ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ጠየቁ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 28/2012 ዓ. ም. ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ካቀረቡት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በመቀጠል በየሳምንቱ እሑድ የሚያቀርቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከምዕመናን ጋር በኅብረት ካደረሱ በኋላ አጭር መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጦርነት እየተካሄደ በሚገኝባቸው አካባቢዎች አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ጦርነቱ ካስከተለው ስቃይ በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጡት ሕዝቦች ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማዳረስ ምቹ መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጦርነት በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች እያደረሰ ያለውን ተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አደጋን ለመከላከል ሲባል ጦርነት በሚካሄድባቸው ሁሉም የዓለማች ክፍሎች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪውን ማስተላለፉን አስታውሰዋል። በጸጥታው ምክር ቤት የቀረበው ዓለም አቀፍ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪ፣ በጦርነቱ ክፉኛ በተጎዱት አካባቢዎች ሰላም ሰፍኖ ሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈው አስቸኳይ የተኩስ ማቆም ውሳኔ ቢያንስ ለዘጠና ቀናት ተግባራዊ እንዲሆን እና ይህም በጦርነት ምክንያት በችግር ውስጥ ለሚገኙት ሕዝቦች ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማድረስ መልካም መንገድ የሚያመቻች እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ወደ ዘላቂ ሰላም ለመድረስ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ሰኔ 24/2012 ዓ. ም. ጦርነት እየተካሄደ ባሉባቸው አካባቢዎች አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ ጦርነት ካሰከተለው አደጋ በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጡት ዕርዳታን ለማድረስ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። 

በመቀጠልም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኝት የሮም ከተማ ምዕመናን እና ከልዩ ልዩ አገሮች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅድሱነታቸው በተጨማሪም መጭው ቅዳሜ ሐምሌ 4/2012 ዓ. ም. በፖላንድ አገር ቼስቶኮፕቫ ከተማ በሚከበረው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልደት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ለመገኘት ዝግጅት በማድረግ ላይ ለሚገኝ የሬዲዮ ማርያ ማኅበረሰብ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ መንፈሳዊ ጉዟቸው የተባረከ እንዲሆን ተመኝተውላቸዋል። 

ጦርነት እና አመጽ በሚካሄድባቸው የሰላም እና የእርቅ ድርድሮችን በማስተባበር የሚያወቅ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር፣ በተባበሩት መንግሥታ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የተላለፈውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪን በሙሉ ድምጽ የደገፈው መሆኑን አስታወቋል። ማኅበሩ በዚህ ማስታወቂያው የጸጥታው ምክር ቤት ጥሪ ሰላምን ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙት መልካም መንገድ የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገንጾ፣ በዚህ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እና በተለያዩ አገሮች መካከል በሚደረገ ስምምነት መሠረት ብቻ የጋራ ጠላታችን የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከለከል የሚቻል መሆኑን አስረድቷል። የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር በመጨረሻም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ በተአገራቱ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ በርትቶ እንደሚሰራ እና ጦርነቶች እና ግጭቶች በሚገኙበት አካባቢዎች ዘላውቂ ሰላምን ለማምጣት የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል።

06 July 2020, 07:41