የነጻነት እና የእኩልነት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ንግግር ሲያደርግ፤   የነጻነት እና የእኩልነት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ንግግር ሲያደርግ፤  

የርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት መልካም ምኞት እና የማርቲን ሉተር ኪንግ "ህልም" መታወሱ ተገለጸ።

መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በበላይነት ከመሯት ከቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እስከ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ድረስ ያሉት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ለሚገኘው ለአፍሮ-አሜሪካዊያን ማኅበረሰብ ነጻነት ሲሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም የነጻነት እና የእኩልነት ተሟጋች በነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ ሰላማዊ ትግል የተገለጸ መሆኑ ታውቋል።  

የቫቲካን ዜና፤

በሰሜን አሜሪካ፣ ሚኒያፖሊስ ግዛት በአፍሮ-አሜሪካዊው ወጣት በጆርጅ ፍሎይድ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ፣ በማርቲን ሉተር ኪንግ ይካሄድ የነበረው የነጻነት እና የእኩልነት ትግል በዘረኞች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኝነት ገና ብዙ እንደሚቀረው ያረጋግጣል ተብሏል። ማርቲን ሉተር ኪንግ የዛሬ 57 ዓመት፣ በነሐሴ ወር ላይ “ሕልም አለኝ” በማለት ያሰማው ታሪካዊ ንግግር ዛሬም በእነዚህ ቀናት ውስጥ ፍትህ እና ሰብዓዊ ክብር በጠማቸው አፍሮ-አሜሪካዊያን አንደበት መስተጋባቱ የቀጠለ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ጥያቄ በሌሎች አናሳ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚነሳ መሆኑ ታውቋል። መሠረቱን በቅዱስ ወንጌል ላይ ያደረገ፣ የፍትህ እና የእኩልነት ሕልም፣ ነጻነትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር አምላካዊ ፍቅር በመታገዝ በቀድሞ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እስከ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ድረስ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ሲደርስበት መቆየቱ ይታወሳል።

ሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን መሪነት ሥልጣን ከተቀበሉ ከአራት ዓመት በኋላ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ የነጻነት እና የእኩልነት ተሟጋች የሆነው የማርቲን ሉተር ኪንግ ዕረፍት መረዳታቸው ይታወሳል። ማርቲን ሉተር ኪንግ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለመቀበል መብቃቱን የሰሙት ር. ሊ. ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ፣ ሽልማቱ በሰሜን አሜሪካ ዜጎች መካከል የጥላችን እና የበቀል መንፈስን በማስወገድ ፣ በአዲስ መልክ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የፍትህ መንገድ እንዲፈጠር መጸለያቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በሕዝቡ ልብ ውስጥ የተሰማው ጥልቅ ሕመም፣ ከአመጽ እና ከሥርዓተ አልበኝነት የበለጠ ተሰሚነት እንዳለው ገልጸው፣ የሕዝብ ሃላፊነት በተጣለባቸው እና መልካም ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ የማርቲን ሉተር ኪንግ ሞት አዲስ ተስፋ እንዲያድግ ማድረጉን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ከሃያ ዓመታት በኋላ፣ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 12/1987 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የማርቲን ሉተር ኪንግ ህልም ማስታወሳቸው ይታወሳል። በወቅቱ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ሰሜን አሜሪካ ግዛት ወደ ሆነው ኒው ኦርሌንስ ባድረጉት ሐዋርያዊ ግብኝታቸው፣ ከአገሪቱ አፍሮ-አሜርካዊ ማኅበረሰብ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታችው በወቅቱ ባሰሙት ንግግር በአገሪቱ የሚገኙ የአፍሮ-አሜሪካዊ ማኅበረሰብ ጉዞ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፣ ፍትህን ለማምጣት፣ ነጻነትን ለመቀዳጀት እና የሚደርስባቸውን ጭቆና ገርስሶ ለመጣል ረጅም መንገድ መጓዛቸውን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ዘረኝነትን እና ጭቆናን ለማስወገድ ያደረጉትን አስቸጋሪ ጉዞ እግዚአብሔር በሰላም የመራቸው መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። ከእግዚብሔር ዘንድ የተሰጠውን የማርቲን ሉተር ኪንግ የውክልና ሚናን ያስታወሱት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በሰላማዊ የነጻነት እና የእኩልነት ትግል የአፍሮ-አሜሪካዊያን የኑሮ ሁኔታ ተሻሽሎ መገኘቱንም አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛም በነበራቸው ጥልቅ ክርስቲያናዊ የወንድማማችነት መንፈስ፣ በማርቲን ሉተር ኪንግ ልብ ውስጥ ለሞት ያበቃው የኢየሱስ ክርስቶስ የነጻነት አገልግሎት በተግባር የተገለጸ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሚያዝያ 16/2008 ዓ. ም. ወደ ዋሽንግተን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ በእግዚ አብሔር ላይ እምነትን መጣል ወደ መልካም መንገድ እንደሚመራ ገልጸው፣ በማርቲን ሉተር ኪንግ የተመራው ሰላማዊ የነጻነት ጉዞ በእግዚአብሔር የተመራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስም እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር መጋቢት 12/2018 ዓ. ም. የማርቲን ሉተር ኪንግ ልጅ፣ ቤርኒስን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ግንኙነት ልዩ የሚያደርገው በአባቷ እረፍት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ወቅት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2017 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ በዘር መድልዎ ላይ የተቀዳጃቸው ድሎች ምን ጊዜም የሚረሱ አይደለም ብለው፣ ቆራጥነት የታከሉባቸው ዘላቂ ትግሎቹ መልካም ውጤቶችን ለማግኘት አስችሎታል ማለታቸው ይታወሳል።         

04 June 2020, 18:44