Vatican News
ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት  (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ጸሎት እንድንረጋጋ ያረጋጋል፣ ልብን ለእግዚአብሄር ይከፍታል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በሕዳር 09/2013 ዓ.ም  ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ” (ሉቃስ 2) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ጸሎት እንድንረጋጋ ያረጋጋል፣ ልብን ለእግዚአብሄር ይከፍታል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረነው የነበረውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ድንግል ማርያም የፀሎት ሰው እንደ ነበረች እንመለከታለን። ዓለም ስለ እርሷ ምንም ባላወቀበት በእዚያን ጊዜ፣ እንደ ማነኛውም ሰው የዳዊት ዘር ለሆነው ሰው የታጨች ልጃገረድ በነበረችበት በእዚያን ወቅት ማርያም ትጸልይ ነበር። ከናዝሬት ከተማ የተገኘች ልጃገረድ በቅርቡ ተልእኮን ከሚሰጣት ከእግዚአብሄር ጋር በተከታታይ በመወያየት በዝምታ ተጠምዳለች ብለን መገመት እንችላለን። ከተፀነሰችበት ጊዜ አንስቶ ቀድሞውኑ በፀጋ እና በንፅህና የተሞላች ናት ፣ ነገር ግን ስለ አስገራሚው፣ ያልተለመደ ጥሪዋ እና መሻገር ስለሚገባት ማዕበል ገና ምንም የምታውቀው ነገር የለም። አንድ ነገር እርግጠኛ ነው -ማርያም ታዋቂ የታሪክ ጸሐፊዎች በመጽሐፎቻቸው ውስጥ በጭራሽ ያላካተቱት ፣ ነገር ግን ለልጁ መምጣት እግዚአብሔር ያዘጋጀው ትሁት የሆነ ልብ ነበራት።

ማርያም ሕይወቷን ብቻዋን ሁና አልመራችም፣ የመንገዶቿን መስመር ወስዶ ወደ ሚፈልገው ቦታ እንዲመራው እግዚአብሔርን ትጠብቃለች። እርሷ የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም የተዘጋጀች ናት ፣ ዝግጁ በመሆኗ እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ በሚሳተፍባቸው ታላላቅ ዝግጅቶች ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ ናት። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በኢየሱስ የሕይወት ዘመን ሁሉ የአባቱን መልካም ፈቃድ እየፈጸመች እንደኖረች ያስታውሳል (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2617-2618  ይመልከቱ)።

የመላእክት አለቃ የሆነው መልአኩ ገብርኤል የምስራቹን ቃል ሊያበሥራት ወደ ናዝሬት በመጣ ጊዜ ማርያም እየጸለየች ነበር። የእሷ ትንሽ የሚመስል ሆኖም ግዙፍ የሆነው “እነሆኝ” የተሰኘው ቃል በዚያ ጊዜ ሁሉም ፍጥረታት በደስታ እንዲዘሉ ያደረገ፣ በእርሱ በመታመን ብዙ “እነሆኞች” እንዲከሰቱ በማድረግ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ያስገዙ ብዙ ሰዎች በደህንነት ታሪክ ውስጥ እንዲነሱ አድርጓል። ራስን በፈቃደኝነት አስተሳሰብ ውስጥ ከማስቀመጥ የበለጠ ለመጸለይ ምንም የተሻለ መንገድ የለም- “ጌታ ሆይ ፣ ምን እንደምትፈልግ ፣ መቼ እንደምትፈልግ እና እንዴት እንደምትፈልግ” እባክህን ንገረኝ ልንለው ይገባል። ስንት አማኞች ናቸው በእዚህ መልኩ የሚኖሩት! ቀኖቻቸው በችግር ሲሞሉ እንኳን አይበሳጩም ፣ ግን እውነታውን በመጋፈጥ እና በእያንዳንዱ ሁኔታ በሚቀርበው ትህትና እና ፍቅር የእግዚአብሔር ጸጋ መሳሪያዎች እንደሆንን እያወቁ ይሄዳሉ።

ጸሎት የመረበሽ ስሜትን እንዴት እንደሚረጋጋ ያውቃል፣ ዝግጁዎች ሆነን እንድንገኝ እንዴት እንደሚለውጠን ያውቃል። በእነዚያ የምስራች ቃል በተነገረበት ጥቂት የግልጸት ጊዜያት ውስጥ ድንግል ማርያም “እነሆኝ” በማለት ቃሉን ስትቀበል እጅግ በጣም ከባድ ፈተናዎች እንደሚያመጣባት እየተገነዘበች እንኳን ፍርሃትን እንዴት እንደምትቀበል ታውቅ ነበር። በጸሎት ውስጥ እግዚአብሔር የሚሰጠው እያንዳንዱ ቀን ጥሪ መሆኑን ከተረዳን፣ ከዚያ ልባችን ይሰፋል እናም ሁሉንም ነገር እንቀበላለን። “ጌታ ሆይ የምትፈልገውን ነገር ምንድነው። በመንገዴ ሁሉ ላይ እንደምትገኝ ቃል ግባልኝ” ብለን እንዴት እንደ ምንናገር እንማራለን።

ማርያም እስከ ኢየሱስ ሞት እና ትንሣኤ ድረስ እስከ መላው የኢየሱስ ሕይወት ድረስ በጸሎት ታጅባ ነበር፣ በመጨረሻም ፣ ገና ወጣት የነበረችውን ቤተክርስቲያን የመጀመሪያ እርምጃዎችን አጅባ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 1፡14 ይመልከቱ)። የመስቀልን መከራ ከተመለከቱት ደቀ መዛሙርት ጋር ጸልያላች። በፍርሃት ተሸንፎ ከነበረው ከጴጥሮስ ጋር ጸልያለየች፣ እንዲጸጸት አድርጋለች። ማርያም የልጇን ማህበረሰብ እንዲመሰርቱ ከተጠሩ ወንዶችና ሴቶች መካከል ነበረች። አብራቸው ስለእነሱም ጸልያለየች። እናም እንደገና የመጪው ጊዜ እንኳን ሳይቀር መልካም ፍጻሜ እንዲኖረው ትጸልያለች፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ አማካይነት የእግዚአብሔር እናት ሆነች ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራም የቤተክርስቲያን እናት ሆነች። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ይህንን በተመለከተ ሲያብራራ “የእግዚአብሔር ስጦታ ከዘመን መጀመሪያ አንስቶ ይጠባበቀው የነበረውን ተቀባይነት ያገኘው በትሁቷ አገልጋይ እምነት ነው” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2617) ይለናል።

በድንግል ማርያም ውስጥ ተፈጥሮአዊ የሴቶች ውስጣዊ ግንዛቤ የምናገኝ ሲሆን ይህም ከእግዚአብሄር ጋር በጸሎት መተባበር ነው። ለዚህ ነው ቅዱስ ወንጌልን በማንበብ አንዳንድ ጊዜ የሚጠፋ መስሎ የሚታየውን እናስተውላለን ፣ በወሳኝ ጊዜያት የእርሷን ልብ እና እርምጃ የሚመራው የእግዚአብሔር ድምጽ ነበር። ለምሳሌ በቃና ዘገሊላ በተደረገ ሠርግ ላይ ኢየሱስ ክብሩን የገለጠበትን የመጀመሪያዎቹን “ተአምር” በፈጸመበት ወቅት (ዮሐ 2፡1-12 ይመልከቱ)፣ ወይም በመጨረሻው ሰዓት በመስቀል ስር ሆና በሀዘን እና በፍቅር ከእርሱ ጋር ነበረች (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2618 ይመልከቱ) ።

“ማርያም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በልቧ እያሰላሰለች ትጠብቅ ነበር” (ሉቃ 2፡19)። ስለዚህ ወንጌላዊው ሉቃስ በወንጌሉ ውስጥ የኢየሱስን መወለድ በገለጸበት ወቅት የጌታን እናት ያሳያል። በዙሪያዋ የሚከናወኑ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ሁሉንም ነገር በልቧ ውስጥ ትይዘው ነበር፣ በደስታ የተሞሉ ቀናት ፣ እንዲሁም ቤዛችን በየትኞቹ መንገዶች ማለፍ እንዳለበት በተረዳችበት በእነዚያ የጨለማ ጊዜያት እንኳን ሁሉንም ነገር በልቧ ትይዘው ነበር። በጸሎት ወንፊት ውስጥ እንዲያልፍ እና በእሱ እንዲለወጥ ሁሉም ነገር በልቧ ውስጥ ትይዘው ነበር፣ ሰባሰገል ስጦታዎችን ባመጡበት ወቅት ይሁን ወይም ወደ ግብፅ በተሰደዱበት ወቅት ፣ በልጇ ላይ መከራ አስከተፈጸበት ስቅለተ አርብ እለት ድረስ ሁሉንም ነገር በልቧ ይዛ ነበር። እናት ሁሉንም ነገር በልቧ ይዛ ከእግዚአብሄር ጋር ለመወያየት ትሄዳለች። አንድ ሰው የማርያምን ልብ በጸሎት ባሰላሰሉበት ወቅት በኢየሱስ ምስጢሮች አማካኝነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ በትዕግሥት በመቀበል የተፈጠረ እና ከማነኛውም የሚያንጸባርቅ ዕንቁ ጋር ሊስተካከል የማይችል ክብር ያለው ልብ ነው ብሎ ነበር። እኛም እንደ እናታችን ብንሆን ምንኛ መልካም ነበር!

18 November 2020, 12:27