ፈልግ

የዓለም የወጣቶች ቀን አርማ የዓለም የወጣቶች ቀን አርማ 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ 2023 ዓ.ም ለ የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ያስተላለፉት መልእክት

“አንተ ወጣት ተነሥ እልሃለሁ!” (ሉቃስ 7፡14)

የተወደዳችሁ ወጣቶች!

በጥቅምት ወር 2018 (እ.አ.አ.) በወጣቶች ዙሪያ ላይ ወጣቶች፣ እምነት እና በጥሪ ላይ በማስተዋል ጥበብ ተሞልቶ መወሰን በሚል መሪ ቃል አንድ የብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ቤተክርስቲያን እናንተ በዚህ ዓለም ውስጥ ባላችሁ ቦታ ላይ፣ እናተ ለሕይወታችሁ ትርጉም እና ዓላማ ለማግኘት ስትሉ በምታደርጉት ፍለጋ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያልችሁን ግንኙነት ላይ የማሰላሰል ሂደት ጀምራለች። እ.ኤ.አ. ጥር 2019 ዓ.ም በፓናማ ተካሂዶ የነበረውን የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ለማክበር ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ በመቶዎች እና በሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር ተገናኝቼ ነበር። የዚህ ዓይነቱ ክስተቶች - ሲኖዶስና የዓለም ወጣቶች ቀን - “አብረን እንጓዝ” የሚለውን ትርጉም የሚያሰማ እና የቤተክርስቲያኗ መሰረታዊ ልኬት መገለጫ ናቸው።

በዚህ ጉዞ አንድ አስፈላጊ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በደረስን ቁጥር በእግዚአብሔር እና በህይወት ሂደት መሪነት  አዳዲስ ፈተናዎችን የመጋፈጥ ተግዳሮ ተጥሎብናል። ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን እናንተ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥሩ ግንዛቤ ያላችሁ ይመስለኛል! አዳዲስ ቦታዎችን እና ሰዎችን ለመፈለግ እና አዳዲስ ልምዶችን ለማግኘት መጓዝ እንደ ምትወዱ አውቃለሁ። ለዚህም ነው እ.አ.እ በ 2023 ዓ.ም ላይ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ ንግደት የፖርቹጋልን ዋና ከተማ ሌዝቦን የመረጥኩት ለዚህ ዓላማ ነው። በሌዝቦን ብዙ ሚስዮናውያንን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የኢየሱስን ልምዶች ለመጋራት የሌሎች ህዝቦች እና ብሄሮች ባሕል እና ልምድ ለማካፈል ከእዚህ ቀደም አይተውት ወደ ማይውቁት አገሮች ይጓዛሉ። በሌዝቦን ለሚካሄደው የዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ይሆን ዘንድ የተመረጠው “ማርያም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” (ሉቃ 1፡39) የሚለው መሪ ቃል ነው።  በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ እኔ በሌሎች ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ከአናንተ ጋር አስተንትኖ ለማደረግ እፈልጋለሁ፣ እ.አ.አ በ2020 ዓ.ም  “አንተ ወጣት ተነሥ እልሃለሁ!” (ሉቃስ 7፡14) እና እ.አ.አ. በ2021 ዓ.ም “አሁንም ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለ እኔ ስላየኸውና ምስክር እንድትሆን ልሾምህ ተገልጬልሃለሁ”(ሐዋ. 26፡16) በሚሉት ጥቅሶች ላይ እንድታስተነትኑ እፈልጋለሁ።

እንደምትመለከቱት “ተነስ” ወይም “ቁም” የሚለው ግስ በሦስቱም ጭብጦች ውስጥ ይታያል። እነዚህ ቃላት ደግሞ ስለ ትንሣኤ፣ ስለ አዲስ ሕይወት መነቃቃት ይናገራሉ። እ.አ.አ. በ2018 ዓ.ም የተካሄደው ሲኖዶስ ካበቃ በኋላ ከወጣቶች ጋር ተገናኝቼ ከተነጋገርኩኝ በኋላ በወጣው የመጨረሻው ሰነድ ላይ ቤተክርስቲያን በህይወታችሁ ጎዳና ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅ መብራት እንደ ሆነ የሚያመለክቱ እነዚህ ቃላት በሰፊው የተንጸባረቁበት በላቲን ቋንቋ “Christus Vivit” በአማርኛው “ክርስቶስ ሕያው ነው!” በሚል አርእስት የተጻፈ እንድ ቃለ ምዕዳን ይፋ መሆኑ ይታወቃል።  መላው ቤተክርስቲያን ወደ ሌዝቦን የምታደርገው ጉዞ እነዚህን ሁለት ሰነዶች ለመተግበር እና ለወጣቶች ሐዋርያዊ የሆነ እንክብካቤ መስጠት ላይ የተሰማሩትን ሰዎች ተልእኮ ለመምራት ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚያደርግ ተስፋ አለኝ።

አሁን “አንተ ወጣት ተነሥ እልሃለሁ” (ሉቃስ 7፡14) ወደ ሚለው ወደ የዚህ ዓመት መሪ ቃል ጭብጥ እንመለስ። ይህንን የወንጌል ጥቅስ “Christus Vivit” (ክርስቶስ ሕያው ነው!” በተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ በመጥቀስ  “ጥንካሬህን፣ ህልምህን፣ ጉጉትህን፣ ተስፋህን እና የልግስና መንፈስህን ካጣህ፣ ኢየሱስ እንድ ቀን ልጇ በሞተባት አንዲት መበለት ሴት ፊት ቆሞ በትንሳሄው ኃይል ሞቶ የነበረውን ልጅ እንደ ገሰጸው እና ከሞት እንዳስነሳ ሁሉ እናንተንም “አንተ ወጣት ተነስ እልሃለሁ!” ብሎ ይናገራል (Christus Vivit  ቁ. 20)።

ያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ውስጥ የተወሰደው ቃል ኢየሱስ በገሊላ ክፍለ አገር ናይን በመባል በምትታወቅ ከተማ ሲገባ የአንዲት መበለት እናት ብቸኛ ወንድ ልጅ የቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ እንደደረሰ ይተርካል። ኢየሱስ ሴቲቱ በልጇ መሞት በደረሰባት ከፍተኛ ሐዘን በመነካቱ የልጇ በድን ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ ሕይወት እንዲዘራ ያደርጋል። ይህ ተዓምር የተከሰተው ተከታታይ ቃላትን ከተጠቀመ እና ምልክቶች ከተከናወኑ በኋላ ነው - “ ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ “አይዞሽ፤ አታልቅሺ” አላት ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ “አንተ ወጣት ተነሥ እልሃለሁ” አለው” (ሉቃስ 7፡13 14)። በእነዚህ በጌታ ቃላት እና አካላዊ መገለጫዎች ላይ ለማሰላሰል ትንሽ ጊዜ እንውሰድ።

ሕመም እና ሞትን የማየት ችሎታ

ኢየሱስ ይህንን የቀብር ሥነ-ስርዓት በጥንቃቄ ይመለከት ነበር። በሕዝቡ መካከል ከነበሩ ሰዎች ውስጥ በታላቅ ስቃይ ውስጥ የነበረች የአንዲት ሴት ፊት ይመለከታል። የኢየሱስ የማየት ችሎታ የአዳዲስ ሕይወት ምንጭነት ያስከትላል። ጥቂት የሆኑ ቃላትን ብቻ ይጠቀማል።

የእኔ የማየት ችሎታ ምን ያህል ነው? ነገሮችን ስመለከት በጥንቃቄ እመለከታለሁ ወይንስ በሞባይል ስልኬ በሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶዎችን ወይም ማህበራዊ መገለጫዎችን በፍጥነት ሸብልዬ እንደምመለከተው ነው የማያቸው? በእውነተኛ ሰዓት ወይም ጊዜ በጭራሽ ላላየናቸው ነገሮች የዓይን ምስክሮች ሆነን የምንመሰክርባቸው ጊዜያት ምን ያህል ናቸው! አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ምላሻችን የተሳተፉትን ሰዎች ዓይኖች ለመመልከት እንኳን ትኩረት ሳንሰጥ በሞባይል ስልካችን ፎቶግራፍ ማንሳት እንወዳለን።

በዙሪያችን ሁሉ ያሉትን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በውስጣችን የሚገኙትን አካላዊ ፣ መንፈሳዊ ፣ ስሜታዊ ፣ ማህበራዊ የመሳሰሉ የሞት እውነታዎች ማየት እንችላለን። እኛ በእርግጥ እናስተውላቸዋለን ወይስ በቀላሉ እንዲደርስብን እንፈቅዳለን? ሕይወታችንን ለማትረፍ ምን በማድረግ ላይ እንገኛለን?

እኔ እንደማስበው በእናንተ እድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ሁሉ የሚያጋጥሟቸው አሉታዊ ሁኔታዎች አሉ ቢዬ አስባለሁ። አንዳንዶች በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም ነገር ለመፈጸም ይሞክራሉ፣ እናም በእዚህ መልኩ ባካበቱት ከፍተኛ ልምዶች የራሳቸውን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላሉ። ሌሎች ደግሞ ተስፋ የቆረጡ በመሆናቸው “ሞተዋል” ። አንዲት ወጣት ሴት “ከጓደኞቼ መካከል በነገሮች ተሳታፊ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ተነሳሽነታቸው እጅግ በጣም አናሳ መሆኑን እመለከታለሁ፣ ለመነሳት ድፍረቱን ስያጡ እመለከታለሁ” ብላ ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ ድብርት በወጣቶች ላይም እየተስፋፋ ነው፣ በአንዳንድ ሁኔታዎችም ሕይወታቸውን የማጣፋት ፈተና ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች አሉ። ሰዎች በጭንቀት እና በጸጸት ወደ ጥልቁ ውስጥ የሚዘፈቁበት ግድየለሽነት የሚንጸባረቅበት ስንት ሁኔታዎች አሉ! ጩኸቶቻቸው የማይሰማ ምን ያህል ወጣቶች እሉ! ይልቁንም ስለማንኛውም ነገር ወይም ስለ አንዳች ነገር ሳይጨነቁ የእራሳቸውን “የደስታ ሰዓት” በመጠቀም ለሌሎች ሰዎች ትኩረት የማይሰጡ ለሌሎች ሰዎችን በግድዬለሽነት የሚመለከቱ ሰዎች አሉ።

ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸውን ጥራዝ ነጠቅ በሆኑ ነገሮች ላይ ያባክናሉ፣ የኖሩ ይመስላቸዋል ነገር ግን ሞተዋል። በሃያ ዓመታቸው ሕይወታቸውን እውነተኛው ክብር ወደ ሚያስገኝ ደረጃ ከማሳደግ ይልቅ ህይወታቸውን ዝቅተኛ ወደ ሆነ ደረጃ ያወርዳሉ። ሁሉም ነገር ወደ “መኖር” እና እርካታ ወደ መፈለግ ደረጃ ያወርዳሉ፣ የመዝናኛ ጊዜ ይፈልጋሉ፣ ትኩረት እና ፍቅር … ወዘተ ወደ ሚያስገኙ ነገሮች ላይ ያተኩራሉ። እናም ወጣቶችን እና ጎልማሶችን በተመሳሳይ መልኩ የሚነካው እየጨመረ የመጣው ራሳችንን እንድናመልክ የሚያደርገን የዲጂታል ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋላል። በጣም ብዙ ሰዎች በዚህ መንገድ እየኖሩ ነው! አንዳንዶቹ ምናልባት የሕይወት ብቸኛ ዓላማ እየመሰላቸው ገንዘብ ለማግኘት ቀላል እና ቋራጭ መንገድ እየመሰላቸው በፍቅረ ነዋይ ሊወሰዱ ይችላሉ። በእዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ ደግሞ ለወደፊቱ ሐዘንተኛ፣ ግድየለሽ እና የብስጭት መንፈስ ይከተላል፣ የባዶነት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያስከትላል።

አሉታዊ ሁኔታዎች የሚከሰቱት ደግሞ በግለሰቡ ድክመት ሊሆን ይችላሉ፣ ምንም እንኳን የምንጨነቅበት ነገር፣ የወሰነው ነገር፣ ከእንግዲህ የማይሠራ ወይም የተፈለገነውን ውጤት የሚሰጥ ላይመስለን ይችል ይሆናል። ይህ በትምህርት ቤት ወይም በስፖርት እና በኪነጥበብ ረገድ በወጠነው ሕይወት ላይ ሊከሰት ይችላል… የ “ሕልሙ” ማለቂያ ሞት እንደ ሆነ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ነገር ግን ውድቀቶች የሁሉም የሰው ልጆች ሕይወት አካል ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ውድቀቶቻችን ፀጋ ሊያስገኙልን ይችላሉ። በተከታታይ ባይሆንም  ደስታ ያስገኛል ብለን ያሰብነው አንድ ነገር ቅዤት ወይም ጣዖት ሊሆንብን ይችላል። ጣዖት ማንኛውንም ነገር ከእኛ ይፈልጋሉ ፤ የእርሱ ባሪያዎች ያደርገናል በምላሹ ደግሞ ለእኛ የሚሰጡን ምንም ነገር የለም። በመጨረሻ ግን አቧራ ብቻ ትተው ይወድቃሉ። ውድቀት ምንም እንኳን ብዙ መከራ ቢያስከትልም ጣዖቶቻችን እንዲደመሰሱ የሚያደርግ ከሆነ ጥሩ ነገር ነው።አንድ ወጣት ሊያጋጥመው የሚችል ሌሎች ብዙ አካላዊ ወይም ሞራላዊ ሁኔታዎች አሉ። እንደ ሱሰኝነት ፣ ወንጀል፣ ድህነት ወይም ከባድ ህመም ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።  ስለእነዚህ ነገሮች እንድታስብ እና ለራሳችሁ ወይም ለእናንተ አሁን ወይም ከእዚህ ቀደም ቅርብ ለነበሩ ሰዎች ስለእነዚህ ነገሮች ታስቡ ዘንድ እጠይቃለሁ። በተመሳሳይ መልኩም ​​በወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ወጣት በእውነት ሞቷል (ሉቃስ 7፡14)፣ ነገር ግን በሕይወት እንዲኖር በሚፈልግ አንድ ሰው እንደታየ እንድታስታውሱ እጠይቃለሁ። ተመሳሳይ ነገር በየቀኑ በእኛም ላይ ሊከሰት ይችላል።

ርህራሄ እንዲኖር

ቅዱሳን መጽሐፍት ብዙውን ጊዜ የሌሎች ሰዎችን ሥቃይ በሚመለከቱበት ወቅት “በደመ ነፍስ” ስሜት ውስጥ ስለሚገቡ ሰዎች ይናገራሉ። የኢየሱስ ስሜቶች በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ እንዲሳተፍ ያደርጉታል። ህመማቸውን የእርሱ ሕመም ያደርጋቸዋል። የዚያ ወጣት ልጅ እናት ሐዘን የእርሱ ሐዘን እንዲሆን ያደርጋል። የዚህ ወጣት ልጅ ሞት የእሱ ሞት ሆነ።

ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን የመወደድ ተስጦ እና ችሎታ እንዳላችሁ በተደጋጋሚ አሳይታችኋል። ሁኔታዎች በሚጠይቁት መልኩ እና ጊዜ ሁሉ ሁላችሁም የፈጸማችሁት በጎ ተግባር እንዳለ አስባለሁ። ወጣት የበጎ ፈቃድ ስራ ተሳታፊ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም የጎርፍ አደጋ በሚደርስበት ወቅት እርዳት ማደረግ እጅግ በጣም ከባድ ይሆን ነበር። በአከባቢያችን ላይ እየደርሰ የሚገኘውን ከፍተኛ ጥፋት ለመከላከል በሚደርገው ጥረት ውስጥ ሰፊ የሆነ የወጣቶች እንቅስቃሴ ባይታከልበት ኖሮ የምድራችንን ጩኸት ለመስማት እዳጋች ይሆን ነበር።

ውድ ወጣቶች! በስሜታዊነት መንፈስ እንዳትወሰዱ ተጠንቀቁ! እየተሰቃዩ ያሉትን ሰዎች አቤቱታ ሁል ጊዜ በትኩረት ተከታተሉ፣ እናም በዚህ ዓለም ውስጥ በሚያለቅሱ እና በሚሞቱ ሰዎች እንድትነቃቁ ይሁን።  “አንዳንድ የህይወት እውነቶች በእንባ በነጹ ዓይኖች ብቻ ነው የሚታዩት” (ክርስቶስ ሕያው ነው ቁ. 76 ይመልከቱ) ። ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር ማልቀስ መማር ከቻላችሁ እውነተኛ ደስታ ታገኛላችሁ። ስለዚህ ብዙ የእናንት ዘመን  ሰዎች የጥቃት እና የስደት ሰለባዎች ናቸው። ቁስሎቻቸው የእናንተ ቁስል ይሁን፣  እናም በዚህ ዓለም ውስጥ የእነርሱ ተስፋዎች ትሆናላችሁ። ለወንድሞቻችሁ ወይም ለእህቶቻችሁ “ብቻችሁን አይደላችሁም እና ተነሱ!” ማለት ትችሉ ዘንድ፣ እናም እግዚአብሔር አብ እንደሚወደን፣ እኛን ለማሳደግ ኢየሱስ ለእኛ የሚዘረጋው እጁ መሆኑን እንዲገነዘቡ ትረዳላችሁ።

ወደፊት መምጣት እና በእርሱ “መንካት”

ኢየሱስ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን አስቆመው። ወደ እነርሱም ቀረበ፣ ይህም ተገባሩ እርሱ ለሁሉም ቅርብ መሆኑን ያሳያል። በዚህ መንገድ ያደርገው ቅርበት ሕይወትን ለመመለስ ደፋር ተግባር ይሆናል። የትንቢት ምልክት ነው። ህያው የሆነው የኢየሱስ ንክኪ ህይወትን ያስተላልፋል፣ መንፈስ ቅዱስን ወደዚያ ወጣት ሰው አካል ውስጥ አፍስሶ ወደ ሕይወት ያመጣ ንክኪ ነው።

ያ ንክኪ ሁሉንም የጎዳ እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ ይገባል። እሱ የእግዚአብሔር ንክኪ ነው፣ በእውነተኛ የሰዎች ፍቅርም የተነካ ነው ፣ ይህ ሊታሰብ የማይችል አዲስ የነፃነት እና የሙሉነት፣ እንከን የሌለበት ጣዕምን ያመጣል። ይህ የኢየሱስ ተግባር ውጤታማነት የማይካድ ነው። ምንም እንኳን አንድ የመቀራረብ ምልክት ቀለል ባለ መልኩ ነገር ግን ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ የትንሳኤ ኃይል ማስነሳት እንደሚችል ያስታውሰናል።

እናተም ወጣት እንደ መሆናችሁ መጠን ለሚያጋጥሟችሁ ህመም እና ሞት እውነታዎች መቅረብ ትችላላችሁ። እናተም እነሱን መንካት እና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና እንደ ኢየሱስ አዲስ ሕይወት ማምጣት ትችላላችሁ። ነገር ግን በመጀመሪያ በእርሱ ፍቅር ልትነኩ እና ልባችሁ እርሱ ለእናንተ ባዳርገው መልካም ነገር ተሞክሮ ተነክቶ ሲቀልጥ ብቻ ነው ይህንን ማደረግ የምትችሉ። ለሁሉም ህይወት ላለው ፍጡር ሁሉ እግዚአብሔር ያለውን ጥልቅ ፍቅር ሊሰማችሁ ከቻለ - በተለይም ረሃብ እና ጥማት ያጋጠማቸው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ የታመሙ፣ የታረዙ ወይም የታሰሩ ሰዎችን እርሱ ለእናተ ቅርብ እንደ ነበረ ሁሉ እናተም እነርሱን ወደ እርሱ ማቅርብ ትችላላችሁ። እንደ እሱ እነሱን መንካት እና ህይወታቸው በሐዘን ውስጥ ለሚገኙ፣ የሞቱ የሚመስሉ ሰዎችን እና ጓደኞቻችሁን ሳይቀር በእምነት እና በተስፋ ተሞልተው እንዲኖሩ ማድረግ ተችላላችሁ።

“አንተ ውጣት ተነስ እልሃለሁ!”

ናይን በመባል በሚታወቀው ስፍራ  ውስጥ ኢየሱስ ከሞት ያስነሳው ወጣት የነበረው ልጅ ስም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ አልተጠቀሰም። ይህ እያንዳንዱን አንባቢ ይህንን ታሪክ ከራሱ ጋር እንዲያቆረኘው ይጋብዛል። ለእያንዳንዳችን ኢየሱስ “ተነሱ” ብሏል። እኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በቋሚነት እንደምንወድቅና እንደገና መነሳት እንዳለብን እናውቃለን። በጉዞ ላይ ያልሆኑ ሰዎች በጭራሽ አይወድቁም፣ ከዚያም እንደገና ወደ ፊት መጓዝ አይችሉም።  ለዚያም ነው ኢየሱስ የሚሰጠንን እርዳታ መቀበልና በአምላክ ላይ እምነት መጣል ያለብን። የመጀመሪያው እርምጃ ራሳችንን ማንሳት እና ኢየሱስ የሰጠን አዲስ ሕይወት ጥሩ እና ለመኖር የሚያስችለን መሆኑን መገንዘባችን ነው። የወደፊቱ ጉዞአችን ከጎናችን በሚሆን አንድ ሰው ይደገፋል ። ይህንን ሕይወት ክብር ትርጉም ባለው መንገድ እንድንኖር ኢየሱስ ይረዳናል።

ይህ ሕይወት በእውነቱ የስነ-ልቦና ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አዲስ ፍጥረት ፣ አዲስ ልደት ነው። ምናልባትም ችግር በሚያጋጥመን ወቅቶች ሁሉ ተስፋ እደርጋለሁ ብዙዎቻችሁ ስምታችሁት ይሆናል “አስማታዊ” የሚመስሉ ቀመሮችን ቀምረው፣ ዛሬ ዘመናዊ በሚባል መልኩ የሆነ ነገር ይመስላል ሁሉንም ነገር የሚንከባከቡ የሚመስሉ ቀመሮችን “በራስህ ማመን አለብህ”፣ “ውስጣዊ የሆኑ ብቃቶችህን ማወቅ አለብህ”፣ “አዎንታዊ ኃይልህን በደንብ ማወቅ አለብህ”… በማለት ይናገራሉ። ነገር ግን እነዚህ ቃላት እንዲሁ ቃላቶች ብቻ ናቸው፣ እነሱ በእውነት "በውስጡ ለሞተ" ሰው ጠቃሚ አይደሉም። አይሰሩም ፡፡ የኢየሱስ ቃል ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው ፣ እሱ በጥልቀትይገባል፣  በጥልቀት ይሄዳል። ሙታንን ወደ ሕይወት ሊያመጣ የሚችል መለኮታዊ የሆነ እና አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ፈጣሪ የሆነ ቃል ነው።

አዲሱን ሕይወት “እንደ ተነሱ” ሆኖ መኖር!

ወጣቱ ልጅ “መናገር መጀመሩን” ቅዱስ ወንጌል ይገልጻል (ሉቃ 7፡ 15)። በኢየሱስ የተነኩ እና ወደ ሕይወት የተመለሱት ሰዎች በእነሱ ውስጥ ጥልቅ የሆነውን ነገር፣ ስብዕናቸውን፣ ፍላጎታቸውን እና ህልሞቻቸውን ወዲያውኑ ያለምንም ማመንታት ወይም ያለምንም ፍርሃት ይናገራሉ። ማንም ሊያስተውል የማይችል መስሎ ስለታያቸው ምናልባት ከዚህ በፊት ይህን ማድረግ ይችሉ ይሆናል።

መናገር ከሌሎች ጋር ግንኙነት መመስረት ማለት ነው። “ስንሞት” በራሳችን ውስጥ እንደተቀበርን እንቆያለን። ግንኙነቶቻችን ይፈርሳሉ፣ ወይም ውጫዊ፣ ሐሰተኛ እና ግብዝ ይሆናሉ። ኢየሱስ ሕይወታችንን መልሰን እንድናገኝ ስያደርገን ለሌሎች ይሰጠናል (ሉቃስ 7፡ 15)።

ዛሬ እኛ ብዙውን ጊዜ “የተገናኘን” ቢመስለንም ነርገ ግን አንነጋገርም። የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን አለአግባብ መጠቀማችን በተከታታይ በማያ ገጹ ላይ ተጣብቀን እንድንቆይ ያደርገናል። ወጣቶች “ተነሱ” በሚለው የኢየሱስ ትእዛዝ መሠረት ባህላዊ ለውጥን በማምጣት ከእናንተ ጋር መቀላቀል እፈልጋለሁ። ወጣቶች እንዲገለሉ እና ወደ ምናባዊ ዓለም እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ ባህል ውስጥ ያሉትን ሰዎች “ተነሱ!” የሚለውን የኢየሱስን ጥሪ እናሰራጭ። ከምናባዊነት እጅግ የላቀ የሆነውን እውነት እንድንቀበል ይጠራናል። ይህ ቴክኖሎጂን ማግለል አያካትትም፣ ይልቁንም ቴክኖሎጂ እንደ አንድ ግባት እንጂ እንደ መጨረሻው መንገድ እድርገን መውሰድ አይጠበቅብንም። በተጨማሪም “ተነስ!” የሚለው ቃል “ህልም” እንድናልም ይጋብዘናል፣ “የሚከስተውን አደጋ እንድንጋፈጥ”  “ዓለምን ለመለወጥ” ቁርጠኛ እንድንሆን፣ ተስፋዎቻችንን እና ምኞቶቻችንን እንደገና ለማደስ እና ሰማይን፣ ኮከቦችን እና በዙሪያችን ባለው ዓለም ላይ ለማሰላሰል የቀረበ ግብዣ ነው። “ተነስና የነበርከውን ሁን!” መልእክታችን ይህ ከሆነ፣ ብዙ ወጣቶች መሰልቸት እና ተስፋ መቁረጥ ያቆማሉ፣ እናም ፊታቸው ሕያው ይሆናል፣ ከማንኛውም ምናባዊ እውነታ የበለጠ ቆንጆ ይሆናል።

ሕይወት የምሰጥ ከሆነ ይህን ለመቀበል አንድ ሰው እዚያ ይኖራል። አንዲት ወጣት ሴት በአንድ ወቅት “አንድ የሚያምር ነገር ስታዩ ከአልጋችሁ ውስጥ ውጡና ተመሳሳይ ነገር አድርጉ፣ ተመሳሳይ ነገር ስሩ” ብላ ነበር። ውበት ስሜትን ያነቃል። እናም አንድ ወጣት ስለ አንድ ነገር መልካም ስሜት ካለው፣ ስለ አንድ ሰው በጣም የሚጓጓ ከሆነ እርሱ ይነሳል ፣ ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን ይጀምራል። ወጣቶች ከሙታን ይነሳሉ፣ ለኢየሱስ ምስክር ይሆናሉ፣ እናም ህይወታቸውን ለእርሱ ያኖራሉ።

ውድ ወጣቶች! ምኞቶቻችሁ እና ህልሞቻችሁ ምንድናቸው? በመንፈሳዊው ዓለም፣ በኪነ-ጥበቡ ወይም በኅብረተሰቡ ውስጥ ቢሆን ነፃ ዓለም በመስጠት በእነሱ አማካኝነት ለዓለም ፣ ለቤተክርስቲያኗ እና ለሌሎች ወጣቶች አንድ የሚያምር ነገር ስጡ። በአንድ ወቅት በእናቴ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የተናገርኩትን እደግማለሁ! “ድምጾቻችሁ እንዲሰሙ አድርጉ!” “ኢየሱስ ስለራሱ ብቻ የሚጨነቅ ቢሆን ኖሮ የመበለቲቱ ልጅ ከሞት አይነሣም ነበር” ብሎ የተናገረ ሌላ ወጣት አስታውሳለሁ!

የዚያ ወጣት ልጅ ትንሣኤ ለእናቱ እፎይታን ሰጥቱዋል። በዚያች ሴት ውስጥ የአለም ወጣቶች ሁሉ አደራ የተሰጣትን የማርያምን ምስል ማየት እንችላለን። በእሷ ውስጥ ያለ ምንም ልዩነት በሞቀ ፍቅር ለመቀበል የምትፈልገውን ቤተክርስቲያን እንደ ምትገኝ እንገነዘባለን። ስለዚህ ለሞቱ ልጆቿ እናት እንድትሆን ፣ እያለቀሰች ወደ ሕይወት እንድትመልሳቸው ለመጠየቅ ማርያም ለቤተክርስቲያን እንድታማልድ እንጠይቅ። በሚሞቱ እያንዳንዱ ልጆቿ ውስጥ ቤተክርስቲያኗም ትሞታለች፣ እናም በሚነሱ እያንዳንዱ ልጆቿ ቤተክርስቲያን ትነሳለች።

ጉዞዎዎቻችሁን እባርካለሁ።  ለእኔ መጸለይ እንዳዘነጉ አመሰግናለሁ።

ከቅዱስ ዩሐንስ  ላተራን ባዚሊካ፣ እ.ኤ.አ. የካቲት 11 ቀን 2020 ዓ.ም የእመቤታችን ሉርድ ማርያም መታሰቢያ በዓል በተከበረበት ወቅት የተላለፈ መልእክት።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

23 November 2020, 11:59