የመጥመቁ ዮሐንስ መወለድ የመጥመቁ ዮሐንስ መወለድ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ እንድንመሰክር ያስተምረናል

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ መጥምቁ ዮሐንስ የተወለደበ እለት በሰኔ 17/2012 ዓ.ም መከበሩ ተገልጿል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ሳምንታዊውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ እንድንመሰክር ያስተምረናል ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “ዛሬ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁ ልደት በዓል ነው፣ እምነትን ጠብቆ መኖር፣ ከእውነት የመነጨ ሰላም እና ደስታ የሚገኘው የኢየሱስን ወንጌል በሕይወታችን በመመስከር ነው” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

”ስንክሳር ከአዲስ ዓመት ዕለተ ማግስት መስከረም 2 ቀን የመጥምቁ የቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕትነት ያስታውሰናል። “በዚህች ዕለት የካሕኑ የዘካሪያስ ልጅ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በጨካኙና በከሐዲው ንጉሥ ሄሮድስ እጅ ተገድሎ ሰማዕትነትን ተቀብሎአል (.ስንክሳር መስከረም 2 ቀን )።

መጥምቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ በጾም፣ በጸሎትና በተጋድሎ ረጅም ጊዜ ካሳለፈ በኃላ በሰማይ ተሰጥቶት የነበረውን ከፍ ያለ መንፈሳዊ መልእክት እፊት እፊት እየሄደ የመሲህን መንገድ አዘጋጅና ጠራጊ ሆኖ ወደ እስራኤል ሕዝብ መጣ፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ሆኖ ትምህርቱን ለማዳመጥ ወደ እርሱ ይቀርቡ ለነበሩት አይሁዳውያን «መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንሰሐ ግቡ (.ማቴ  3፣2) እያለ ከሰው ሰው ሳይለይ ይሰብክላቸው ነበር፡፡

ሕዝቡ ሁሉ ካህናትን፣ ባለጠጐችን፣ ወታደሮችን፣ ባለሥልጣኖችን ወዘተ.. ሳይፈራና ሳያፍር እንደ አስፈላጊነቱ ይገስጻቸውና ይመክራቸው ነበር፡፡ ንጉሡን ሄሮድስንም ሳይቀር በመጥፎ ተግባሩ አጥብቆ ይገስጸው ነበር፡፡ «የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም (ማር. 6፣18) ይለው ነበር፡፡ ንጉሥ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅ ሰው መሆኑን አውቆ መፍራት ብቻ ሳይሆን ያከበረውም ስለነበነር በተግሳጹ አይቀየመውም ነበር፡፡ ነገር ግን በምንዝርና የያዛትን የሕግ ሚስቱ ያልሆነችውን ሴት ለማስደሰት ሲል እስር ቤት ሊያስገባው ግድ ሆነበት፡፡ ሂሮዲያዳ መጥምቁ ዮሐንስ ክፋኛ ትጠላው ነበር፡፡ በልቧም ተቀይማው እርሱን የምታስገድልበት ቀንና ምክንያት ትጠብቅና በአእምሮዋም ታውጠነጥን ነበር፡፡ በጉጉት የጠበቀችውን ቀን እምብዛም አልዘገየም፡፡ የንጋት ጨለማ ቀስ በቀስ ከተወገደ በኃላ ከተራሮች ጀርባ ወገግ እንደሚል የፀሐይ ጮራ ቀኑ ከተፍ አለላት።

አንድ ቀን ንጉሥ ሄሮድስ በልደት በዓሉ ዕለተ የመንግሥቱን ባለስልጣኖች ሁሉ ከእርሱ ጋር ምሳ እንዲበሉ ጋበዛቸው፡፡ መኳንንቱም ተደስተው ከእርሱ ጋር ምሳ እየበሉ ሳለ የሄሮዲያዳ ሴት ልጅ ወደ ምሳ ግብዣው አዳራሻ ገብታ አስደናቂ የሆነ ዘፈን በታጋባዦቹ ሁሉ ፊት ዘፈነች፡፡ ንጉሱ ከተጋባዦች ጋር በጣም ደስ አለው፡፡ በሞያዋ ሽልማት ሲሰጣት ፈልጐ «የምትፈልገውን ጠይቂኝ አላት፡፡ የመንግስቱን እኰሌታም እንኳን ቢሆን እንደሚሰጣት እንጂ እንደማይነፍጋት ማለላት በተጨማሪም የመሐላ ቃል ገባላት፡፡

ልጅቷ ወጣ ብላ ወደ እናቷ ዘንድ ሄዳ፣ «ንጉሡን ምን ልለምነው ብላ ጠየቀቻት፡፡ እናቷም «የመጥምቁ ዮሐንስ ጭንቅላት በሳህን አድርገህ አሁን ስጠኝ ብለሽ ለምኝው ስትል መለሰችላት፡፡ ልጀቷም ወደ ንጉሱ ተመልሳ ገብታ «የመጥምቁ ዩሐንስን ጭንቅላት በሳህን አድርገህ አሁን ስጠኝ አለችው፡፡ ሄሮድስ በጣም አዘነ፡፡ ነገር ግን መሐላውን እንዳይሽር በይሉኝታ ስለተሸነፈ እምቢ ሊላት አልፈለገም፣ ወታደሮቹምን ጠርቶ የመጥምቁ ዮሐንስን ጭንቅላት በሳህን አድርገው እንዲያመጡላት አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ወደ እስር ቤቱ ውስጥ ገብተው ዮሐንስን አንገቱን ቆርጠው ጭንቅላቱን በሳሕን አድርገው ለልጅቷ ሰጡአት፡፡ እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠቻት፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ሞቱን ከሰሙ በኋላ ሬሳውን ወስደው ቀበሩት (ማር  6፣21-29)።

በዚህ ሁኔታ የልዑል ነቢይ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ ሕይወቱን በሰማዕትነት ጨረሰ። ጽድቅን እየሰበከ ሲኖር የጨለማና የኃጢያት ልጆች በሐሰት ተነስተው ከምድረ ገጽ አጠፋት፡፡

መንፈሳችንን ከቅዱስ ዮሐንስ መንፈስ ጋር ብናስተያየው በጣም የተለያዩና ደካማ ሆኖ እናገኘዋልን፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መንፈስ የሰማይ ነው፣ የእኛ ግን የምድር ነው፡፡ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር አገልግሎት ትጉህ፣ ጽኑ፣ ብርቱና ታማኝ ነበር፡፡ ከሰው ይልቅ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ስፋትና ክብር ባለው ኃይል በታታሪነትና በትጋት ይሠራ ነበር፡፡ እኛ ግን በአምላክ ጉዳይ ቀዝቃዞችና ሃኬተኞች ነን፡፡

ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን፣ ከፈጣሪያችን ይልቅ ፍጡርን እንፈራለን፣ ብዙ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ለመሥራት እንታክታለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር መንፈስ ይመራ ስለ ነበር ጽድቅን ይወድና ይከተል ነበር፣ ኃጢአትን ግን ይጠላና ይዋጋውም ነበር፡፡

በልዑል ሰማያዊ አምላክ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመፈጸም የሰውን ዓይን አይፈራም ነበር፡፡ እኛ ግን ወደ ዓለም መንፈስ ያዘነበልን ስለሆንን ጽድቅ ይከብደናል፡፡ ከጽድቅ በመሸሽ ከጠላታችን ከኃጢአት ጋር ወዳኝነትን እንመሠርታለን፣ በእርሱም ስንመላለስ እንኖራለን፡፡ ብዙ ጊዜ የሰውን ዓይን ፈርተን ጽድቅን እንተዋልን፣ መጥፎ ሥራን ድርጊት እንፈጽማለን ይሉኝታ ፈርተን በመንፈሳዊ ተግባራችን እናፍራለን፡፡ እንደዚህ ያለ ቀዝቃዛና ደካማ መንፈስ እግዚአብሔርን ያስቀይማል!! ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ኑሮ ብዙ ነገሮችን ይጐድሉታል፡፡ ከእግዚአብሔር ክብርና ከነፍሳችን ደህንነት የበለጠ ነገር የለንም፡፡ እንደዚህ ከሆነ ቀዝቃዛ መንፈሳችንን አነቃቅተንና አስወግደን የቅዱስ ዮሐንስን ትጉህና ጠንካራ መንፈስ እንልበስ።  

24 June 2020, 18:35