ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓዶቫ ምሳሌ መከተል ይኖርብናል አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓዶቫ ማሕበር አባላት ለሆኑ ታናናሽ የፍራንቸስካዊያን ወንድሞች ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት የማሕበሩ አባላት የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓዶቫ ምሳሌ መከተላቸውን እንዲቀጥሉ በመልእክታቸው ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን መልእክት ያስተላለፉት የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓዶቫ ማሕበር የተመሰረተበትን 800ኛ አመት በማስመልከት ለፍራንችስካዊያን ማሕበር ታናናሽ ወንድሞች ባስተላለፉት መልእክት ሲሆን ይህም መልእክት የማሕበሩ አጠቃላይ የበላይ አለቃ በሆኑት በአባ ካሎስ አልበሮ በኩል የተላለፈ መልእክት እንደ ነበረውም ተያይዞ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስተላለፉት መልእክት “በተለይም በፍራንችስካዊያን ማሕበር አባላት እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓዶቫ ወዳጆች እና ተከታዮች የቅዱስ አንጦኒዮስን የቅድስና ምንጭ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር በመላው ዓለም በሚገኙ መንገዶች ላይ እንድትዘሩ እና እንድትመሰክሩ አደራ እላለሁ” የሚል ጭብጥ የያዘ መልእክት እንደ ሆነም ተገልጿል።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች በመቀጠል የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓዶቫ ታሪክ በአጭሩ እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።
ቅዱስ አንጦንኒዮስ ዘፓዶቫ
ቅዱስ አንጦኒዮስ እ.ኤ.አቆ. በ 1195 ዓ.ም. በፓርቱጋል አገር በሊስቦና ከተማ ተወለደ። የክርስትና ስሙ ፈርናርዶ ሲሆን ቆይቶ በምንኩስውናዊ ስም አንጦንዮስ ተባለ። በሕይወት ቅዱስና በትምህርተ ሃይማኖታዊና በሞራላዊ መንፈሳዊነት በስሎ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ሕዝብን በማገልገል መሥራች አርአያ ሆኖ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበት ቦታ በፖዶቫ ከተማ ስለነበረ ደግሞ "ቅዱስ አንጦንዮስ ዘፓዶቫ" ተሰየመ።
በወጣትነቱ ግዜ በሊስቦን ከተማ በቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ በነበረው ቊምስናዊ ትምህርት ቤት ተማረ። ቀጥሎም በቅዱስ አጎስጢኖስ ማኀበርተኞች ዘንድ ለ 2 ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሎ ወደ ኮይምብራ ሄዶ በቅዱስ መስቀል አጎስጢኖስ ገዳም 9 ዓመታት የተዮሎጊና የቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት አጥልቆ ካጠናቀቀ በውኀላ ማዕረገ ክህነትን ተቀበለ። በዚያን ግዜ የመስቀል ድልንና የሉተራን ጉባኤ ትምህርትን መመልከት የስብከተወንጌላዊ ስሜትን በኋይል አነቃቃበት። እንደ አውሮጳውያን አቆ. ጥር 16 ቀን 1220 ዓ.ም. በ 25 ዓመት እድሜው ክርስትናን ለመስበክ ወደ ሞሮኮ ይሄዳል። በሞሮኮም በሰማዕትነት የሞቱ የፍራንቼስካዊያን ክቡር ቅንዋትን በመመልከት ወደ ንዑሳን አኀው ማሕበር ይገባል። ነገር ግን በበሽታ ምክንያት ወደ አገሩ ሲመለስ በኢጣልያ በማለፈ ወደ አሲዚ በመሄድ ከቅዱስ ፍራንቼስኮስ ጋር ተገናኘ። በአለቆቹ ፈቃድ መጀመሪያ ፎርሊ በሚባለው የኢጣልያ ከተማ ቆየ። ቀጥሎም በቅዱስ ፍራንቼስኮስ ፈቃድ በቦሎኛ ከተማ ቴኦሎጂን አስተማረ። በ1225 ዓ.ም. ወደ ደቡብ ፈረንሳይ በመጓዝ በልዩ ልዩ ከተማዎች በመዘዋወር ቅዱስ ወንጌልን እየሰበከ የዘመኑ መናፍቃዊ መሰናክሎችን ተቃወመ። መነኮሳንን እየጎበኘ ሰንበታዊ አስተምህሮችን እያዘጋጀና እየዘረዘረ ሐዋሪያዊ አገልግሎቱን ሲጠጥ በመኀበራዊ ጉዳይ በ 1228 ዓ.ም. ወደ ሮም በተላከ ግዜ በካርዲናሎቹ ፊት ያሰማው ስብከት ጥልቅ መኖሩን በመገንዘብ ር.ሊ.ጳጳሳት ጎርጎርጊዮስ 9ኛ "ታቦተ ኪዳን ወማኀደረ ቅዱስን መጻሕፍት" በማለት ትምህርተ ሃይማኖታዊ ብስለቱንና ስብከተወንጌላዊ ቅናቱን በማድነቁ ሐዋሪያዊ ሙያውንም በማመልከት አመሰገኑት።
በዚሁ በሚመሰገነው አኳኋን ሐዋሪያዊ አገልግሎቱን አበርክቶ ሲያበቃ ቅ. አንጦንዮስ ሰኔ 13 ቀን 1231 ዓ.ም. በፖዶቫ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ር.ሊ.ጳጳሳት ጎርጎርዮስ 9 ግንቦት 30 ዕለት 1932 ዓ.ም. በሞት ከመለየቱ 11 ወራት በውኋላ በስፖሌቶ ከተማ የቅድስና ቤተክርስቲያናዊ ሥርዓትን ፈጸሙለት። ገና በምድራዊ ሕይወቱ ስለ ብዙ ተአምራታዊ እርዳታዎችን ያወረደ እንደመሆኑ መጠን መንፈሳዊ ከበሬታው በመላ ዓለም ሕዝበ ክርስቲያን ተዘረጋ። የፖዶቫ ሰበካ ሃውልታዊ የሆነው የሁለት ዘመናት ኪነ ጥበበኞች በተደጋገፉበት ሥራ አማካይነት የተፈጸመውን ቤተክርስቲያን ያሠራበት መሆኑን እናውቃለን።
ቅዱስ አንጦንዮስ የቤተክርስቲያን ሊቅ
ቅዱስ አንጦንዮስ ጥልቅ ጸሐፊ አስተማሪና ሰባኪ እንደመኖሩ መጠን ከቤተክርስቲያን ከሚታወቁት ሊቃውንት አንድ መሆኑ ተመስክሮለታል። ተዮሎጊያዊ አስተዳደጉ መልካም የትምህርት አሰጣጡ ፍሪያማ አሰባበኩ ምግባራዊ ቅዱስ መጽሐፍትን በመተርጐም ይገልጽ የነበረው አስተያየቱም እጅግ በጣም የበሰለ መኖሩ በሕይወት ታሪክ ይመለከታል። የድርሰቱ አስተማሪነቱና የስብከቱ ምንጭ ከቅዱስ መጽሐፍ በላይ የቅዱሳን አበው ወንጌላዊ ትምህርት ነበር። ከዚህ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ከር.ሊ.ጳጳሳት "ታቦተ ኪዳንና የቅዱሳን መጽሐፍትን ተሬንተራ" ለመሰየም በቃ። ተዮሎጊያዊ ትምህርቱ በቅዱስ አጎስጢኖስ ትምህርት ላይ የተመረኮዘ እንደ መሆኑ መጠን ስለ ጸጋ ሚሥጢር ጥልቅ የሆኑ አንቀጾችን የጻፈ በስብከቶቹ የገለጸ መሆኑን የሕይወት ታሪክ ደራሲያን ያስታውሳሉ።
የጸረ ሃይማኖት መናፍቃዊ ባህሎችን በኋይል የተቃወመና በዚሁ ትምህርታዊ ሆነ ሞራላዊ ትግል ያገነው ድልን ለማስገንዘብ የዘመኑ ሕዝበ ክርስቲያንና የሕይወቱ ታሪክን ጸሐፊዎችን "የመናፍቃውያን መዶሻ " ሰይመውታል። ስብከቶቹ ኃጢዓትን ለማስወገድና መንፈሳዊ ኃይሎቹን ለማነቃቃት ለሕዝበ ክርስቲያን የቀረቡ መኖራቸው ከይዞታቸው ይገለጻል። በተለይ ስለ ሚስጥረ ንስሐና ስለ መሥዋዕትነት ጥልቅ ስብከቶችን ሲዘረዝር ሁሉን የሚችል ንጉሥ የሆነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኛ ፍቅር ትሕትናን የተቀዳጀ መሆኑን ከማሳሰብ አያቋርጥም ነበር። ስለ ሚሥጥረ ቁርባን ሲሰብክም ከሌላ ይልቅ መድኃኔ ዓለም የፈጸመውን መሥዋዕትነትና እመቤታችን ማሪያም የታገሠችው መከራ በማስታወስ ያድማጮቹ መንፈሳዊነት ያነቃቃ ነበር።
የቅዱስ አጎስጢኖስ የቅዱስ ጎርጎርዮስና የቅዱስ በርናርዶስ አርአያን በመከተል ስለ መንፈሳዊ አኗኗር ጥልቅ ሥርወ ሐሳቦችን ሰበከ። ባንድ በኩል መናፍቃውያን ባህሎችን ሲኮንንና ሲያስወግድ በሌላ በኩል ሕዝበ ክርስቲያን በተቀደሰው ሕይወት በሚያድግበት በቅዳሴ ስርዓት የሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብን መነሻ በማድረግ የሚዘረዘር ትምህርተ ሃይማኖታዊ ስብከቱን ይኮተኩት ነበር።
የቅዱስ አንጦንዮስ ዘፓዶቫ ሕይወትና ሐዋሪያዊ ግልጋሎት ታሪክ እንዲሁ ባጭሩ ሲመለከት ዘመኖች አልፈው ዘመናት ሲከተሉ በማኀበርተኞቹ በፍራንቼስካውያን አኀው ብቻ ሳይሆን በመላ ዓለም ሕዝበክርስቲያን በእውነተኛ መንፈሳዊነት ይከበራል። እንደየ ሕዝቦቹ ልማድ ልዩ ልዩ በዓሎችና የርኀራሔ ሥራዎች ለታላቁ ቅዱስ ክብር ይፈጸማሉ። አንዳንዶቹ የሕይወቱ ታሪክን ባለማወቅ ከአበምኔቱ ከቅዱስ አንጦንዮስ ገዳማዊ ያደባልቁታል።
የምስልን ቀራጺዎችና ሠዓሊዎች ቅ. አንጦንዮስ ዘፓዶቫን መጽሐፍን አስይዘው ሕፃኑን ኢየሱስ አሳቅፈው የንጽሕና ማሳሰቢያ የሆነውን ነጭ አበባንም ጨምረው ያሳዩታል። ለቅዱስ አንጦንዮስ ክብር ድሆችን ማስተናገድ በተለይም እንጀራን መስጠት በቅዱሱ የሕይወት ታሪክ የተመሠረተው ያንዳንዶቹ ሕዝቦች ደግ ሥራ ነው። እንዲሁ አንዲት ሴት ልጇን ስላስነሣላት እንደ ልጇ ሚዛን የሚያህል እንጀራን ለድሆች ለማበርከት ያመሰገነችው መሆንዋን ያስታውሳሉ።