በያንማር የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በያንማር የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የማይናማር መሪዎች የጋራ ጥቅምን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቅርቡ በማያንማር የተደርገውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በመቃወም ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ከቅርብ ጊዜ አንስቶ በማያንማር ውስጥ እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ክስተቶች ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እሁድ ዕለት ጥር 30/2013 ዓ.ም ለማይናማር ህዝብ አጋርነታቸውን በመግለጽ በአገሪቷ የሚገኙ መሪዎች የጋራ ጥቅምን ለማገልገል ፈቃደኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጥር 30/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን በእለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከደገሙ በኋላ ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት እ.አ.አ. በ 2017 ዓ.ም “በማያንማር ካደረኩት  ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀምሮ የማያንማር ሕዝብ በልቤ ውስጥ በጣም በፍቅር የማስበው ህዝብ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቷ እየተከሰተ የሚገኘው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በስጋት እየተከታተልኩ ነው ብለዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ “ለማያንማር ህዝብ ያለኝን መንፈሳዊ ቅርበት ፣ ጸሎት እና አብሮነት ማረጋገጥ እፈልጋለሁ” ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ “የፖለቲካ ኃላፊነት የጋራ ጥቅምን ለማገልገል ፣ ማህበራዊ ፍትህን እና ብሄራዊ መረጋጋትን በማስፋፋት ቅን የሆነ ፈቃደኝነት እንዲያሳዩ እጸልያለሁ” በማለት ታማኝ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ አብሮ የመኖር ፍላጎትን እንዲያሳዩ ለመላው የአገሪቷ ሕዝብ ጸሎት እንደ ሚያደርጉ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

በአመታት ውስጥ የተካሄደ ትላልቆቹ ተቃውሞች

ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.አ.አ. ከ 2007 ዓ.ም የሣፍሮን አብዮት በመባል ከሚታወቀው የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ ወደ ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ማሻሻያዎች እንዲመራ የረዳው ትልቁ የተቃውሞ ሰልፍ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን መፈንቅለ-መንግስት ለማውገዝ እና በዲሞክራሳዊ መንገድ የተመረጡት መሪ አውን ሳን ሱ ኪይ ከእስር እንዲለቀቁ እሁድ እለት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማያንማር ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

በሰፊው እየተቀጣጠለ በሚገኘው በእዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ሁለተኛ ቀን በታላቋ ከተማ ያንጎን ትላንት ጥር 30/2013 ዓ.ም መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን ከሰዓት በኋላ ላይ ወታደራዊው ጁንታ ባለፈው ሰኞ ካካሄደው መፈንቅለ መንግስት ወዲህ ሕዝቡ ንዴቱ ገንፍሎ በመውጣቱ የተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድርግ ወደ አደባባዮች እየወጣ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ወታደራዊው መንግስት በበኩሉ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎችን በመዝጋት እና የእንተርኔት አገልግሎቶችን በማቋረጥ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማገድ እየጣረ እንደ ሆነም ከስፍራው የሚወጡ ዜናዎች ያስረዳሉ።

የታጠቁ አድማ በታኝ ፖሊሶች መንገዶችን ቢዘጉም ሰላማዊ ሰልፉን ለማስቆም አለመሞከራቸው ግን የተገለጸ ሲሆን አንዳንድ ሰልፈኞች የሰላም ምልክት አድርገው ለአድማ በታኝ ፖሊሶች አበባ ማቅረባቸው ተገልጻል።

መፈንቅለ መንግስቱ የተካሄደው በጦር ኃይሉ አዛዥ ሚን አንግ ህላንግ ሲሆን እ.ኤ.አ. በሕዳር ወር በአገሪቷ የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ እውነተኛ መሪ እና የዴሞክራሲ ምልክት በሆኑት የሳን ሱ ኪ ፓርቲ ከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ የሚታወቅ ሲሆን ምርጫው ከፍተኛ ማጭበርበር ተደርጎበታል በማለት የወታደራዊው ክንፍ በወቅቱ የምርጫውን ውጤት አንደ ማይቀበል መግለጹ ይታወሳል፣ የምርጫ ኮሚሽኑ በበኩሉ ይህንን ክስ ወድቅ ማደረጉ ይታወሳል።

ወታደራዊው ክንፍ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ ከ160 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።

07 February 2021, 10:53