ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአረጋዊያን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአረጋዊያን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ለአረጋዊያን እንክብካቤ በማይደረግበት ሥፍራ መልካም ወጣትን ማፍራት አይቻልም"።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአረጋዊያን ላይ እየተፈጸመ ያለ በደል ሕዝብ አውቆ አስፈላጊውን እርምት እንዲያደርግ ለማስተማር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባዘጋጀው ቀን፣ የአረጋዊያን አቅም ማነስ ሕዝቡ በመገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እና ሰብዓዊ ክብር ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማኅበረሰባችን ለአዛውንት ምቹ ሥፍራን በማዘጋጀት ተገቢውን እንካብካቤን እና ክብር ለመስጠት ራሱን ያላዘጋጀ መሆኑን ግልጽ አድርጓል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለአዛውንት ተገቢው እንክብካቤ የማያደርግ ማኅበረሰብ መልካም ወጣት ትውልድ ማዘጋጀት የማይችል መሆኑን ትናንት ሰኔ 8/2012 ዓ. ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ በዋለው የአዛውንት እንክብካቤ ቀን አስታውቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊትም ለአረጋዊያን ያላቸውን ከፍተኛ ክብር በመግለጽ፣ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅላቸው በማለት መልዕክት ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው አረጋዊያን ያካበቱት የሕይወት ልምድ ለመላው ዓለም ትልቅ ሃብት መሆኑን ገልጸው፣ የማኅበረሰብ ሸክም ናቸው በሚል አስተሳሰብ አረጋዊያንን ማግለል ትክክል እንዳልሆነ መናገራቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ጥቅምት ወር 2012 ዓ. ም. በጣሊያን ብሔራዊ የአረጋዊያን ሰራተኛ ማኅበር አባላትን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ አረጋዊያን እንደ ዛፍ በርካታ ፍሬን የተሸከሙ፣ ለአንድ ማኅበረሰብ ባሕላዊ እሴቶች ማደግ እና ለማኅበራዊ ሕይወት ብዙ አስተዋጽዖን ማድረግ የሚችሉ መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

ልጆች ከአያቶቻቸው ጋር መወያየት ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍል እርስ በእርስ ተገናኝተው እንዲወያዩ በማለት ሃሳባቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ሲታወቅ፣ ልጆች ከአያቶቻቸው ጋር በመነጋገር ወደ ጋራ ስምምነት መድረስ የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል። የጣሊያን ብሔራዊ የአረጋውያን ሰራተኛ ማኅበር አባላትን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት እንደገለጹት፣ መልካም ዓለምን መገንባት የሚቻለው በአዲሱ እና በአሮጌው ትውልድ መካከል ውይይት በማድረግ ነው ብለዋል። አረጋዊያን እምነትን ለትውልድ በማሸጋገር ከፍተኛ ሚናን መጫወት ይችላሉ ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ አረጋዊያን እምነትን ለህጻናት እና ወጣቶች በማስተላለፍ ወይም በማስተማር ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ ማለታቸው ይታወሳል። በመሆኑም አረጋዊያን በዘላቂ ሐዋርያዊ አገልግሎት እቅዶች ውስጥ ማካተት እንደሚገባ አሳስበው አረጋስዊያን ማኅበረሰብን በማስተማር ትልቅ አስተዋዝዖን ማበርከት የሚችሉ፣ ቅዱስ ወንጌልን በመመስከር ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ማበርከት የሚችሉ እና ወደ እግዚአብሔር ፍቅር የተጠሩ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው አስታስውቀዋል።

አረጋዊያን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት፣

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጠቁ አረጋዊያን ቁጥር በማስመልከት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለማችን ወደ 703 ሚሊዮን የሚጠጉ አዛውንት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ገልጿል። ሪፖርቱ በማከልም አረጋዊያኑን የሕሊና እና የአካል ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑን ገልጾ፣ የገንዘብ አቅም ማነስ ሌላው ችግር መሆኑን አስታውቋል። ሪፖርቱ በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በይበልጥ የተጎዱት አረጋዊያን መሆናቸውን አስታውቋል። በጣሊያን ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተያዙት መካከል ሰማንያ ከመቶ የሚሆኑት ዕድሜአቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፉት ወራት ውስጥ ባቀረቡት ጸሎታቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጠቁትን አስታውሰው፣ ብቻቸውን በመሆን በፍርሃት እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን አረጋዊያንን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለው፣ አረጋዊያን ጥበብን፣ ዕውቀትን፣ ሕይወትን እና ታሪክን እንዳወረሱን ሁሉ እኛም ከጎናቸው በመሆን በጸሎታችን ልናግዛቸው ይገባል ብለዋል።

አረጋዊያንን የሚደግፉ በጎ ፈቃደኞች መኖር አስፈላጊ ነው፣

በብቸኝነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ለመርዳት እና ለማገዝ ከተለያዩ ማኅበራት የተወጣጡ በጎ ፈቃደኞች መኖራቸውን ያስታወሱት “አውሰር” የተባለ ድርጅት ፕሬዚደንት፣ ክቡር አቶ ኤንዞ ኮስታ፣ በእነዚህ ወራት ውስጥ በአረጋዊያን ላይ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲዛመት ዋና ምክንያቱ በቂ ትኩረት እና ጥንቃቄ ባለመደረጉ እንደሆነ አስረድተው፣ በለይቶ ማቆያ ወቅት ድርጅታቸው ከአርባ ሺህ በላይ ለሚሆኑ አረጋዊያን የስነ ልቦና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀው፣ በተጨማሪም ዕለታዊ ቀለብን እና መድኃኒቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውቀዋል። አስፈላጊ ነገሮች በጊዜ አለማቅረብ አረጋዊያንን ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳርጋቸው መሆኑን ክቡር አቶ ኤንዞ ኮስታ አስታውቀዋል። በጣሊያን በእርዳታ ማዕከል ውስጥ በሚገኙት አረጋዊያን ላይ ከፍተኛ የሞት አደጋ ያጋጠማቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤንዞ ኮስታ፣ በአረጋዊያን ላይ የሚደርስ የሞት አደጋን ለመከላከል የዕርዳታ ማዕከ መፍትሄ እንደማይሆን ገልጸው፣ ከአረጋዊያኑ በኩልም ወደ ማዕከሉ የመግባት ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው አረጋዊያን በግል የመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እርዳታ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም በዚህ አስጨናቂ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለአረጋዊያን የሚበጅ አዲስ የአገልግሎት መንገድ ማግኘት እና በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኝ ሰው ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።     

16 June 2020, 17:55