ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ ሲያደርጉ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ ሲያደርጉ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሕብረት ግጭቶችን ያሸንፍ ዘንድ እንጸልይ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 12/2013 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በጸሎት ዙርያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ሕብረት ማነኛውንም ዓይነት ግጭቶች ያሸንፍ ዘንድ እንጸልይ ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤እነርሱ የአንተ ስለሆኑ እጸልይላቸዋለሁ […] የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው (ዮሐንስ 17፡1.9. 20 -21)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አስተንድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ውስጥ ለክርስቲያናዊ አንድነት በሚደረገው ጸሎት ላይ ለማተኮር እወዳለሁ። በእውነቱ ከጥር 10 እስከ 25/2013 ዓ.ም ያለው ሳምንት በተለይ ለዚህ ለክርስቲያናዊ አንድነት ለሚደረገው ጸሎት የተተወ ጊዜ ነው፣ በኢየሱስ ውስጥ ባሉ አማኞች መካከል የተፈጠረው አሳፋሪ መለያየትን ለማሸነፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ የአንድነትን ስጦታ ለመጠየቅ ጸሎት የሚደረግበት ወቅት ነው። እርሱም ከመጨረሻው እራት በኋላ የራሱ ለሆኑት ሁሉ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” (ዮሐ. 17 21) በማለት ወደ አባቱ ጸለየ። እሱ ከህማሙ በፊት የጸለየው ጸሎት ነበር ፣ የእርሱ መንፈሳዊ ኑዛዜ ነው ማለት እንችላለን። ሆኖም ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ አንድነት እንዳላዘዘ እናስተውላለን። ፍላጎታቸውን ለማነቃቃት እንኳን ያቀደ ንግግር እንዳላደረገም እንታዘባለን። እንዲህ አላደረገም፣ ይልቁኑ እኛ አንድ እንድንሆን ወደ አብ ጸለየ። ይህ ማለት እኛ በራሳችን ጥንካሬ አንድነትን ለማሳካት በቂ አይደለንም ማለት ነው። አንድነት ከሁሉም በላይ ስጦታ ነው ፣ በጸሎት የሚጠየቅ ጸጋ ነው።

እያንዳንዳችን አንድነት ያስፈልገናል። በእውነቱ እኛ በራሳችን ውስጥ እንኳን አንድነትን የማስጠበቅ አቅም እንደሌለን እንገነዘባለን። ሐዋርያው ​​ጳውሎስም በራሱ ውስጥ ይህንን በተመለከተ የተወዛገበ ግጭት ተሰምቶት ነበር - ጥሩን በመፈለግ እና ወደ ክፋት ማዘንበል (ሮሜ 7፡19)። እርሱ በዙሪያችን ያሉ በሰዎች ፣ በቤተሰቦች ፣ በኅብረተሰብ ፣ በሕዝቦች እና በአማኞች መካከል እንኳ ያሉ የብዙ ክፍፍሎች መነሻ በውስጣችን እንዳለ ተገንዝቧል። ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ “ዓለም ከሚሰቃየው ሚዛን መዛባት በሰው ልብ ውስጥ ከሚሰፍረው ጥልቅ ሚዛን መዛባት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያረጋግጣል። ብዙ አካላት እርስ በርሳቸው መዋጋት የሚጀምሩት በትክክል በሰው ውስጥ ነው። […] ለዚህም እሱ በራሱ ውስጥ መከፋፈልን ይቀበላል ፣ ከዚህ ውስጥም በጣም ብዙ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ከባድ አለመግባባቶች ይነሳሉ ”(Gaudium et spes (ደስታ እና ተስፋ) ቁ. 10)። ስለዚህ የመከፋፈሉ መፍትሔ አንድን ሰው መቃወም አይደለም ፣ ምክንያቱም አለመግባባት የበለጠ አለመግባባት ያስከትላልና። እውነተኛው መድሃኒት የሚጀምረው ሰላምን ፣ እርቅን ፣ አንድነት ከእግዚአብሔር በመጠየቅ ነው።

ይህ ደግሞ በቀዳሚነት ለክርስቲያኖች እውነት የሆነ ነገር ነው፣ አንድነት ሊመጣ የሚችለው በፀሎት ፍሬ ብቻ ነው። የዲፕሎማሲ ጥረቶች እና በምሁራን አማካይነት የሚደረጉ ውይይቶች በቂ አይደሉም። ኢየሱስ ይህንን አውቆ በጸሎት መንገድ ከፍቶልናል። ስለ አንድነት የምናቀርበው ፀሎት በትህትና መደረግ የሚገባው ሲሆን ነገር ግን እምነት የሚጣልበት የጌታ ጸሎት ውስጥ መጠቃለል ይኖርበታል፣ እርሱም በስሙ የሚደረገው እያንዳንዱ ጸሎት በአባቱ እንደሚሰማ (ዮሐ. 15፡7) ማመን ነው። በዚህ ጊዜ "ስለ አንድነት እፀልያለሁ ወይ?" ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፣ የኢየሱስ ፈቃድ ነው፣ ነገር ግን የምንጸልይበትን ዓላማ ከገመገምን ምናልባት ለክርስቲያናዊ አንድነት ብዙም እንዳልፀለይን እንገነዘባለን። ሆኖም በዓለም ውስጥ ያለው እመነት በእሱ ላይ የተመሠረተ ነው። በእውነቱ ጌታ በመካከላችን አንድነት እንዲኖር የጠየቀው “ዓለም እንዲያምን” ነው (ዮሐ. 17፡21)። መልካም የሚባሉ ሙግቶችን በማደረግ ዓለምን ማሳመን አንችልም፣ ነገር ግን እኛን የሚያስተሳስረን እና ወደ ሁሉም ሰው የሚያቀርበንን ፍቅር ከተመለከትን ዓለም አንዲያምን ማደረግ እንችላለን።

በዚህ ወቅት በከባድ ችግር ውስጥ በምንገኝበት በአሁኑ ጊዜ፣ በግጭቶች ላይ አንድነት የበላይ ሆኖ እንዲያሸንፍ ጸሎት ይበልጥ አስፈላጊ ነው። የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ የግል ጉዳዮችን መተው አጣዳፊ ነው፣ እናም በዚህ ምክንያት እኛ የምናሳየው ጥሩ ምሳሌ መሠረታዊ ነው -ክርስቲያኖች ወደ ሙሉ እና ወደሚታይ አንድነት በሚወስደው ጎዳና ላይ መራመድ መቀጠላቸው አስፈላጊ ነው። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ለእግዚአብሄር ምስጋና ይግባውና፣ በእዚህ ረገድ ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚረዱን ብዙ እርምጃዎች ተወስደዋል፣ ነገር ግን ታስፋ ሳንቆርጥ እና ሳንታክት በእምነት፣ በፍቅር እና በጸሎት መጽናት አስፈላጊ ነው። መንፈስ ቅዱስ ያስነሳው እና ወደ ኋላ የማንመለስበት መንገድ ነው።

መጸለይ ማለት ለአንድነት መታገል ማለት ነው። አዎ አንድነትን ለመፍጠር መጣር፣ ምክንያቱም ጠላታችን ዲያብሎስ ራሱ ቃሉ እንደሚለው የሚከፋፍል ስለሆነ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሁል ጊዜ ወደ አንድነት የሚመራ ሲሆን ዲያቢሎስ ግን እርሱ በሁሉም ቦታ እና በሁሉም መንገድ መከፋፈልን ያስባል። ዲያቢሎስ በአጠቃላይ በወንድሞቻችን ድክመቶች ውስጥ በመግባት ነው እንጂ በከፍተኛ ሥነ-መለኮት ትምህርቶች ውስጥ ገብቶ አይፈትነንም። እሱ ተንኮለኛ ነው፣ የሌሎችን ስህተቶች እና ጉድለቶች ያጎላል፣ አለመግባባትን ይዘራል ፣ ትችትን ያስነሳል እንዲሁም አንጃዎችን ይፈጥራል። የእግዚአብሔር መንገድ ግን ከእዚህ የተለየ ነው፣ እርሱ እንዳለን ይቀበለናል፣ አንዳችን ከሌላው የተለየን ኃጢአተኞች አድርጎ ይቆጥረናል ወደ አንድነትም የመራናል። እኛ በምንኖርባቸው አከባቢዎች ውስጥ እግዚአብሔር በሰጠን መሳሪያዎች ማለትም በጸሎት እና በፍቅር አንድነትን ለማሳደግ፣ ግጭቶች እንዲበራከቱ የበኩላችንን ጥረት እንዳደርጋለን ወይስ አንድነት እንዲፈጠር እንታገላለን ብለን ራሳችንን መፈተሽ እንችላለን።

ለዚህ የአንድ ሳምንት ለክርስቲያናዊ ሕብረት ለሚደረገው ጸሎት የተመረጠው መሪ ቃል ጭብጥ በትክክል ፍቅርን ይመለከታል “በፍቅሬ ኑሩ ብዙ ፍሬ ታፈራላችሁ” (ዮሐ. 15፡5-9) የሚለው ነው። የኅብረት መሠረቱ የክርስቶስ ፍቅር ሲሆን ይህም በሌላው ወንድም እና እህት ውስጥ ሁል ጊዜ ፍቅርን እንድንመለከት እና በተቃራኒው ደግሞ ጭፍን ጥላቻን እንድናሸንፍ ያደርገናል። ከዚያ በተለያዩ የክርስትና የእምነት ተቋማት አማኞች ውስጥ ያለውን የእምነት መግለጫዎች፣ ባህሎቻቸው ፣ ታሪካቸው የእግዚአብሔር ስጦታዎች መሆናቸውን ፣ በሀገረ ስብከታችን እና በየቁምስናዎቻችን ውስጥ የሚገኙ ማህበረሰቦች ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ስጦታዎች መሆናቸውን እናስተውላለን። ስለእነሱ መጸለይ እንጀምራለን ፣ ሲቻል ከእነሱ ጋር አብረን መጸለይ እንጀምራለን። ስለዚህ እነሱን መውደድ እና ማድነቅ እንማራለን። ጸሎት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ እንደ ሚያሳስበን የሁሉም የአንድነት እንቅስቃሴ ነፍስ ነው ( Unitatis Redintegraio (ሕብረት እና አንድነት) ቁ. 8) ላይ እንደ ተገለጸው። ይህም “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” በማለት ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት እውን ይሆን ዘንድ ለመርዳት የመነሻ ነጥብ ይሁን!

20 January 2021, 11:24