት በኋላ ወደ ባግዳድ ተመልሰው ሰኞ መጋቢት 29/2013 ዓ. ም. ጉዟቸውን ወደ ሮም የሚያደርጉ መሆኑን የኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መሪ ቃል እና አርማ

ከማቴ. ወንጌል የተወሰደው እና “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” የሚለው ጥቅስ ቅዱስነታቸው ወደ ኢራቅ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃል መሆኑ ሲታወቅ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሚገልጽ አርማ ላይ ቅዱስነታቸው ለኢራቅ ሕዝብ ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ የሚያሳይ ምስል ያለበት መሆኑ ታውቋል። የኢራቅ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ በሚታይበት በዚህ ዓርማ ላይ የአገሪቱ ምልክት የሆኑ የዘንባባ እና የሁለቱ ጥንታዊ ወንዞች ማለትም የጤግሮስ እና ኤፍራጥስ ወንዞች ምስል ያለበት መሆኑ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የሰላም ምልክት የሚገልጽ የእርግብ ምስልም በአርማው ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከዚህም ሌላ የሁለቱ አገራት ማለትም የቅድስት መንበር እና የኢራቅ ባንዲራዎች የተቀመጡ መሆኑ ታውቋል።

09 February 2021, 11:22