ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “መክሊታቸውን በበጎ ነገር ላይ ያዋሉ ሰዎችን እግዚአብሔር ይሸልማቸዋል” አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት እሁድ ሕዳር 06/2013 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ በተጠቀሰውና “የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ” (ማቴ 25፡14-30) የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ ማደረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “የተሰጣቸውን መክሊት ለመልካም አገልግሎት ያዋሉትን ሰዎች እግዚአብሔር ይሸልማቸዋል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቀራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህንን ምሳሌ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረው ቆይታ በመጨረሻው ዘመን ከተቀበለው ከህማሙ ፣ ከሞቱ እና ከትንሳኤው በፊት ይህንን ምሳሌ ማናገሩን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ገልጸዋል።

ለእያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው ይሰጣቸዋል

“ምሳሌው የሚያመለክተው ጌታቸው ብዙ ገንዘብ በአደራ የተሰጣቸውን ሦስት አገልጋዮችን ነው ፣ እርሱም ወደ አንድ ሩቅ አገር ለመሄድ ይነሳል” በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በምሳሌው ላይ ጌታው ለእያንዳንዱ አገልጋዮች የሚሰጣቸው “እንደየችሎታቸው” እንደ ነበረ ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው እንደ ገለጹት “ጌታ ለሁላችን የሚሰጠው ስጦታ ከአቅማችን እና ከችሎታችን ጋር የተመጣጠነ አንደ ሆነ” ያብራሩ ሲሆን እግዚአብሔር “በደንብ ያውቀናል፣ እኛ ሁላችንም እኩል እንዳልሆንን ያውቃል፣ እናም ሌሎችን ለመጉዳት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር አይሰጣቸውም፣ ነገር ግን ለእያንዳንዱ እንደየ አቅሙ መክሊቶችን  በአደራ ይሰጣል” ብለዋል።

ጌታው ሲመለስ እና ለአገልጋዮቹ በአደራ የተሰጣቸውን ገንዘብ እንዲመልሱ ከተጠሩ ሁለት አገልጋዮች “የድካማቸውን መልካም ፍሬ” ያቀርባሉ እናም በጌታው ይመሰገናሉ፣ ሦስተኛው ግን መክሊቱን የሸሸገው በጌታው የተወገዘ ሲሆን በእዚህ ምክንያት ከጌታው ቤት እንደ ተባረረ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ስጦታችንን ለመልካም መጠቀም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስተንትኖዋቸውን በቀጠሉበት ወቅት አክለው እንደ ገለጹት “ይህ ምሳሌ ሁሉንም የሚመለከት ምሳሌ ነው፣ ነገር ግን እንደ ሁልጊዜው ይህ ምሳሌ በተለይ ክርስቲያኖችን ይመለከታል” ማለታቸው የገለጸ ሲሆን አክለውም በተለይ ዛሬ (ሕዳር 06/2013 ዓ.ም) የአለም የድሆች ቀን በሚከበርበት እለት ቤተክርስቲያን እያንዳንዱን እጃችንን ወደ ድሆች መዘርጋት ተገቢ እንደ ሆነ ታሳስበናለች” ብለዋል።

ሁላችንም የተለያዩ ችሎታዎች ተሰጥቶናል - እናም “እነዚህ ስጦታዎች ለእግዚአብሄር፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አገልግሎት ለመስጠት በዚህ ሕይወት ውስጥ መልካም ለማድረግ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው” ብለዋል።

ለድሆች ትኩረት ይስጡ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉም ሰዎች በአሁኑ ወቅት በቁጥር እጅግ ብዙ የሆኑ ድሆችን እንዲመለከቱ ያሳሰቡ ሲሆን “በከተሞቻችን እምብርት ውስጥ እንኳን በጣም ብዙ ረሃብ አለ” ብለዋል። “ብዙውን ጊዜ ወደ ግድየለሽነት አስተሳሰብ ውስጥ እንገባለን ፣ ድሃው ሰው እዚያ አለ ግን በተቃራኒው እንመለከታለን” በማለት የገለጹ ሲሆን ይልቁንም “እጆቻችንን ለድሆች መዘርጋት ይኖርብናል፣ በእነርሱ ውስጥ ክርስቶስ ይኖራል” ብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አክለው እንደ ገለጹት ኢየሱስ ከድሆች ጋር እንድንነጋገር አስተምሮናል፣ እርሱ የመጣው ለድሆች እንደ ሆነ” በመግለጽ አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመልካም ሥራ ተግባር አብነት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም የእርሷን ምሳሌ በመከተል መልካም ተግባራትን ማከናውን እንድንችል፣ እርሷ “ኢየሱስን ታላቅ ስጦታ ተቀብላለች ፣ ነገር ግን ለራሷ ብቻ ይህንን ስጦታ አልተጠቀመችም፣ ለዓለም ሁሉ ስጦታ አድርጋ እንዳቀረበች ሁሉ እኛም የተሰጡንን ምክሊቶች ከሌሎች ጋር መጋራት እንችል ዘንድ እና ፍሬያማ አንድናደርጋቸው “እጃችንን ወደ ድሆች ለመዘርጋት ከእሷ መማር እድንችል” ትረዳን ዘንድ አመላጅነቷን መማጸን ይኖርብናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የእለቱን አስተንትኖ አጠናቀዋል።፡

15 November 2020, 12:18