2020.10.14 Udienza Generale 2020.10.14 Udienza Generale 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ደንቦችን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን ወረርሽኙን ማስወገድ ይቻላል”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅምት 4/2013 ዓ. ም በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመስብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን ከፈጸሙ በኋላ ሰላምታቸውን አቅርበዋል። በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቀነስ የሚያስችሉ መንገዶችን፣ ከእነዚህም መካከል ማሕበራዊ ርቀት ማክበር እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። በአዳራሹ ውስጥ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የሚለዋወጡትን ሰላምታ፣ እንደተለመደው ወደ ምዕናኑ መካከል ሄደው ለማድረግ ምኞት ቢኖራቸውም፣ ወረርሽኙ በመስፋፋት ላይ መሆኑ እየተነገረ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ይህን ለማድረግ ባለመቻላቸው ይቅርታን ጠይቀዋል። በወረርሽኙ ለተጠቁትም ጭምር ሰላምታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር ማሕበራዊ ርቀትን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ወረርሽኙን መከላከል እንዲቻል ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት እና ከጤና ባለሞያዎች የሚሰጡትን ደንቦችን እና ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ወረርሽኙን ማስወገድ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። 

ቅዱስነታቸው በማስከተልም ከጣሊያን እና ከተለያዩ አገራት ለምጡት ዕመናን እና ነጋድያን ሰላምታቸውን አቅርበው፣ በተለይም በተለያዩ ባሕሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙት ማኅበራት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። ቀጥለውም በፖርቱጋል አገር ማኅበራቸውን ለመጀመር የተዘጋጁ መነኩሳትን፣ የ”NATO” ወታደራዊ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና በቅርቡ ምስጢረ ተክሊል ሥርዓትን የፈጸሙ ወጣቶችን በማስታወስ፣ በእግዚአብሔር እገዛ እና ከመንፈስ ቅዱስ በሚያገኙት የአእምሮ እና የልብ መረጋጋት  የሰላም መሣሪያ እንዲሆኑ ተመኝተውላቸዋል።

ቀጥለውም አረጋዊያንን፣ ወጣቶችን፣ ሕሙማንን እና ጋብቻቸውን በቅርቡ የፈጸሙ ባለትዳሮችን አስታውሰው፣ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ የቅዱስ ወንጌል ጥበብ እንዲያድግ፣ የኢየሱስን መልካም ዜናን በመስማት፣ እርሱ የሚሰጠውን የሕይወት እንጀራን በመመገብ፣ ዘወትር የእውነት ምስክሮች በሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

14 October 2020, 14:46