ፈልግ

Vatican News
ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳን እግዚአብሔር እኛን መባረኩን ይቀጥላል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በሕዳር 23/2013 ዓ.ም  ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ የጠቅላላ አስተምህሮ ነበር፣ እንዲህም ይላል. . .

“በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን፤ ይኸውም፣ በሚወደው በእርሱ በኩል በነጻ የተሰጠን ክቡር የሆነው ጸጋው እንዲመሰገን ነው። በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን፤ ጸጋውንም በጥበብና በማስተዋል ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።

ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በእርሱ ተመርጠናል፤ ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል፤ አምናችሁም፣ በእርሱ በመሆን ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል።ለክብሩ ምስጋና ለመሆን የእግዚአብሔር የሆኑት እስኪዋጁ ድረስ፣ እርሱ ለርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው” (ኤፌሶን 1፡3-14)።

በሚለውና በክርስቶስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳን መንፈሳዊ ለውጥ አስክናመጣ ድረስ እግዚአብሔር እኛን መባረኩን ይቀጥላል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ ትኩረት የምናደርገው በጸሎት አስፈላጊ ልኬት ማለትም በረከት ላይ ነው። በጸሎት ዙሪያ ላይ የጀመርነውን አስተንትኖ ዛሬም እንቀጥላለን። በፍጥረት ታሪኮች ውስጥ (ዘፍ. 1-2) እግዚአብሔር ዘወትር ሕይወትን ይባርክ እንደ ነበረ አይተናል። እንስሳትን ይባርካል (ዘፍ. 1፡22) ፣ ወንድና ሴትን ይባርካል (ዘፍጥረት 1፡28) ፣ በመጨረሻም የእረፍት ቀን የሆነውን ሰንበትን በመባረክ ፍጥረታት ሁሉ ደስተኛ እንዲሆኑ አድርጓል (2፡3)። የሚባርከው እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች ውስጥ የማያቋርጥ የበረከት ድግግሞሽ አለ። እግዚአብሔር ይባርካል ፣ ነገር ግን ሰዎችም ይባርካሉ ፣ እናም በረከቱን በሕይወቱ በሙሉ ከተቀበለው ሰው ጋር አብሮ የሚሄድ ልዩ ጥንካሬ እንደነበረው እና በእግዚአብሔርም እንዲለወጥ የሰውን ልብ የሚያዘጋጅ መሆኑ ተገልጧል።

በዓለም መጀመሪያ ላይ ስለዚህ ሁሉም ነገር “ጥሩ ነበር” በማለት የሚናገር፣ በጥሩ ሁኔታ የሚናገር ፣ በደንብ የሚናገር እግዚአብሔር አለ። የእጆቹ እያንዳንዱ ሥራ ጥሩ እና የሚያምር መሆኑን ይመለከታል፣ እናም የሰው ልጆችን የፈጠረበትን ሁኔታ ሲመለከት የእጆቹ ሥራ “እጅግ መልካም” (ዘፍ 1፡31) መሆናቸውን ተመለከተ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ እግዚአብሔር በሥራው የቀረፀው ያ ውበት ይቀየራል ፣ እናም የሰው ልጅ በዓለም ላይ ክፋትን እና ሞትን የማስፋፋት ችሎታ ያለው ብልሹ ፍጡር ይሆናል ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን የመጀመሪያ አሻራ ፣ እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ ፣ በሰው ተፈጥሮ ፣ በሁላችን ውስጥ ያስቀመጠው የመልካም ሥራ አሻራ መቼም ቢሆን ሊያጠፋው አይችልም ፣ የመባረክ ችሎታ እና የመባረክ እውነታ እርሱ ጋር አለችና። እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሆነ የሰው ልጆችን እንኳን ሳይቀር በመፍጠሩ አልተሳሳተም።  የዓለም ተስፋ በእግዚአብሔር በረከት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይኖራል - እርሱ እኛን መውደዱን ቀጥሏል ፣ እሱ በመጀመሪያ ገጣሚው ፔጊ እንደተናገረው ለእኛ መልካም ነገርን ይመኛል።

የእግዚአብሔር ትልቁ በረከት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፣ የእግዚአብሔር ፣ የልጁ ታላቅ ስጦታ ነው። ለሰው ልጆች ሁሉ በረከት ነው ፣ ሁላችንን ያዳነን በረከት ነው። እርሱ “እኛ ገና ኃጢአተኞች ሳለን” እንባረክበት ዘንድ አብ የላከልን ዘላለማዊ ቃል ነው (ሮሜ 5፡8) ይላል ቅዱስ ጳውሎስ- ቃል ሥጋ ሆነ በመስቀል ላይ ስለ እኛ  ብሎ ተሰቀለ።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በስሜታዊነት የእግዚአብሔርን የፍቅር ዕቅድ በማወጅ እንዲህ ይላል-“ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን፤ ይኸውም፣ በሚወደው በእርሱ በኩል በነጻ የተሰጠን ክቡር የሆነው ጸጋው እንዲመሰገን ነው” (ኤፌ 1፡3-6) በማለት ይገልጸዋል። በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን የክርስቶስን ምስል ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋው የሚችል ኃጢአት የለም። እግዚአብሔር የሰጠንን ያን ምስል ምንም ዓይነት ኃጢአት ሊያጠፋው አይችልም። የክርስቶስ ምስል ነውና። ምስሉን ሊያበላሸው ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን በእግዚአብሄር ምህረት ሊስተካከል ይችላል። ኃጢአተኛ በስህተቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የኃጢአተኛው ልብ በመጨረሻ እንደሚከፈት እና እንደሚለወጥ ተስፋ በማድረግ እስከ መጨረሻው ይታገሳል። እግዚአብሔር እንደ ጥሩ አባት ነው - እሱ እንደ ጥሩ እናት ነው- እግዚአብሔር እንደ አንድ መልካም እናት ነው። እናት እና አባት ምንም ያህል ቢሳሳትም ሁል ጊዜም ቢሆን ልጃቸውን መውደዳቸውን አያቆሙም። ሰዎች ወደ እስር ቤት ለመግባት ወረፋ ሲይዙ ያየሁባቸውን ብዙ ጊዜያት አስታውሳለሁ። ብዙ እናቶች ወደ እስር ቤት ለመግባት እና በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ልጆቻቸውን ለመጎብኘት የተሰለፉ ብዙ እናቶች፣ ልጆቻቸውን መውደዳቸውን አያቆሙም እናም በመንገድ ላይ በአውቶቡስ በመጓዝ ላይ የሚገኙ ሰዎች ይህንን ሰለፍ ሲመለከቱ “አህ እነዚህ የእስረኞች እናቶች ናቸው” ብለው እንደሚያስቡ ያውቃሉ። ነገር ግን በዚህ አያፍሩም፣ ወይም ያፍሩ ይሆናል ነገር ግን ልጆቻቸውን መጎብኘት አያቆሙም ይቀጥላሉ ፣ ምክንያቱም ከእፍረት ይልቅ ልጆቻቸው የበለጠ አስፈላጊ ስለሆኑ። ስለዚህ እኛም ከፈጸምናቸው ወይም ማደረግ ከምንችላቸው ኃጢአቶች ሁሉ በላይ ለእግዚአብሄር በጣም አስፈላጊዎች ነን ፣ ምክንያቱም እርሱ አባት ነው ፣ እርሱ እናት ጭምር ነው፣ ንፁህ ፍቅር ነው ፣ ለዘላለም ባርኮናል። እናም በረከታችንን መቼም አያቆምም።

ጠንካራ ተሞክሮ በእስር ቤት ውስጥ ወይም በማገገሚያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኘው ማህበረሰብ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ የበረከት ጽሑፎች ማንበብ ነው። እነዚያ ከባድ ስህተቶች ቢኖሩባቸውም የተባረኩ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሰማይ አባት መልካሙን እንደሚፈልግ እንዲሰማቸው እና በመጨረሻም ራሳቸውን ለመልካም ነገር ይከፈታሉ የሚል ተስፋ አለው አግዚአብሔር። በጣም የቅርብ ዘመዶቻቸው እንኳን ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህ ሰዎች ከፈጸሙት ስህተት በፍጽሙ ሊመለሱ አይችሉም ብለው ቢያምኑም ቢተዋቸው እንኳን ለእግዚአብሄር ግን ሁሌም ልጆቹ ናቸው። እግዚአብሔር በውስጣችን ያለውን የለጅነት ምስል መሰረዝ አይችልም፤ እያንዳንዳችን የእርሱ ወንድ እና ሴት ልጆቹ ነን። አንዳንድ ጊዜ ተዓምራት ሲከሰቱ ይታያሉ-ወንዶች እና ሴቶች እንደገና ሲወለዱ። ምክንያቱም በልጅነት መንፈስ የሰጣቸውን በረከት ተመልሰው ያገኛሉና፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ጸጋ ሕይወትን ይለውጣል እኛን እንደ ማንነታችን ይቀበለናል፣ እኛን ፈጽሞ አይተወንም።

እስቲ ለምሳሌ ኢየሱስ ከዘኬዎስ ጋር ያደረገውን እናስብ (ሉቃስ 19፡1-10)። ሁሉም ሰው በእሱ ላይ የነበረውን ክፉ ነገር ብቻ ነው የተመለከተው፣ በሌላ በኩል ኢየሱስ በእርሱ ውስጥ የመልካም ነገር ፍንጭ ያያል፣ ከዚያ ኢየሱስን ለማየት ካለው ጉጉት የተነሳ የሚያድነውን ምህረት ለማየት ዛፍ ላይ ይወጣል። ስለሆነም በመጀመሪያ የዛኪዎስ ልብ ከዚያም ሕይወት ተለውጧል። በተተው እና በተጣሉ ሰዎች ውስጥ፣ ኢየሱስ የአባቱን የማይሽረውን በረከት አየ። ዘኬዎስ ሕዝቡ የሚያውቀው ኃጢአተኛ  የነበረ ሰው ነው፣ እሱ ብዙ መጥፎ ነገሮችን አደረገ ፣ ነገር ግን ኢየሱስ ያንን የማይረሳ የአባቱን በረከት ምልክት እና ከዛም ርህራሄውን አይቷል።

በወንጌል ውስጥ በጣም የተደጋገመው ይህ ሐረግ “ለእርሱ ራራለት” የሚለው ቃል እሱን ለመርዳት እና ልቡን ለመለወጥ ይመራዋል። በተጨማሪም እርሱ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ ጋር ራሱን ለመለየት መጣ (ማቴ 25፡31-46)። በማቴዎስ 25 ሁላችንም የምንፈርድበት የመጨረሻው “ፍርድ” በሚለው አንቀፅ ውስጥ ኢየሱስ “እኔ ተርቤ ነበርኩ ፣ ራቁቴን ነበርኩ ፣ እስር ቤት ነበርኩ ፣ ሆስፒታል ውስጥ ነበርኩ ፣ እዚያ ነበርኩ ...ወዘተ” ይላል።

ለሚባርከን እግዚአብሔር እኛም በበረከት ምላሽ እንሰጣለን - እግዚአብሔር እንድንባርከው አስተምሮናል እናም መባረክ አለብን - ይህ የምስጋና ፣ የስግደት ፣ የምስጋና ጸሎት ነው። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል “ቡራኬ የክርስቲያናዊ ጸሎትን መሰረታዊ እንቅስቃሴ ይገልጻል፣ ይም ማለት በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል የሚደረግ ግንኙነት ነው። በቡራኬ አማካይነት እግዚአብሔር ስጦታና ስጦታውን የሚቀበለው ሰው እሽታ በምክክር እርስ በእርስ ይተሳሰራሉ (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2626)። ጸሎት ደስታ እና ምስጋና ነው። እግዚአብሔር እኛ እንድንዋደድ እስክንለውጥ አልጠበቀንም ፣ ነገር ግን እሱ ገና ብዙ ጊዜ ቀደም ብሎ ፣ ገና ኃጢአት ውስጥ ሳለን ወደደን።

እኛን የሚባርከንን ይህንን እግዚአብሔርን ብቻ መባረክ አንችልም ፣ በእሱ ውስጥ ያለውን ሁሉንም ፣ ሁሉንም ሰዎች መባረክ አለብን ፣ እግዚአብሔርን መባረክ እና ወንድሞቻችንን መባረክ ፣ ዓለምን መባረክ አለብን -ይህ የክርስቲያን የዋህነት ፣ የተባረከ የመሆን ችሎታ እና የመባረክ ችሎታ ነው። ሁላችንም ያንን ብናደርግ ኖሮ ጦርነቶች በእርግጠኝነት አይኖሩም ። ይህ ዓለም በረከት ይፈልጋል፣ እኛም በረከቱን መስጠት እና በረከቱን መቀበል እንችላለን። አብ ይወደናል። እና እኛ እሱን የመባረክ ደስታ እና እሱን የማመስገን ደስታ እና በእርሱ ለመረገም ሳይሆን ለመባረክ ብቻ የመማር ደስታ ብቻ ነው ያለን። እናም መራገም ለለመዱት ሰዎች ፣ሁል ጊዜ አስቀያሚ ቃል ለሚናገሩ ሰዎች ፣ በልባቸውም ቢሆን በአፋቸው ላይ እርግማን ያላቸው ሰዎች ከመራገም መባረክ ይሻላል። እያንዳንዳችን ማሰብ እንችላለን -እንደዚህ የመረገም ልማድ አለኝ? የተባረከ ልብ ስላለን ከተባረከ ልብ መርገሙ መውጣት ስለማይችል ይህንን ልማድ እንዲለውጥ የጌታን ጸጋ እንጠይቅ። እንባረክ እንጂ መቼም ቢሆን እንዳንረግም ጌታ በምሕረቱ ይርዳን።

02 December 2020, 13:46