ፈልግ

በኢራቅ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጣቃት ተፈጸመ በኢራቅ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጣቃት ተፈጸመ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኢራቅ በደረሰው የቦምብ ጥቃቶች ማዘናቸውን ገለጹ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ የ32 ሰዎች ህይወት የቀጠፈ እና ከ 100 በላይ በሚሆኑት ላይ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ባስከተለው መንታ የአጥፍቶ መጥፋት ፍንዳታ ማውገዛቸው የተገለጸ ሲሆን በጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ጸሎት እንደ ሚያደርጉ ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐሙስ ጥር 13/2013 ዓ.ም ዕለት በባግዳድ በአንድ የገበያ ማዕከል ላይ በተፈፀመ መንትያ የቦንብ ጥቃት ያወገዙ ሲሆን ጥቃቶቹንም “እርባና ቢስ የጭካኔ ድርጊት” በማለት አውግዘውታል። በአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቱ ቢያንስ 32 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ 100 በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቫቲካን ወይም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል በቴሌግራም ባስተላለፉት መልእክት “ለሟቾች እና ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለተጎዱ እና በቦታ ላይ ላሉት የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች” መጸለየቸውን ተናግረዋል።

ኢራቅ በ “ወንድማማችነት ፣ አብሮነትና ሰላም” ሁከትን ለማሸነፍ መስራቷን እንደምትቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በኢራቅ እና በሕዝቦቿ ላይ ጌታ በረከትን ያወርድ ዘንድ በጸሎታቸው እንዳሰቡ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ወደ ኢራቅ በመጓዝ ባግዳድ እና ሌሎች አራት ከተሞችን እ.አ.አ ከመጋቢት 5 እስከ 8/2021 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸው ይታወሳል።

በኢራቅ ዋና ከተማ ላይ ያልተለመዱ ጥቃቶች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እስላማዊ መንግሥት እየተባለ የሚጠራው የአሸባሪዎች ቡድን ወታደራዊ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ በመዲናዋ ውስጥ እጥፍቶ የመጥፋት ጥቃቶች ብቅ እያሉ  መጥተዋል ፣ ስለሆነም ይህ ጥቃት አገሪቱን አስደንግጧል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ቦምብ ለማፈንዳት በመሞከር ላይ ሳሉ በማዕከላዊ ባግዳድ ፖሊስ ድጊቱን ለማስቆም በማሰብ እጥፊዎቹን በማሳደድ ላይ በነበረበት ወቅት አጥፍቶ ጠፊዎቹ በሰውነታቸው ላይ የተጠመደውን ቦንብ በማፈንዳት ጥቃቱን ፈጽመዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው ታያራን አደባባይ አቅራቢያ በሚገኘው የልብስ መሸጫ ገበያ ላይ ራሳቸውን ባፈነዱ ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች መሆኑም ተገልጿል።

ብዙ ቁስለኞች በመዲናዋ በሚገኙ ሆስፒታሎች እና ክሊኒኮች ለመውሰድ የህክምና አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ገበያ ማዕከሉ በፍጥነት መድረሳቸውም ተዘግቧል።

የአይሲስ ጥቃት?

እስካሁን ድረስ ይህንን ጥቃት ያከናወንኩት እኔ ነኝ ብሎ ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን ያልተገኘ ሲሆን ነገር ግን እስላማዊ መንግስት እየተባለ የሚጠራው አካል ከእዚህ ግፍ በስተጀርባ ይገኛል ተብሎ ይገመታል። በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው  ሪፖርት ከ 10,000 በላይ የአይኤስ ተዋጊዎች አሁንም በኢራቅ እና በሶሪያ እንደሚንቀሳቀሱ ገምቷል።

አሁንም ቢሆን የተደመሰሰ በመምሰል አድብቶ የተቀመጠ የእስላማዊ መንግስት ህዋስ በገጠር እና በትናንሽ ከተሞች ውስጥ አመፅን ማቀጣጠል እንደሚቀጥሉ የሚጠበቅ ቢሆንም ወደ ዋና ከተማው እምብዛም ዘልቆ ገብተው ጥቃት የፈጽማሉ የሚል ግምት ግን አልነበረም።

በባግዳድ ውስጥ የመጨረሻው ገዳይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈጸመ ሲሆን በወቅቱ በደርሰው የቦንብ ፍንዳታ ከ 30 ሰዎች በላይ መገደላቸው ይታወሳል።

ይህ አረመኔያዊ ድርጊት የተፈጸመው ቀደም ሲል በአገሪቷ ሊካሄድ የታቀደው አጠቃላይ ምርጫ ከሰኔ ወር ወደ ጥቅምት ወር 2021 ዓ.ም እንዲተላለፍ ተብሎ መንግስት ከገለጸ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑም ተገልጿል።

21 January 2021, 12:06