ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ገንዘብ ተልእኮን ልያስፈጽም የሚችል መሳሪያ ነው እንጂ በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 20/2012 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን እጅግ በጣም እያስጨነቃት በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ በጣም ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለማጽናናት ይረዳ ዘንድ በማሰብ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ዐብይ አርዕስት ከጀመሩት አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዛሬው እለት ባደረጉት የክፍል አራት አስተምህሮ “ንብረት እና ገንዘብ ተልእኮን ልያስፈጽም የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው እንጂ በራሳቸው የመጨረሻ ግብ አይደሉም”  ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ወረርሽኙ ባስከተለው ጣጣ እና ወረርሽኙ ባስከተለው ማህበራዊ መዘዝ የተነሳ ብዙዎች ተስፋ የማጣት አደጋ ተደቅኖባቸዋል። አለመረጋጋት እና ጭንቀት በሞላበት በዚህ ሰዓት ሁሉም ከክርስቶስ የሚመጣውን የተስፋ ስጦታ እንዲቀበሉ እጋብዛለሁ። በመጨረሻ መድረሻችን ላይ የመጨረሻ ቃል የሌላቸውን የሕመም ፣ የሞት እና የፍትህ ጥማት ውጣ ውረድ እንድንጓዝ የሚረዳን እርሱ ነው።

የበሽታው ወረርሽኝ ከሁሉም በላይ የእኩልነት ችግሮች የሆኑትን ማህበራዊ ችግሮች አጋልጧል እንዲሁም አስከፊ እንደ ሆኑ አሳይቷል። አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው ሁነው ሊሠሩ ይችላሉ ፣ ይህ ግን ለብዙዎች የማይቻል ነው። የተወሰኑ ልጆች ምንም እንኳን የተሳትፎ ችግሮች ቢኖሩም ፣ መደበኛ ትምህርት ማግኘታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ ፣ ይህ ግን በአጋጣሚ ለብዙዎች በድንገት የተከሰተ በመሆኑ እድሉን ለማግኘት ይቸገራሉ። አንዳንድ ኃያላን አገራት ቀውሱን ለመቋቋም ገንዘብ መስጠት ይችላሉ ፤ ይህ ግን የወደፊቱን ማሕበረሰብ ባለ እዳ ያደርጋል።

እነዚህ የእኩልነት እጦት እና ተመጣጣኝ ይልሆነ ሕይወት ምልክቶች ማህበራዊ በሽታን ያመለክታሉ፣ ከአንድ ከታመመ ኢኮኖሚ የሚመጣ ቫይረስ ነው። መሠረታዊ የሰው ልጆችን እሴቶች የሚያቃልል እኩል ያልሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ፍሬ ነው። በዚህ ዓለም ውስጥ በጣሚ ጥቂት የሆኑ ሐብታሞች የአብዛኛውን ሕዝብ ሐብት ተቆጣጥረው ይገኛሉ። ይህ ወደ ሰማይ የሚጮህ ኢፍትሐዊነት ነው! በተመሳሳይ መልኩም ይህ የኢኮኖሚ መዋቅር በጋራ ቤታችን ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ግድየለሽ ነው። ለእኛ አጅግ ቅርብ የሆነች እና የምንኖርባት አስደናቂ የሆነች ምድራችን  ከባድ እና ለመቀልበስ አዳጋች የሆነ  አደጋ እየተጋረጠባት ይገኛል፣ የብዝሀ ሕይወት መጥፋት እና የአየር ንብረት ለውጥ እስከ የባህር ጠለል መጨመር እና ሞቃታማ አከባቢዎች ላይ የሚገኙ ደኖችን አስከማጥፋት ደረጃ ደርሷል። ማህበራዊ እኩልነት አለመኖር እና በአከባቢ ላይ እየደረሰ የሚገኘው ውድመት አብረው የሚሄዱ እና አንድ ዓይነት ስር መሰረት አላቸው፣ በወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ የበላይነት ለማሳየት፣ ተፈጥሮን እና እግዚአብሔር ራሱ ለመቆጣጠር እና የበላይ ለመሆን የመፈለግ ኃጢአት። ነገር ግን ይህ የፍጥረታት እቅድ አይደለም።

“በመጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር ምድርንና የያዘቻቸውን ሃብቶች የሰው ልጅ በጋራ እንዲጠቀምባቸው፣ በሥራ አማካይነት እንዲቆጣጠራቸው ፍሬዎቻቸውን እንዲበላ በአደረራ ሰጠው” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2402)። እግዚአብሔር በስሙ ምድርን እንድንገዛ ጠርቶናል (ዘፍ. 1፡28 ተመልከት) ፣ እንደ አትክል ሥፍራ አድርገን እንድንተክል እና እንድንከባከባት እና እንድናቆያ ሰጠን (ዘፍ 2፡15 ተመልከቱ)። “መትከል” ማለት እርሻን  ማረስ ወይም መስራት  ማለት ሲሆን “ማቆየት” ማለት መንከባከብ፣መከላከልን ፣ መቆጣጠርን እና መጠበቅን  ያመለክታል። ነገር ግን በምድር ላይ የፈለኩትን ማደረግ እችላለሁ በሚለው አስተሳሰብ እንዳይተረጎም መጠንቀቅ ይኖርብናል። በፍጹም እንዲህ ማደረግ አይገባም፣ በራሳችን እና በተፈጥሮ መካከል “የእርስ በርስ የመተሳሰር ግንኙነት” አለ። ከፍጥረት እንቀበላለን እኛም በምላሹ ለፍጥረት እንመልሳለን። እያንዳንዱ ማህበረሰብ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ከምድር ጸጋ ሊወስድ ይችላል ፣ ነገር ግን መሬትን የመጠበቅ ኃላፊነትም አለበት ”።

በእርግጥ ምድር “ከእኛ በፊት ነበረ ፣ ለእኛም ተሰቶናል”፣ “ለሰው ልጆች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው። እናም ስለዚህ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ፍሬው ለሁሉም ሰው መዳረሱን ማረጋገጥ የእኛ ግዴታ ነው። ከምድራችን ሐብት ጋር ያለን ግንኙነት ቁልፍ ነገር ነው። በሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ወቅት የነበሩ አባቶች እንዳስታወሱት “ሰው ነገሮችን በሚገለገልበት ወቅት የግሉ የሆኑ ውጫዊ መገልገያዎች በሕጋዊ መንገድ የእርሱ ቢሆኑም እንኳን እርሱን እንደሚጠቅሙት ሁሉ ሌሎችንም እንዲጠቅሙ በማሰብ የእርሱ የራሱ ብቻ ሳይሆን የጋራ እንደሆኑ አድርጎ ማየት ይኖርበታል” በማለት ወደንገጋቸው ይታወሳል።  በእርግጥ “የየተኛውም ንብረት ባለቤትነት ባለ መብቱን የአምላክ አቃቤ ያደርገዋል፣ ንብረቱን የሚያለማ እና ጥቅሙንም ለሌሎች በተለይ መጀመሪያ ለቤተሰቡ የማካፈል ኃላፊነት ይሰጠዋል” ((የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2404)።

እኛ ያለን ንብረት ከህብረተሰቡ እሴት ጋር  መመጣጡን ለማረጋገጥ “የፖለቲካ ስልጣን ለጋራ ጥቅም ሲባል የባለንብረትነትን መብት አተገባበር የመቆጣጠር ኃላፊነት እና መብት አለው” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2406)። “የግለሰቦችን ንብረት ለአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተደራሽ ማድረጉ […] የማኅበራዊ ሥነ ምግባር ወርቃማ ደንብ እና የመላው ሥነ ምግባር እና ማህበራዊ ስርዓት የመጀመሪያ መርህ ነው” ።

ንብረት እና ገንዘብ ተልእኮን ሊያስፈጽሙ የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው። ሆኖም ግን እኛ በቀላሉ የግለሰብ ወይም የጋራ የመጨረሻ ግብ እንደ ሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። እናም ይህ በሚሆንበት ጊዜ ፣ ​​መሰረታዊ እና አስፈላጊ የሆኑ የሰዎች እሴቶች ይነካሉ። የሰው ሰብዓዊ ክብር ወደ ኢኮኖሚያዊ ክብር ይቀየራል ማለት ነው፣ ይህ ማለት ግለሰባዊነት ፣ ስሌት እና የበላይነትን መፍጠር ማለት ነው። በእግዚአብሔር አምሳያ እና መልክ በመፈጠራችን እኛ ማፍቀር የምንችል ከፍተኛ ችሎታ ያለን ማህበራዊ ፣ የፈጠራ ችሎታ ያለን እና ጠንካራ ፍጡራን መሆናችንን እንዘነጋለን። በእውነቱ ፣ ከሁሉም ዝርያዎች መካከል እኛ በጣም መተባበር የምንችል ፍጡራን ነን፣ እናም በቅዱሳን ሕይወት ልምድ እንደ ምንመለከተው በህብረተሰቡ ውስጥ እድገት እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን።

ነገሮችን ለማጋበስ እና ለመቆጣጠር የምናሳየው ዝንባሌ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዳያገኙ ያደርጋል፣ ኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ያልተመጣጠነ ከሆነ ማሕበራዊ መስተጋብራችን ይበጣጠሳል፣ ባልተገደበ የቁሳዊ እድገት ላይ ጥገኛ ስንሆን የጋራ ቤታችንን አደጋ ላይ ሲጥል ያን ጊዜ ነገሩን እንዲያው በቸልታ ማለፍ አንችልም። ይህ አስጨናቂ ነው። ትኩረታችን በኢየሱስ ላይ ሲወሰን (ዕብ 12፡2) እና ፍቅሩ በደቀ መዛሙርቱ ማህበረሰብ በኩል እንደሚሰራ እርግጠኛ ስንሆን ፣ አንድ የተለየ እና የተሻለ ነገር ለማምጣት በተስፋ ሁላችንም አንድ ላይ መስራት አለብን። በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ የክርስትና ተስፋ መልህቃችን ነው። ሁሉንም ነገር ለማካፈል ፍላጎቱ እንዲኖረን ያደርገናል፣ እንደ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ተልዕኳችንን ያጠናክርልናል፣ ያለንን ነገር ሁሉ ከሌሎች ጋር መካፈል እንችላለን ማለት ነው።

የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ይህንን ተረድተዋል። እንደ እኛ አስቸጋሪ ጊዜያት ኖረዋል። አንድ ልብ እና ነፍስ እንደመሰረቱ ስለሚያውቁ በእነሱ ውስጥ ያለውን የክርስቶስ ብዙ ጸጋ በመመስከር ንብረታቸውን ሁሉ ከሌሎች ጋር ይካፈሉ ነበር (ሐዋ. 4፡32-35 ይመልከቱ)። ለ 21ኛው ክፍለዘመን የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ይህንን እውነታ እንዲረዱት በማደረግ የጌታን ትንሳኤ መመስከር ይገባል። ፈጣሪ የሚሰጠንን ነገሮች የምንከባከብ ከሆነ ፣ ያለንን ሁሉ ማንም በማይጎዳ መንገድ አንድ ላይ የምንጠቀም ከሆነ፣ የበለጠ ጤናማ እና ፍትሃዊ የሆነ ዓለም እንደገና እንደሚመጣ ተስፋን በእውነት እናለመልማለን።

26 August 2020, 11:36