ፈልግ

Vatican News
ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት  (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የሚጸልዩ ሰዎች ጀርባቸውን ለዓለም በጭራሽ አይሰጡም፣ ለዓለም ይጸልያሉና” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 07/2013 ዓ.ም ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ። የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ። በሰንሰለት የታሰረ መልእክተኛ የሆንሁት ለዚሁ ነውና። ስለዚህ መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ” (ኤፌሶን 6፡18-20) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “የሚጸልዩ ሰዎች ፊታቸውን በጭራሽ ወደ ዓለም  አያዞሩም” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የሚጸልዩ ሰዎች ጀርባቸውን በጭራሽ  ወደ ዓለም  አያዞሩም።  ለዓለም ይጸልያሉና! ጸሎት ደስታን እና ሀዘንን፣ የሰዎችን ተስፋ እና ጭንቀቶች የማይሰበስብ ከሆነ “የማስዋብ” እንቅስቃሴ፣ እንዲያው ቀስቃሽ የሆነ እንቅስቃሴ ሆኖ ይቀራል። ሁላችንም ውስጣዊነትን እንፈልጋለን - ከአምላክ ጋር ለሚኖረን ግንኙነት በተወሰነ ቦታ እና ጊዜ ውስጥ ወደ ውስጣችን በመግባት እናፈገፍጋለን። ይህ ማለት ግን ከእውነታው እንሸሻለን ማለት አይደለም። በጸሎት አማካይነት እግዚአብሔር የሁሉንም ሰው ረሃብ ለማርካት “ይወስደናል ፣ ይባርከናል ፣ ከዚያም ልባችንን ይሰብራል እንዲሁም ይሰጠናል”። እያንዳንዱ ክርስቲያን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ የሚቆረስ እና የሚጋራ እንጀራ እንዲሆን ተጠርቷል።

ስለሆነም የፀሎት ሰው የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች ብቸኝነትን እና ዝምታን ይፈልጋሉ፣ እንዳይረበሹ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ድምጽ በተሻለ መጠን ለማዳመጥ ያስችላቸው ዘንድ። አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ ራሱ እንደመከረው በራሳቸው ክፍል ምስጢር ውስጥ በመግባት ከዓለም ይወጣሉ (ማቴ 6፡6 ይመልከቱ)። ነገር ግን የትም ቢሆኑ ሁል ጊዜ የልባቸውን በሮች ክፍት ያደርግላቸዋል - እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ሳያውቁ ለሚጸልዩ ሰዎች የተከፈተ በር ነው፣ እነዚያ በጭራሽ የማይጸልዩ ነገር ግን በውስጣቸው አንድ የሚያናፍቅ ጩኸት ፣ የተደበቀ ልመና ለያዙ ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር ልቡን ይከፍትላቸዋል። ለተሳሳቱ እና መንገዱን ላጡት…. የሚጸልይ ሰው በር ማንኳኳት የሚችል ለማንንም የማያዳላ ርህሩህ ልብ ያገኛል። በብቸኝነት ውስጥ ሁሉንም ነገር እና ሁሉንም በእግዚአብሔር ውስጥ ለማግኘት ራሳቸውን ከሁሉ እና ከማንኛውም ሰው ይለያሉ። እነዚህ ሰዎች ሀዘኖቻቸውን እና ኃጢአቶቻቸውን በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ለመላው ዓለም ይጸልያሉ። ለእያንዳንዱ ሰው ይጸልያሉ - እነሱ በዚህ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር “አንቴናዎች” ናቸው። የሚጸልይ ሰው ሁሉ በሩን በሚያንኳኳ እንድ ሚስኪን ድሃ ሰው እና የነገሮችን ትርጉም በሳተ ሰው ሁሉ ውስጥ የክርስቶስን ፊት ያያል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ይህንን በተመለከተ ሲናገር “ምልጃ ማለት ስለሌላው መለመን ማለት ሲሆን ከእግዚአብሔር ምሕረት ጋር ራሷን ያስማማች ልብ መለያ ባሕሪይ ነው። በቤተክርስቲያን ዘመን ደግሞ ከክርስቶስ ምልጃ ጋር ተሳታፊነት ያለው ክርስቲያናዊ ምልጃ የቅዱሳን ሱታፌ መገለጫ ነው” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2635)።

የሰው ልብ ወደ ጸሎት ያዘነብላል። በቀላሉ ጸሎት ሰብዓዊ ነው። ወንድማቸውን ወይም እህታቸውን የማይወዱ በቁም ነገር አይጸልዩም። በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የሌሎችን ሀዘን እና ደስታ የሚያውቁ ሰዎች የዓለምን “ዋና ስርዓቶችን” ከሚመረምሩት ሰዎች በላቀ ሁኔታ ምጡቅ ናቸው። በዚህ ምክንያት የሰዎች ተሞክሮ በእያንዳንዱ ጸሎት ውስጥ ይገኛል፣ ምክንያቱም ሰዎች ምንም ዓይነት ስህተት ቢሠሩም ፈጽሞ ውድቅ መሆን ወይም መጣል የለባቸውም።

አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ምንም ልዩነት ሳይፈጥሩ ለኃጢአተኞች ሁሉ ሲጸልዩ ፍርድም ሆነ ውግዘት አያቀርብም - ለሁሉም ይጸልያሉ። እናም ለራሳቸውም ይጸልያሉ። በዚያን ጊዜ እነሱ ከሚጸልዩላቸው ሰዎች ያን ያህል የተለዩ እንዳልሆኑ ያውቃሉ። የፈሪሳዊው እና የቀራጩ ሰው ምሳሌ ትምህርት ሁል ጊዜም ሕያው እና ወቅታዊ ነው (ሉቃስ 18: 9-14 ይመልከቱ)፤ እኛ ከማንም አንበልጥም ፣ ሁላችንም ደካማ፣ መከራ የበዛብን እና ኃጢአተኛ የሆንን ወንድማማቾች እና እህተማማቾች ነን። ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ልናቀርበው የምንችለው ጸሎት እንዲህ የሚል ነው “ጌታ ሆይ ፣ ማንም በአንተ ፊት ጻድቅ አይደለም (መዝ 143: 2 ን ተመልከት) ፣ ሁላችንም ባለዕዳዎች ነን፣ እያንዳንዳችን ልንከፍለው የማንችለው ከፍተኛ ዕዳ አለብን፣ በፊትህ ኃጢአት የሌለበት ማንም ሰው የለም። ጌታ ሆይ ማረን! ” ብልን ልንጸልይ ይገባል። ለሚጸልዩ፣ ለሚማልዱ እና በአብዛኛዎቹ ለማይታወቁ ሰዎች ምስጋና ይግባቸውና ዓለም መኖሯን ቀጥላለች! በስደት ወቅት የጌታቸውን ቃል ደጋግመው የሚናገሩ ብዙ ስማቸው ያልታወቁ ክርስቲያኖች አሉ “አባት ሆይ ይቅር በላቸው። የሚያደርጉትን አያውቁምና ”(ሉቃ 23፡ 34) በማለት ለሌሎች ይጸልያሉ።

መልካሙ እረኛ የራሱ ሰዎች ኃጢአት ከመገንዘቡ በፊትም ቢሆን ታማኝ ሆኖ ይቀጥላል - ልጆቹ ራቅ ብለው ትተውት ሲሄዱ እንኳን አባት ሆኖ ከእነርሱ ጋር መጓዝ ይቀጥላል። እጆቹን አቁስለው ካደሙ ሰዎች ጋርም እንኳ አብሮ በመጓዝ እንደ እረኛ ሆኖ በአገልግሎቱ ይጸናል፤ እሱ መከራ እንዲቀበል ላደረጉ ሰዎች እንኳን ቢሆን ልቡን አይዘጋም።

ቤተክርስቲያኗ በሁሉም አባላቶቿ ውስጥ የምልጃ ጸሎት የማድረግ ተልእኮ አላት። ይህ በተለይ የኃላፊነት ሚና ለሚጫወቱት ወላጆች ፣ መምህራን ፣ የተቀቡ አገልጋዮች ፣ የማኅበረሰብ ኃላፊዎች … ሚና ነው። እንደ አብርሃምና ሙሴ በአምላክ ፊት በአደራ የተሰጧቸውን ሰዎች አንዳንድ ጊዜ “መከላከል” አለባቸው። በእውነቱ እኛ እየተናገርን ያለነው በእግዚአብሔር አይኖች እና ልብ ፣ በተመሳሳይ የማይበገር ርህራሄ እና ምሕረቱ በእነርሱ ላይ ሆኖ እንዲጠብቃቸው ነው።

ሁላችንም በአንድ ዛፍ ላይ እንዳለ ቅጠሎች ነን-እያንዳንዱ የሚወድቅ ቅጠል እያንዳንዳችን ለሌላው በመጸለይ ታላቅ የሆነውን እግዚአብሔርን እንድናስታውስ ያደርገናል።

16 December 2020, 12:40