ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለስደተኞች እና ለአከባቢ እንክብካቤ ማድረግ እንድንቀጥል ጠየቁ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለስደተኞች፣ ለጥገኝነት ጠያቂዎች እና አከባቢን የመንከባከብ አስፈላጊነት በተመለከተ ግንዛቤ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት ትላንት ሰኔ 14/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ነው።
የቫቲካን ዜና
የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ምዕመናን የራሳቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉ እና ቁርጠኛ እንዲሆኑ፣ ምዕመናን አብሯቸው እንዲጸልዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጠይቀዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን የብስራተ ገብርኤል ጽሎት” ከደገሙ በኋላ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰኔ 13/2012 ዓ.ም የሰደተኞች ቀን እንዳከበረ ያስታወሱ ሲሆን አሁን መላውን ዓለም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የከተተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ “ክብራቸውንና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ለስደተኞች አስፈላጊውን ጥበቃ የማረጋገጥ አስፈላጊነትን አጉልቶ አሳይቷል” ብለዋል።
ለሁላችንም ውጤታማ በሆነ መንገድ የሰው ልጆችን መብት ለመታደግ በተለይም ለከባድ አደጋ ተጋላጭ የሆኑትን አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱትን ሰዎች ለመርዳት እና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ቆራጥ እንድንሆን ምዕመናን ከእርሳቸው በዚህ ተግባር ተሳታፊ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸው መጋበዛቸው ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን ጥሪ ለማቀረብ የተገደዱት ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ታቋም ያወጣው አስደንጋጭ መረጃ ሲሆን መረጃው በሪፖርቱ እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ 80 ሚልዮን ስደተኞ እንደ ሚገኙ፣ ይህም መረጃ እስካሁን ስደተኞችን በተመለከተ ከወጣው ሪፖርት በቁጥር እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ የተነሳ እንደ ሆነ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
ለአከባቢ እንክብካቤ ማደረግ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመቀጠል “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንድናሰላስል ያደረገን ሌላው ገጽታ በሰውና በአከባቢ መካከል ያለው ግንኙነት ነው” ያሉ ሲሆን “በወረርሽኙ የተነሳ በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ እንድንቆይ በመገደዳችን የተነሳ በመኪና እና ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በሚለቀቁ ጪሶች ምክንያት ይከሰት የነበረው የአከባቢ ብክለት ቀንሷል፣ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከትራፊክ መጨናንቅ እና ጫጫታ ነፃ የሆኑ የብዙ ቦታዎችን ውበት ለመገንዘብ ችለናል፣ የጋራ መኖሪያችንን የመንከባከብ ስራችንን መቀጠል እንድንችል በመጋበዝ ሥራችንን እንድንጀምር ጥሪ አቅርቦልናል” ማለታቸው ተገልጿል።
በአንዳንድ አህጉራት እና ክልሎች ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለው ሞት እና ሕመም እየተበራከቱ መሄዳቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም ዙሪያ ያሉ አንዳንድ አገሮች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭ እየቀነሰ በመምጣቱ የተነሳ አንዳንድ እገዳዎችን በማንሳት ላይ እንደ ሚገኙ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ተጥለው የነበሩ አስገዳጅ ገደቦች ሊነሱ የቻሉት በወረርሽኙ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማደረግ እና ስራ አጥነትን እና ድህነትን ለመቀነስ ታቅዶ የተደረገ መሆኑን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ ዙሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተደረገ የሚገኘውን ስር ነቀል ለውጥ ማድነቃቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ተግባር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎላ እና ዜጎች የጋራ ሀብታቸውን ከሌሎች ጋር እንዴት ተጋርተው መኖር እንደ ሚገባቸው እንዲገነዘቡ አጋጣሚውን የፈጠረ ክስተት እንደ ነበር ከገለጹ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።