ፈልግ

የሕንድ ገበሬ ማሳውን ሲቆጣጠር፤ የሕንድ ገበሬ ማሳውን ሲቆጣጠር፤ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጥራጥሬ ሰብሎች ረሃብን ለመቋቋም የሚረዱ መሆናቸውን አስታወቁ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ ሰብሎች ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ በተባበሩት መንግሥታት ለምግብ እና እርሻ ድርጅት ያቀረቡትን መልዕክት፣ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ተቀብለው መላካቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በገጠራማው አካባቢዎች በተለይ ሴቶች በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ከፍተኛ ሚናን የሚጫወቱ መሆናቸውን አስታውሰው እህሎችን አምርተው በማከፋፈል በዕእለማችን የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን እና ረሃብን ለመቋቋም እገዛ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው የካቲት 3/2013 ዓ. ም. የተከበረውን ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ ሰብሎች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች በማኅበር ተደራጅተው አብሮ በመስራት ለሌሎች ያላቸውን ፍቅር ጥጠንክረው በመሥራት የሚያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥራጥሬ ሰብሎች እና ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትናቸው

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ጥራጥሬ ሰብሎች ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስናን በማረጋገጥ የሚጫወቱትን ከፍተኛ ሚናንም ገልጸዋል። የጥራጥሬ እህሎች የምንላቸው እንደ ምስር ፣ ባቄላ ፣ አተር እና ሽምብራ ያሉት በተለያዩ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና ባህሎች ውስጥ እንደ ቀላል እና ገንቢ ምግቦች ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸው ይትስወቃል። በዕለታዊ ቀለቦች መካከል የተለያዩ ሰውነት ገንቢ ንጥረ-ነገሮችን የያዙ በመሆናቸው በበርካታ ቤተሰቦች ውስጥ በገበታ ላይ የሚቀርቡ መሆናቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንደገለጹት እነዚህን የጥራጥሬ እህሎችን ለማምረት በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች መሬታቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ሳይፈልጉ በእጃቸው በመቆፈር በቀላሉ የሚያመርቷቸው መሆኑንም አስታውሰው ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሕጻናትን ጨምሮ በዓለማችን በርካታ ሰዎች መሠረታዊ የሆኑ ምግቦችን በበቂ መጠን የማያገኙ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ረሃብ የጤና ቀውሶችን እያስከተለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሟላ ጤናን ማግኘት ከሰው ልጅ መብቶች አንዱ ነው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን በመቀጠል፣ መሬትን ለጉዳት ሳይዳርጉ በተገቢው መንገድ የእርሻ ሥራን በማካሄድ የምድራችንን ፍሬ ከመጭው ትውልድ ጋር መካፈል የሚቻል መሆኑን አስረድተው፣ በመሆኑም በገጠራማው አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች ለሚያደርጉት የማምረት ጥረት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። እነዚህ ሴቶች በቂ ምግብን ለማምረት የሚያስችሉ አንድነቶች እና የሚከፈሉ መስዋዕትነቶች ብዙ መሆናቸውን እንደሚያስተምሩ እና ፍትሃዊ የሸቀጦች ስርጭት እና የእያንዳንዱን ሰው ፍላጎት እውን ለማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩንም ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ የተሟላ ጤናን ማግኘት ከሰው ልጅ መብቶች አንዱ በመሆኑ መንግሥታት በዚህ ዘርፍ እንዲያስቡበት አሳስበው፣ የትምህርት ፖሊሲዎች በትምህርት ሥርዓቶቻቸው የጥራጥሬ ሰብሎች ከሌሎች የምግብ ዓይነቶች ጋር ተዳምረው የተመጣጠነ ምግብን ለማሟላት የሚያግዙ መሆናቸውን ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለሁሉም በቂ ቦታ ሊኖረው ይገባል

ለልጆቻቸው እና መላው የቤተሰብ አባላት በቂ ምግብን ለማቅረብ የሚፍጨረጨሩትን የገጠር ሴቶች ምሳሌን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ማንም ወደ ጎን ሳይደረግ በጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን ለሁሉም በቂ ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል። ለሁሉም ሰው ጤናማ የምግብ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል ብለው፣ ይህን እኩል ዕድል ለሁሉም በማመቻቸት፣ ፍትሃዊ በሆነ ዓለማችን በጋራ በኖር የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት አስተባባሪነት የሚከበረው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ ሰብሎች ቀን ዋና ዓላማም የጥራጥሬ ሰብሎች የሚሰጡትን የጤና ጥቅሞችን ማኅበረሰቡ እንዲገነዘብ እና ዓለማችንን ረሃብ የሌለበት ለማድረግ መሆኑ ታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ እ.ኤ.አ. በ 2016 ዓ. ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፣ ዓለም አቀፉ የጥራጥሬ ስብል ምርት ስኬት ላይ በመመስረት፣ የካቲት 10 ቀን የዓለም የጥራጥሬ ሰብሎች ቀን ተብሎ እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል።

13 February 2021, 16:14