የጥር 02/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘልደት ቅዱስ ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጥር 02/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘልደት ቅዱስ ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የጥር 02/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘልደት ቅዱስ ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና”!

የእለቱ ምንባባት

1.      ሮሜ 11፡25-36

2.    1 ዮሐንስ 4፡1-8

3.    የሐዋርያት ሥራ 7፡17-22

4.    ማቴዎስ 2፡ 1-12

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የጠቢባን ከምሥራቅ መምጣት

በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ። ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች። እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተ ልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፎአልና አሉ፤ “ ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተ ልሔም፣ ከሌሎቹ የይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፤ የሕዝቤ የእስራኤል ጠባቂ የሚሆን፣

ከአንቺ ይወጣልና።’ ”

ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው። ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጒዞአቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ (ማቴዎስ 2፡1-12)።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሄር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ!

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አስተሪዮ ወይም ሕጻኑ ኢየሱስ ለሰብአሰገል የተገለጸበት የመታሰቢያ በዓል ቀን ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማቴዎስ 2:1-12) ኢየሱስ ወደ ዓለም በመጣበት ወቅት የተደርገለትን አቀባበል እና ለዓለም ራሱን የገለጠበት ሦስት ባሕሪያትን ለእኛ ያቀርብልናል። እነዚህም በደስታ ተሞልቶ መፈለግ፣ ቸልተኝነት እና ፍርሃት የተሰኙት ባሕሪያት ናቸው።

ሰብአሰገል መሲሁን  በደስታ መፈለግ አልታከቱም ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ” (ማቴ 2:2)። በጣም ረጅም የሚባል ጉዞ አድርገዋል። አሁን ደግሞ በታላቅ ጉጉት አዲስ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የተኛበትን ሥፍራ ትክክለኛ ቦታ ለማወቅ በጉጉት ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። ይህንንም  ሥፍራ በትክክል እንዲነግሯቸው በማሰብ ወደ ንጉሥ ሄሮደስ ዘንድ ሄደው ይጠይቁታል። እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 

ይህ በደስታ የተሞላ የሰብአሰግል ፍለጋ የካህናት አለቆችንና የአይሁድ የሃይማኖት መምህራን ከነበራቸው የግዲየለሽነት ባሐሪ ጋር ይቃረናል። እነርሱም በነብያት የተጻፉትን መጽሐፍት በሚገባ ያወቁ ስለነበረ ኢየሱስ የተወለደበት ትክክለኛ ሥፍራ የማወቅ አቅም ነበራቸው። በእዚህም ምክንያት እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፎአልና አሉ” (2፡5)፣ ይሁን እንጂ ወደ እዚያ ሥፍራ ለመሄድ አልተመቻቸውም ነበር። ቤተልሔም እነርሱ ከነበሩበት ሥፍራ በጣም ጥቂት ኪሎሜትሮች ርቃ የምትገኝ ሥፍራ ብትሆንም ቅሉ እነርሱ ግን መነቃነቅ አልፈለጉም።

ከእዚህም የከፋው ደግሞ የሄሮድስ ባሕሪ ነው። እርሱ ይባስ ብሎ ይህ የተወለደው ሕጻን ስልጣኑን የሚንጥቅበት መስሎት ስለተሰማው በጣም ደንግጦ ነበር። ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። ጠቢባኑንም ወደ ቤተልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው (ማቴዎስ 2:7,8)። በእርግጥ ሄሮድስ ሕጻኑ የተወለደበትን ሥፍራ ማወቅ የፈለገው ለሕጻኑ ለመስገድ ፈልጎ ሳይሆን፣ ነገር ግን ባላንጣ አድርጎ ስለቆጠረው ሊገለው ፈልጎ ነበር እንጂ።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማቴዎስ 2፡1-12) በደስታ መፈለግ፣ ችልተኝነት እና ፍርሃት የተሰኙ ሦስት ባሕሪያት ተጠቅሰዋል። እኛም ከእነዚህ ከሦስቱ ባሕሪያት መካከል የትኛውን መውሰድ እንዳለብን መምረጥ ይኖርብናል።

የራስ ወዳድነት መንፈስ ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ለመኖር መምጣቱ እንደ ማስፈራሪያ አድርገን እንድንቆጥር ይገፋፋን ይሆናል። በዚህም መንፈስ የተነሳ የኢየሱስን መልእክት ላለማዳመጥ ወይም ደግሞ እርሱ የሚነግረንን መልእክት ሰምተን ዝም ለማለት እንሞክራለን። አንድ ሰው ሰብዓዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ለምሳሌም በጣም ምቹ የሆኑ አመለካከቶችን፣ የክፋት ዝንባሌዎችን፣ በሚከተልበት ጊዜ ኢየሱስ እንደ እንቅፋት ሆኖ ይታየዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የቸልተኝነት ፈተና ዘወትር በእኛ ውስጥ ይገኛል። ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን እያወቅን እርሱ አዳኝ እንዳልሆነ አድርገን፣ ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን ብናውቅም እንዳልሆነ አድርገን ለመኖር እንመርጣለን።  ከእኛ የክርስትና እምነት ጋር በጥብቅ  ከመወዳጀት ይልቅ የዓለምን መርሆዎች እንከተላለን፣ ይህም የእብሪተኛነት  ዝንባሌን  የስልጣን እና የሐብት ጥማት እንዲኖረን ያደርጋል።

ይልቁኑም እኛ በደስታ እርሱን መፈለግ እንዳለብን እና አልፊ በሆኑ ሁኔታዎችም ውስጥ ሳይቀር ኢየሱስን ለማግኘት ዝግጁ መሆን እንዳለብን ሰብአሰገል ያሳዩንን አብነት ለመከተል ተጠርተናል።  እሱን ለማምለክ መፈለግ፣ እርሱ ጌታችን መሆኑን እንድናውቅ እና እርሱን ለመከተል የምያስችለንን ትክክለኛውን መንገድ የሚያመለክት እርሱ ብቻ መሆኑን ለማወቅ መሻት ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ኢየሱስ በእውነት እኛን ያድነናል፣ እኛ አስደሳች ሕይወት ልንኖር ይችላል፣ በእምነት በመፈለግ እና በተስፋ በእግዚአብሔርና በወንድሞቻችን ላይ ያለንን ፍቅርን ማሳደግ እንችላለን።

በምድር ላይ ምጽሐተኞች ለሆንን ለእኛ ጨረቃችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን። የእናትነት እገዛዋ ሁሉም ሰዎች እውነተኛ ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን በመከተል ዓለማችን በሰላም እና በፍትህ ጎዳና ላይ ትራመድ ዘንድ በአማላጅነቷ ትረዳን ዘንድ እርሷን ልንማጸናት ይገባል።

09 January 2021, 17:43