ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ዝግጅት እንዲደረግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ መስከረም 10/2013 ዓ. ም ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ካጠናቀቁ በኋላ በያዝነው መስከረም ወር በምሥራቅ አውሮጳ አገር ሃንጋሪ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሚቀጥለው ዓመት ማለትም መስከረም 2/2014 ዓ. ም. የተላለፈውን 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤን፣ ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ በመንፈስ ተባብረው እንዲያስቡት አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር አያያዘው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ቀንን በማስታወስ፣ አዲሱ ትውልድ ስለ ሰብዓዊ ክብርና ስለ ጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚሰጠውን እንክብካቤ እና ጥበቃ በሚገባ አውቀው እንዲያድጉ አሳስበዋል።

ወደ ፊት ሊካሄድ የታቀደውን ዓለም አቀፉ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤን በማስታወስ ለሃንጋሪ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን አባቶችና ምዕመናን በላኩት የሰላምታ መልዕክታቸው፣ ይህን ታላቅ የቤተክርስቲያን ጉባኤን በእምነት ይጠባበቁ እንደነበር አስታውሰው፣ የሃገሪቱ ካቶሊካዊ ምዕመናን በመንፈስ በመተባበር፣ ቅዱስ ቁርባን የሕይወት እና የቤተክርስቲያን ተልዕኮ መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ አሁን የምንገኝበት ጊዜ የማይፈቅድ ቢሆንም በሚቀጥለው ዓመት ለሚደረገው ታላቅ ጉባኤ ዝግጅት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

መስከረም 10/2013 ዓ. ም. በጣሊያን የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ቀን መታሰቢያ ዕለት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ ከፍተኛ የባሕል ማዕከል፣ ለበርካታ ወጣት ተማሪዎች የወደ ፊት መልካም ሕይወት በር ከፋች መሆኑን በመገንዘብ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ አዲሱ ትውልድ ለሰብዓዊ ክብርና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ሊሰጥ ስለሚገባው እንክብካቤ እና ጥበቃ በሚገባ አውቀው ማደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።  

21 September 2020, 11:21