ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጥር 16/2012 ዓ. ም. የኢራቅ ፕሬዚደንት የሆኑትን ክቡር ባራም ሳሊን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጥር 16/2012 ዓ. ም. የኢራቅ ፕሬዚደንት የሆኑትን ክቡር ባራም ሳሊን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑ ተነገረ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታወቀ። ቅዱስነታቸው ወደ ኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. መገባደጃ ወዲህ የመጀመሪያቸው መሆኑን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ ገልጾ፣ በኢራቅ ቆይታቸው አምስት አካባቢዎችን እነርሱም፥ ባግዳድ፣ ኡር፣ ኤርቢል እና ቃራቆሽን የሚጎበኟቸው መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዓለማችን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለአሥራ አምስት ወራት አቋርጠው የቆዩ ሲሆን፣ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ በማለት ከኢራቅ ሪፓብሊክ ሕዝብ እና ከአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል ግብዣ የደረሳቸው መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሃላፊ አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀው፣ ወቅቱ ሲደርስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የኮቪድ-19 መከላከያ ደንቦችን ባከበረ መልኩ እንደሚከናወንና ይህም በመርሃ ግብሩ ወደ ፊት የሚገለጽ መሆኑን አስታውቀዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ለመላው የኢራቅ ሕዝብ ያላቸውን ወዳጅነት እና ቅርበት በተጨባጭ ለመግለጽ እንደሆነ፣ ለምስራቅ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን የሚያደርግ ካቶሊካዊ ተቋም ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ለተገኙት ተወካዮች፣ ሰኔ 3/2012 ዓ. ም. መናገራቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ንግግር ኢራቅን ባለማቋረጥ እንደሚያስታውሷት ገልጸው፣ በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ እንደሚመኝ ገልጸዋል። የሐይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከአመጽ ጎዳና ወጥተው በሰላማዊ መንገድ የአገራቸውን ማኅበራዊ ዕድገት በጋራ ለማስጠበቅ የሚችሉበትን አጋጣሚ በመመኘት መሆኑንም አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 16/2012 ዓ. ም. የኢራቅ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት የሆኑትን ክቡር ባራም ሳሊን በቫቲካን ተቀብለው ካነጋገሯቸው ጊዜ ወዲህ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ያላቸው ተስፋ እየለመለመ መምጣቱ ታውቋል። ክቡር ፕሬዚደንት ባራም ሳሊ ቫቲካንን በጎበኙበት ወቅት ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። በውይይታቸው ወቅትም በኢራቅ ውስጥ መረጋጋትን በማምጣት፣ በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ መነጋገራቸው እና ለዚህም የጋራ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገዶች በማፈላለግ፣ ዜጎች ለአገራቸው ሉዓላዊነት በጋራ እንዲቆሙ ለማገዝ መወያየታቸውን፣ በአገሪቱ ውስጥ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረውን የክርስቲያን ማኅበርሰብ ጥንታዊ ታሪክ መጠበቅ እና ለወደ ፊት ደህንነታቸውም ዋስትና መስጠት በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውሷል።

የኢራቅ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ሳዳም ሁሴን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 2003 ዓ. ም. ከስልጣናቸው በኃይል በተወገዱበት ወቅት በአገሪቱ የነበሩ ክርስቲያኖች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን እስከ አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ እንደሚደርስ የሚገመት ሲሆን፣ በጦርነቱ ዓመታት ሜዳማው የነነዌ ክፍለ ግዛት በእስላማዊ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ከወደቀበት ከጎርጎሮሳዊያኑ 2014-2017 ዓ. ም. ድረስ በአገሪቱ የሚገኙ የክርስቲያኖች ቁጥር ከ300 እስከ 400 ዝቅ ማለቱ ታውቋል። የኢራቅ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር ባራም ሳሊን የኢራቅ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን ተጠቅመው አገራቸውን መልሰው በመገንባት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማከታተል መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ሙስጠፋ አል ካዜሚም በበኩላቸው በአስከፊ ጦርነት ምክንያት ከአገራቸው የተሰደዱት በርካታ ክርስቲያኖች ወደ አገራቸው ተመልሰው በመልሶ ግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ መጋበዛቸው ታውቋል። የኤኮኖሚ ቀውስ ያለባት ኢራቅ ሙስናን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ አጥ ችግር የሚገኝባት፣ በጦርነቱ ምክንያት ወደ 1.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎቿ የተፈናቀሉባት አገር በመሆኗ የዕድገት ውጥኖቿን ፈተና ላይ ጥሏል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” በኢራቅ ውስጥ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ከእነዚህም መካከል ግማሽ የሚያህሉ ሕጻናት መሆናቸውን ገልጿል። ባሁኑ ጊዜ በኢራቅ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ሆስፒታሎች እና የመድኃኒት እጥረት ያለ ሲሆን፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያትም በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይነገራል።

በእነዚህ እና ሌሎች ችግሮች ውስጥ ወደምትገኝ ኢራቅ የሚጓዙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኡር ክፍለ ግዛት በሚያደርጉት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ ክፍል፣ ከዚህ በፊት የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በክፍለ ግዛቱ ለሚገኙት ክርስቲያን ማኅበረሰብ ያሰቡትን የልማት ዕቅዶች ተግባራዊነት የሚያረጋግጡላቸው መሆኑ ታውቋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከታኅሳስ 1 - 3/ 1999 ዓ. ም. በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ያቀዱ ቢሆንም ወቅቱ የኢራቁ ፕሬዚደንት የነበሩት ሳዳም ሁሴን ከስልጣናቸው የወረዱበት እና አገሪቱ ወደ እርስ በእርስ አመጽ የገባችበት በመሆኑ ሳይሳካላቸው መቅረቱ ይታወሳል። ዛሬ ከሃያ ዓመታት በኋላ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ምኞት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እውን ሊሆን መቃረቡ ታውቋል።           

08 December 2020, 12:40