ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ፥ “የሕዝብ ሰላማዊ ጥያቄ ተደማጭነት ሊኖረው ይገባል”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሁድ መስከረም 3/2013 ዓ. ም ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ካጠናቀቁ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት፣ ከጣሊያን እና ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡት ምዕመናን አጭር ንግግር አሰምተው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው፣ በቅርቡ የግሪክ ደሴት በሆነችው በሌስቦ በሚገኝ፣ ሞርያ የስደተኞች መጠለያ ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ፣ በመጠለያው የሚኖሩ፣ በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያለ መጠለያ ማስቀረቱን አስታውሰዋል። እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም. በግሪክ ዋና ከተማ አቴን ተገኝተ፣ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርስ ቤርተለሜዎስ እና ከሊቀ ጳጳስ ብጹዕ የሮኒሞስ ጋር ሆነው፣ ወደ ግሪክ ለተሰደዱት ስደተኞች እና በአውሮጳ ውስጥ ጥገኝነትን ለሚጠይቁ ስደተኞች፣ ክብራቸውን የጠበቀ፣ ምቹ የስደተኞች መኖሪያ ቦታ በአውሮጳ አገሮች ውስጥ እንዲመቻች መጠየቃቸውን አስታውሰዋል። ከዚህም አያይዘው በአደጋው የተጎዱትን እና ባሁኑ ጊዜ በመጠለያ እጦት በችግር ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው እና ከጎናቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ከዚህም በተጨማሪ በእነዚህ ሳምንታት፣ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች በመደረግ ላይ ያሉትን ሕዝባዊ ሰልፎችን አስታውሰው፣ የሰልፎቹ ምክንያት የሆነው እና እያደጉ የመጡት ማኅበርዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች መሆናቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው እነዚህ ሕዝባዊ ሰልፎች አመጽን እና ተጨማሪ ቀውሶችን ሳያስከትሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄዱ ጠይቀው፣ ሕዝቡ ብሶቱን በሰላማዊ መንገድ ሃላፊነትን ወደተሸከመው የመንግሥት አካላት እንዲያቀርብ፣ ለሰብዓዊ መብት እና ለሕዝቦች ነጻነት አስፈላጊው ክብር ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ለክርስቲያን ማኅበረሰብ በላኩት መልዕክታቸው፣ ሕዝባዊ አለመረጋጋት በማይታይባቸው አገራት የሚኖሩ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች፣ ከሐይማኖት መሪዎቻቸው ጋር በመተባበር፣ ከሁሉ በላይ ይቅርታን በማድረግ እርቅን ለሚያመጣ የጋራ ውይይት ቅድሚያን መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዓለማችንን እያስጨነቀ የሚገኘውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየዓመቱ ከምዕመናን በኩል ለቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ተብሎ የሚሰበሰብ የገንዘብ ዕርዳታ፣ እግዚአብሔር ስጋን በመልበስ ራሱን በገለጸባት፣ ለእኛ ሲል ሞቶ ትንሳኤውን በገለጠባት በቅድስት አገር ኢየስሩሳሌም ለሚኖሩ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የወንድማማችነት መግለጫ እና የተስፋ ምልክት መሆኑንም አስረድተዋል። በመዝ. 87:7 ላይ “የበረከታችን መገኛ ጽዮን ናት” የሚለውን በመጥቀስ ኢየሩሳሌምን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ በሃሳብ ብቻ መንፈሳዊ ጉዞን ወደ ኢየሩስሌም በማቅናት በዚያ ለሚገኝ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የቸርነት ሥራን እናድርግ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡት ምዕመናን በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ በየዕለቱ ለሚያቀርቡት ሐዋርያዊ ምስክርነት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ለተሰኘ እንቅስቃሴ አባላት ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ተፈጥሮ በመንከባከብ ለሚያርጉት አገልግሎት አመስግነዋቸዋል። በነሐሴ ወር ውስጥ ወደ ሮም ለመጡት ነጋዲያን መልካም መስተንግዶ ላደረጉት የሮም ምዕመናን ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው መልካም ዕለተ ሰንበትን ከተመኙ በኋላ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት የዕለቱን ንግግራቸውን ደምድመዋል።      

14 September 2020, 11:02