ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ደስታ እና የአዲስ ሕይወት ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 28/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ ከማቴ. 11፡ 25-30 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ማኅበራዊ ርቀታቸውን ጠብቀው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙንት ምዕመናን ባሰሙት ስብከታቸው፣ በዕለቱ የተነበበውን የወንጌል ክፍል በሦስት በመክፈል፣ በመጀመሪያው ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የመንግሥተ ሰማያት ምስጢር ለድሆች ስለ ገለጠላቸው ለእግዚአብሔር አብ የምስጋና ጸሎት ማቅረቡን፣ በሁለተኛው ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ እና በአባቱ መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት እና በሦስተኛው ክፍል የሕይወት እርካታን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ እኛን የጋበዘን መሆኑን አስረድተዋል።   

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 28/2012 ዓ. ም. ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የቫቲካን ዜና፤

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት ከማቴ. 11፡ 25-30 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ሦስት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እግዚአብሔር አብ የመንግሥተ ሰማያትን ምስጢር ለድሆች በመግለጡ ምክንያት ያቀረበለትን የምስጋና ጸሎት የሚያስታውስ፣ ቀጥሎም ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት የሚያስታውስ ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ እኛም ሁላችን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ፣ እርሱን ስንከተል የሚገኘውን ሰላም እንድንቀበል ይጋብዘናል።

ከሁሉም አስቀድሞ፣ በማቴ. 11፡25 ላይ እንደ ተገለጸው፣ የመንግሥተ ሰማያትን ምስጢር እና እውነትን ከጠቢባን እና ከአዋቂዎች ሰውሮ ስላቆየው ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አባቱን እንዳመሰገነው እንመለከታለን። የተማሩ እና አዋቂዎች ብሎ የሚጠራቸውም፣ ብዙን ጊዜ በእውቀታቸው በመመካት ልባቸው የተዘጋ በመሆኑ ነው። እውነተኛ ጥበብ የሚመነጨው ከልብ እንጂ ስለ ተማሩ ወይም እውቀት ስላላቸው ብቻ አይደለም። እውነተኛ ጥበብ ከልብ ውስጥ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ልብ ውስጥም ይገባል። ስለ ብዙ ነገር የምናውቅ ከሆነ፣ ነገር ልባችን የተዘጋ ከሆነ አዋቂዎች ወይም ጠቢባን ልንባል አንችልም። ኢየሱስም ሲናገር የአባቱ መንግሥት ምስጢራት የተገለጠላቸው በልበ ሙሉነት ልባቸውን የእግዚአብሔርን ድነት ለመቀበል፣ ድነት ለሚገኝበት ቃሉ ልባቸውን ክፍት ላደረጉት፣ እግዚአብሔርን ዘወትር ለሚፈልጉት፣ ሁሉን ነገር ከእርሱ ለሚጠብቁት፣ መታመኛውን በእግዚአብሔር ላይ ላደረገ ልብ ነው ይለናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ነገር ያገኘው ከአባቱ ዘንድ መሆኑ ይነግረናል። በዚህም ከአባቱ ጋር ልዩ እና የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው “አባቴ” በማለት ያረጋግጥልናል። ይህን የመሰለ ግንኙነት በእግዚአብሔር እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ብቻ ያለ፣ አንዱ ሌላውን የሚያውቅበት፣ አንዱ በሌላው ውስጥ የሚገኝበት ግንኙነት ነው። ይህ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩ ግንኙነት ውበቱን በነጻነት እንደሚገልጽ አበባ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት ሲያሳየን፣ በማቴ. 11፡28 ላይ እንደተገለጸው፣ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናጠናክር፣ ከአባቱ የተቀበለውን ጸጋ ሊሰጠን ይጠራናል። እውነትን ሊሰጠን ትፈልጋል፤ እውነት በነጻ የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው።

አባት ለትንንሽ ልጆቹ እንደሚራራላቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስም ሸክማቸው የከበዳቸው ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዛቸዋል። ይህን የሚያደርገው ራሱን ከተቸገሩት መካከል አንዱ አድርጎ ስለቆጠረ ነው። ቀንብሬን በጫንቃችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህና ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ። የማቴ. 11፡29. ኢየሱስ ክርስቶስ የዋህ እና ትሑት ስለሆነ፣ ራሱንም የሚገልጸው በዚህ መንገድ ነው። በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለሆነች ደስ ይበላቸው (የማቴ. 5፡3)። የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትህና እና ራሱን ዝቅ የማድረግ ምስጢሩ ስልጣናቸውን ለተቀሙት ምሳሌ ለመሆን ወይም ይህ ዕድል ስላጋጠመው ሳይሆን ትህትናን ከልብ በተግባር ለመግለጽ ስለፈለገ ነው። የአባቱን እውነተኛ እና ግልጽ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ፍቅር በተግባር ለመግለጽ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉት፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽሙት እና ስለ መንግሥቱ የሚመሠክሩ የቅዱስ ወንጌል ብጹዓን ምሳሌ ነው።

በመቀጠልም ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ወደ እርሱ የምንመጣ ከሆነ በመፈንስ ቅዱስ ኃይል እንደምንለዋጥ ይነግረናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደከሙት እና ሸክማቸው ለከበዳቸው በሙሉ የሚሰጣቸው መታደስ፣ የስነ ልቦና ዕረፍት እና ሰላም ብቻ ሳይሆን ከቅዱስ ወንጌል የሚገኝ ደስታን እና አዲስ ስብዕና የሚገኝበት መጽናናትን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ደስታ ልዩ ደስታ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የራሱን ደስታ ነው የሚሰጠን። ዛሬም ቢሆን መልካም ፈቃድ ላላቸው የዓለማችን ሰዎች፣ ሃብታም እና ባለ ሥልጣናትም ሳይቀር ግብዣውን ልኮልናል። ብዙን ጊዜ “እንደ እርሱ ሃብታም ብሆን፣ እንደ እርሷ ሃብታም ብሆን እንላለን። ስልጣንም ቢኖረኝ እንላለን”

ዓለማችን በሀብት የከበሩትን እና ከፍተኛ ስልጣን ያላቸውን ያከብራቸዋል፣ ከፍም ያደርጋቸዋል፣ በሌላ ወገን ከእነዚህ ሰዎች ጋር እኩል ስብዕና ያላቸውን ወደ መሬት ዝቅ በማድረግ ክብራቸውን ሲቀንስ የምናየው እና  በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ በገሃድ የምንመለከተው ነው። ይህም ቤተክርስቲያን የምሕረት አገልግሎቷን አጠናክራ እንድታበረክት፣ ትህትና እና የዋህነት እንዲታይ ወንጌልን ለድሆች የማብሰር ግዴታ እንዳለባት ያመለክታል። እግዚአብሔርም ቤተክርስቲያኑ ከሆንን ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው።

ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የዋህ እና ትሑት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከጠቢባን እና ከአዋቂዎች ተሰውሮ ለትሑታን የተገለጸውን የመንግሥተ ሰማያት ምስጢር የሚናውቅበት ልባዊ ጥበብን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንድታማልድልን እንለምናታለን”።  

06 July 2020, 07:48