ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ አመስጋኞች በምንሆንበት ወቅት በዓለም ውስጥ ተስፋን እንዘራለን አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 21/2013 ዓ.ም ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ሁል ጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና።የመንፈስን እሳት አታዳፍኑ” (1 ተሰሎንቄ 5፡16 -19) በሚለው የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “አመስጋኞች በምንሆንበት ወቅት በዓለም ውስጥ ተስፋን እንዘራለን ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በምስጋና ጸሎት ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ። እናም በወንጌላዊ ሉቃስ ከተዘገበው ትዕይንት እንደ ፍንጭ እወስዳለሁ። ኢየሱስ በመንገድ ላይ እያለ አሥር ለምጻሞች “ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ ማረን!” (ሉቃስ17:13) ብለው ለመኑት። የሥጋ ደዌ በሽታ የደረሰባቸው በአካል ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ መገለል እና በሃይማኖት መገለል ጭምር እንደተሰቃዩ እናውቃለን። የተገለሉ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስ እነሱን ከመገናኘት ወደኋላ አላለም።፡ አንዳንድ ጊዜ ​​በሕጉ ከተደነገጉ ገደቦች ባሻገር በመሄድ በለምጽ በሽታ የተያዘውን ሰው ነካ ፣ አቅፎ ፈወሰው - ነገር ግን በሕጉ መሰረት እንዲህ ማድረግ አልነበረበትም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። ተከስተው የነበሩትን ፈውሶች እንዲያረጋግጡ በሕግ ለተሾሙት ለካህናት ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ኢየሱስ ራቅ ብሎ ይጋብዛቸዋል (ሉቃስ 17፡14) ኢየሱስ ሌላ ምንም ነገር አልተናገረም ነበር። እርሱ ጸሎታቸውን ሰማ ፣ የምህረት ጩኸታቸውን ሰምቶ ወዲያውኑ ወደ ካህናቱ ላካቸው።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

እነዚያ አስር ለምጻሞች አመኑ ፣ እስኪያገግሙ ድረስ እዚያ አልቆዩም ነበር፣ በፍጹም እንዲህ አላደረጉም፣ ይልቁኑ አመኑ እናም ወዲያውኑ ሄዱ፣ በመንገድ ላይ ሳሉ ተፈወሱ ፣ አሥሩም ተፈወሱ። ካህናቱ ስለዚህ ፈውሳቸውን ማረጋገጥ እና ወደ ተለመደው ሕይወት እንደገና እንዲመለሱ መፍቀድ ነበረባቸው። ነገር ግን አስፈላጊው ቦታ የሚገባው እዚህ ነው-ከቡድኑ ውስጥ አንዱ ብቻ ወደ ካህናት ከመሄዱ በፊት ኢየሱስን ለማመስገን እና ለተቀበለው ጸጋ እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሷል። አንድ ብቻ፣ ሌሎቹ ዘጠኙ መንገዳቸውን ቀጠሉ። ደግሞም ኢየሱስ እንደ ተናገረው ያ ሰው ሳምራዊ ነበር፣ በዚያን ጊዜ ለነበሩት አይሁዳዊያን ሳምራዊያን እንደ “መናፍቅ” ይቆጠሩ ነበር። ኢየሱስ “ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?” (ሉቃስ 17፡18) በማለት ተናጋሯል። ይህ ታሪክ ልብ የሚነካ ነው።

ስለእዚህ ታሪክ ለመናገር ያህል ዓለምን በሁለት ይከፍላል - የማያመሰግኑ እና የሚያመሰግኑ ሰዎች እንዳሉ ይናገራል፣ ሁሉም ነገር እንደ ሚገባቸው አድርገው የሚወስዱ ሰዎች እና ሁሉን እንደ ስጦታ ወይም እንደ ጸጋ አድርገው የሚቀበሉ ሰዎች። ይህንን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ሲናገር “እንደ ልመና ጸሎት ሁሉ እያንዳንዱ ሁኔታ እና ጥያቄ የምስጋና መባእ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2638) በማለት ይናገራል። የምስጋና ጸሎት ሁል ጊዜ እዚህ ይጀምራል- ጸጋ ከእኛ እንደሚቀድመን መገንዘብ አለብን። እንዴት ማሰብ እንዳለብን ከመማራችን በፊት አስቦን ነበር፣ እንዴት መውደድ እናዳለብን ከመማራችን በፊት ተወደድን፣ ልባችን ምኞትን ከመፀነሱ በፊት ተመኘን። ህይወትን እንደዚህ የምንመለከት ከሆነ “አመሰግናለሁ” የሚለው ቃል የዘመናችን አንቀሳቃሽ ኃይል ይሆናል። እናም “አመሰግናለሁ” ለማለት እንኳን ስንት ጊዜ እንረሳለን።

ለእኛ ለክርስቲያኖች ምስጋና የሚለው ቃል እጅግ አስፈላጊ ለሆነው ምስጢረ ቅዱስ ቁርባን የተሰጠ መጠርያ ስም ነው። በእውነቱ  የግሪክ ቃል በትክክል ይህንን በተመለከተ ሲገልጽ ቅዱስ ቁርባን ማለት ምስጋና ማለት እንደ ሆነ ይገልጻል። ክርስቲያኖች እንደ ሁሉም አማኞች ለሕይወት ስጦታ እግዚአብሔርን ይባርካሉ ፡፡ በሕይወት መኖር ከሁሉም በላይ የተቀበልነው ስጦታ ነው፣ሕይወትን ማግኘት በራሱ ትልቅ ስጦት ነው። ሁላችንም የተወለድነው አንድ ሰው ሕይወት እንዲኖረን ስለፈለገ ነው ፡፡ እናም በመኖር ከሚወጡት ረዥም እድሜያችን ውስጥ እኛ ያለብን የመጀመሪያው እዳችን ነው። የምስጋና ባለዕዳዎች ነን። በሕይወታችን ውስጥ ከአንድ በላይ ሰዎች በንጹህ ዓይኖቻቸው እኛን በምስጢር ተመልክተዋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች አስተማሪዎች ፣ ካቴኪስቶች ፣ ከሚጠበቅባቸው በላይ እና በላይ ሚናቸውን ያከናወኑ ሰዎች ናቸው።፡ እናም አመስጋኞች እንድንሆን ድፍረቱ እንዲኖረን አድርገውናል።፡ ጓደኝነት እንኳን ሁል ጊዜም ልናመሰግነው የሚገባ ስጦታ ነው ፡፡

ያለማቋረጥ ልንለው የምንችለው ይህ “አመሰግናለሁ” የተሰኘው ቃል ክርስቲያኖች ከሁሉም ጋር የሚጋሩት ቃል ሲሆን ይህ ምስጋና ኢየሱስን ለመገናኘት ዕድሉን ይከፍትልናል። ቅዱሳን ወንጌላት እንደሚነግሩን ኢየሱስ ሲያልፍ ብዙውን ጊዜ ባገኛቸው ሰዎች ውስጥ በደስታ  እግዚአብሔርን ያስመሰግን ነበር። የቅዱስ ወንጌል ቃል ውስጥ በአዳኙ መምጣት በጣም በሚነኩ በጸሎት ሰዎች ተሞልተዋል። እኛም በዚህ ግዙፍ ደስታ እንድንሳተፍ ተጠርተናል። የተፈወሱት አሥሩ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ታሪክ ይህንን ይጠቁማል። በተፈጥሮ ሁሉም ጤንነታቸውን መልሰው በማግኘታቸው እና በማገገማቸው ደስተኞች ስለነበሩ ከማህበረሰቡ ያገለላቸውን ያንን የማያቋርጥ የግዳጅ መንገድ እንዲያቆሙ አስችሏቸዋል። ነገር ግን ከእነሱ መካከል ተጨማሪ ደስታን ያገኘ አንድ ሰው ነበር - ከመፈወሱ በተጨማሪ ኢየሱስን በማግኘቱ ይደሰታል። እሱ ከክፉ ነገር ነፃ በመውጣቱ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን አሁን እሱ የመወደድን እርግጠኛነት አግኝቷል። ይህ ቁልፍ ነገር ነው -አንድን ሰው ስታመሰግኑ እንደተወደዱ እርግጠኛ መሆንዎን ይገልጻሉ። እናም ይህ ትልቅ እርምጃ ነው-እርስዎ እንደሚወደዱ እርግጠኛ መሆን በራሱ እጅግ በጣም ያስደስታል። ዓለምን የሚያስተዳድረው ኃይል ፍቅር ነው - ዳንቴ በመባል የሚታወቅ ጸሐፊ እንደ እንደተናገረው “ፀሐይን እና ሌሎች ኳክብትን የሚያንቀሳቅስ” ፍቅር ነው። እኛ ከእንግዲህ ወዲያ እዚህም እዚያም ዓላማ በሌለው መንገድ የሚንከራተቱ ተላላኪዎች አይደለንም፣ በፍጹም እንዲህ አይደለንም፣ ቤት አለን ፣ በክርስቶስ ውስጥ እንኖራለን ፣ እናም ከዚያ “መኖሪያ” ውስጥ ለእኛ እጅግ በጣም ቆንጆ ሆኖ በሚታየው የተቀረው ዓለም ላይ እናሰላስላለን። እኛ የፍቅር ልጆች ነን ፣ የፍቅር ወንድሞች እና እህቶች ነን ፡፡ እኛ የምናመሰግን ወንዶች እና ሴቶች ነን።

ስለዚህ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ኢየሱስን በማግኘታችን በሚሰማን ደስታ ውስጥ ሁነን ሁል ጊዜ ለመቆየት እንፈልግ፡፡ ደስታን እናዳብር። ዲያቢሎስ፣ ​​ይልቁኑ፣ እኛን ካታለለን በኋላ - በማንኛውም ፈተና - ሁል ጊዜ እኛን በሐዘን እና በብቸኝነት ይተወናል። በክርስቶስ ውስጥ ከሆንን ፣ ከሌሎች ብዙ ጓደኞች ጋር በመሆን በመንገዳችን ላይ በደስታ ከመቀጠል የሚያግደን ኃጢአት እና ማስፈራሪያ አይኖርም።

ከሁሉም በላይ ማመስገን መዘንጋት የለብንም-አመስጋኞች ከሆንን ዓለም ትንሽም ቢሆን የተሻለች ትሆናለች ፣ ነገር ግን ትንሽ ተስፋን ለማስተላለፍ በቂ ነው ፡፡ ዓለም ተስፋ ይፈልጋል ፡፡ እናም በምስጋና ፣ በዚህ አመሰግናለሁ የመባባል ልማድ ፣ ትንሽ ተስፋ እናስተላልፋለን ፡፡ ሁሉም ነገር አንድነት ያለው እና ሁሉም ነገር የተገናኘ ነው ፣ እናም እኛ ባለንበት ሁሉ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል። ወደ ደስታ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ገለጸው “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና።የመንፈስን እሳት አታዳፍኑ” (1 ተሰሎንቄ 5፡17-19) በማለት ይናገራል።መንፈስን አታዳፍኑ እንዴት የሚያምር የሕይወት እቅድ ነውና! በውስጣችሁ ያለውን መንፈስ አታዳፍኑ ወደ ምስጋና ያደርሰናል ፡፡ አመሰግናለሁ።

30 December 2020, 13:44

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >