ፈልግ

Vatican News

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የማይነጥፍ ፍቅር ያለውን እግዚአብሔር ሁሌም ማመስገን ይኖርብናል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት በቫቲካን የተጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 05/2013 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ለእኛ የማይነጥፍ ፍቅር ያለውን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ማመስገን ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጿል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በቫቲካን ያደረጉትን ተጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከእዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረነው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል በዛሬው አስተምህሮዋችን ደግሞ የምስጋና ጽሎትን በተመለከተ ጊዜ ስጥተን እንመለከታለን።

 እንደ መነሻች ነጥብ አድርገን በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ የሆኑ ክፍሎችን እንወስዳለን። የመጀመሪያዎቹ ተዓምራት ከተፈጸሙ እና ደቀ መዛሙርት በእግዚአብሔር መንግሥት አዋጅ ውስጥ ከተሳተፉ በኋላ የመሲሑ ተልእኮ ቀውስ ውስጥ ይገባል። መጥምቁ ዮሐንስ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ?” (ማቴ 11 3) በማለት በጥርጣሬ የተሞላውን ጥያቄ አቀረበለት፣ ኢየሱስ ብዙ አስደናቂ ምልክቶችን ባደረገባቸው በሐይቁ ዳርቻ ዙሪያ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ለእርሱ የጥላቻ መንፈስ ነበራቸው (ማቴ 11፡20-24 ይመልከቱ)። አሁን በትክክል በዚህ አሳዛኝ ወቅት ወንጌላዊው ማቴዎስ በእውነቱ አስገራሚ እውነታውን ይናገራል -ኢየሱስ የተሰማውን ሐዘን ለአብ አልገለጸም ነበር፣ ይልቁንም የደስታ መዝሙር በመዝመር “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ”(ማቴ 11፡25) በማለት የምሥጋና መዝሙር ለአብ ያቀርብለታል። በችግር ጊዜ ኢየሱስ አብን ይባርካል ፣ ያወድሳል። ለምን?

በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ እርሱ “አባት ፣ የሰማይና የምድር ጌታ” በመሆኑ የተነሳ ስለ ማንነቱ ያወድሰዋል። ኢየሱስ በመንፈሱ ይደሰታል፣ ምክንያቱም አባቱ የአለም አምላክ እንደሆነ ያውቃል፣ ይሰማዋልም፣ እናም በተቃራኒው ደግሞ እርስ የሁሉም ጌታ የሆነ “አባት” ነው። “የልዑል ልጅ” እንደሆነ ከሚሰማው ከዚህ ውዳሴ ምስጋና ይወጣል።

እናም ከዚያም ኢየሱስ ለትንንሾቹ ሞገስ ስለሰጠ አብን ያወድሳል። እሱ ራሱ የነበረው ተመክሮ ሲሆን በመንደሮች ውስጥ እየተዘዋወረ ይሰብክ በነበረበት ወቅት የገጠመው ነገር ነው፤ “የተማሩ” እና “ጥበበኞች” የነበሩ ሰዎች ተጠራጣሪ እና ዝግ ሆነው የቀሩ ሰዎች ነበሩ፣ “ትንንሾቹ” እራሳቸውን ከፍተው መልእክቱን በደስታ ይቀበላሉ። ይህ የአብ ፈቃድ ብቻ ሊሆን ይችላል ፣ እናም ኢየሱስ በዚህ ይደሰታል። ትሑቶች እና የዋህ የሆኑ ሰዎች ቅዱስ ወንጌልን ስለሚቀበሉ እኛም መደሰት እና እግዚአብሔርን ማወደስ አለብን። በመጪው ዓለም እና በቤተክርስቲያኗ ተስፋ ውስጥ “ትንንሾቹ” አሉ፣ እራሳቸውን ከሌሎች በላይ አድርገው የማይቆጥሩ፣ የራሳቸውን ገደቦች እና ኃጢአቶቻቸውን የተገነዘቡ ፣ በሌሎች ላይ ጌታ ለመሆን የማይፈልጉ፤ በእግዚአብሔር አባት ሁላችንም ወንድሞች እና እህቶች መሆናችንን የሚቀበሉ ሰዎች አሉ።

ስለዚህ በዚያ ውድቀት በሚታይበት ጊዜ ​​ኢየሱስ አብን በማመስገን ይጸልያል። ደግሞም የእርሱ ጸሎት እኛ የወንጌሉ አንባቢዎች የእግዚአብሔር መገኘት እና ድርጊት በግልጽ በማናይባቸው ሁኔታዎች፣ ክፋት የበዛበት እና ምንም መንገድ የሌለበት በሚመስልበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ለማስቆም በግል ድክመቶቻችን ላይ በግልጽ መፍረድ ይኖርብናል። ኢየሱስ አብን ማብራሪያ ለመጠየቅ በቂ ምክንያት ባገኘበት በዚህ ወቅት በጣም ብዙ ጥያቄዎችን በጸሎት መልክ ማቅረብ የሚችል ቢሆንም ቅሉ ይልቁኑ ኢየሱስ  እሱን ማወደስ ይጀምራል ፡፡

ምስጋና ለማን ያስፈልጋል? ለእኛ ወይስ ለእግዚአብሄር? የቅዱስ ቁርባን ሥርዓተ አምልኮ መጽሐፍ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር እንድንጸልይ ይጋብዘናል-“ምንም እንኳን ምስጋናችን ባያስፈልግህም፣ ምስጋናችን በታላቅነትህ ላይ ምንም ነገር የሚጨምር ባይሆንም እንኳን፣ ምስጋናችን ለእኛ መዳን ይጠቅመናል፣ ምስጋናችን ራሱ የእናንተ ስጦታ ነው” በማለት ይገልጸዋል። የምስጋና ጸሎት እኛን ያገለግለናል። ይህንን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሲገልጽ በዚህ መንገድ ይተረጉመዋል “እርሱን በክብር ከማየታቸው በፊት በእመነት እግዚአብሔርን የሚወዱ ለበ-ንፁሃን በሚጠብቃቸው ደስታ ተካፋይ ነው” (ቁጥር 2639) በማለት ይናገራል። ተቃራኒ በሆነ መንገድ ሕይወት በደስታ ሲሞላን ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ መንገዱ አቀበት በሚሆንበት ጊዜ ሊተገበር ይገባል። ያ ደግሞ የምስጋና ጊዜ ነው። ምክንያቱም በዚያ መወጣጫ በጎረበተበት ወቅት ፣ በዚያ አድካሚ መንገድ ፣ እነዚያ ምንባቦች የሚያሳስቡን፣ አዲስ አድማስ እንድንመለከት እና በእዚህም መልኩ ሰፋ ያለ አድማስ እንደምናገኝ ያስረዱናል።

ስምንት ምዕተ ዓመታትን ባስቆጠረው በዚያ ጸሎት ውስጥ አስፈላጊነቱን ጠብቆ የቆየ አንድ ታላቅ ትምህርት አለ ፣ ይህም ቅዱስ ፍራንቸስኮስ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ያቀናበረው “የወንድም ፀሐይ መዝሙር” ወይም “የፍጥረታት” መዝሙር በሚል አርእስት ያቀረበው ነው።ይህ ምስኪን የሆነ ቅዱስ ይህንን ዝማሬ  ያቀረበው በደስታ፣ በመልካም ሁኔታ ላይ በነበረበት ወቅት ሳይሆን ነገር ግን በተቃራኒው በችግር መካከል በነበረበት ወቅት ያዋቀረው መዝሙር ነው። ቅዱስ ፍራንቸስኮስ በዚያን ጊዜ ዓይነ ስውር ነበር እናም በነፍሱ ውስጥ ከዚህ በፊት አጋጥሞ የማያውቀውን የብቸኝነት ክብደት ተሰማው፣ መስበክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ እርሱ የመጨረሻ ጊዜ ድረስ ዓለም አልተለወጠም ነበር፣ አሁንም በጥል እና በክርክር መንፈስ እየተበታተኑ የሚገኙ ሰዎች እንደ ነበሩ የተረዳ ሲሆን በተጨማሪም ሞት ከመቼው ጊዜ በላይ እጅግ በጣም እየቀረበ መምጣቱን ያውቅ ነበር። የከፋ ብስጭት ውስጥ በመግባት እና  የእራሱ ውድቀት በመገንዘቡ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ቅዱስ ፍራንቸስኮስ በዚያ ቅጽበት “ምስጋና ሁሉ የአንተ ነው ፣ ጌታዬ” በማለት ጸለየ። ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ስለ ሁሉም ነገር ፣ ስለ ፍጥረት ስጦታዎች ሁሉ አልፎ ተርፎም እርሱ በድፍረት “እህት” ብሎ ለመጥራት ብርታቱ ስለነበረው ስለራሱ ሞት በእጠቃላይ ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔርን ያመስግናል። ቅዱሳን ሁል ጊዜም በጥሩም ሆነ በክፉ ጊዜ ውዳሴ መስጠት እንደምንችል ያሳዩናል፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ታማኝ ወዳጅ ስለሆነ ፍቅሩም መቼም ይነጥፍምና።

13 January 2021, 13:26