ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ አባትና ልጅ በሚነጋገሩበት መልኩ ከግዚአብሔር ጋር መነጋገር እንደ ሚገባን አብርሃም አስተምሮናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በግንቦት 26/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ ያደረጉት ሳምንታዊ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መተላለፉ ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ እና አምስተኛ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዚሁ “የክርስቲያን ጸሎት” በሚል አርዕስት ቅዱስነታቸው በተከታታይ በማደረግ ላይ በሚገኙት የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ አንድ አባት ከልጁ ጋር በሚነጋገርበት መልኩ ከግዚአብሔር ጋር መነጋገር እንደ ሚገባን አብርሃም አስተምሮናል? ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በአብርሃም ሕይወት ውስጥ በድንገት የሚመላለስ አንድ ድምፅ ተከሰተ። ያልተለመዱ ጉዞዎችን እንዲጀምር የሚጋብዘው ድምጽ - ከትውልድ አገሩ፣ ዘርማንዘሩ ከሚኖርበት አከባቢ ወደ አዲስ እና ወደተለየ የወደፊት ሕይወት እንዲሄድ የሚያነቃቃ ድምጽ። ይህ ሁሉ ጥሪ የተደረገው በተገባው ቃል ኪዳን ላይ መሰረቱን ባደረገ መልኩ ሲሆን እርሱም በዚህ ቃል ኪዳን ማመን ይጠበቅበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጀመሪያው አባታችን ቀድሞ ስለነበረው ታሪክ የሚናገረው ነገር የለም።  የነገሮችን አመክንዮ ስንመለከት ግን ሌሎች አምላኮችን ያመልክ እንደነበር ይጠቁማል፤ ምንአልባትም ሰማይንና ከዋክብትን መመርመር የለመደ ጥበበኛ ሰው ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ዘሩ በሰማይ ላይ እንደሚገኙ ከዋክብት ያህል ብዙ እንደሚሆን ጌታ ለእርሱ ቃል ገብቶለታል።

አብርሃም ጉዞ ጀመረ። የእግዚአብሔርን ድምፅ አዳማጠ እና በቃሉም አመነ። እናም በዚህ ጉዞ  ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሰላስልበት አዲስ መንገድ ተወለደ፣ ለዚህም ነው አባታችን የሆነው አብርሀም ምንም እንኳን ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆን እንኳን፣ ከባድ ቢሆንም እንኳን ለእርሱ ለእግዚአብሔር ታዛዥ በመሆኑ የተነሳ በአይሁዳዊያን፣ በክርስቲያኖች እና በእስልምና የእመነት ባሕሎች ውስጥ ለእግዚአብሔር ራሱን ያስገዛ መልካም ሰው ሆኖ የተጠቀሰው በዚሁ ምክንያት ነው።

ስለሆነም አብርሃም ለቃሉ ታማኝ የሆነ ሰው ነበር። እግዚአብሔር በሚናገርበት ጊዜ ሰው የዚያ ቃል ተቀባይ ሲሆን ሕይወቱ ቃል እና ሥጋ የሚገናኙበት ስፍራ ይሆናል። ይህ በሰው ልጅ የሃይማኖት ጉዞ ውስጥ አዲስ ነገር ይፈጥራል፣ የአማኙ ሕይወት የጥሪ ሕይወት እንደ ሆነ እንዲገነዘብ ያደርገዋል፣ ቃል የተገባለት ነገር የሚፈጸምበት ስፍራ እንደ ሆነም መገንዘብ ይጀምራል፣ እናም በአለም ውስጥ በጥላቻ ስሜት ሳይሆን የሚጓዘው ነገር ግን በዚያ ቀን ብርታት በሚሆነው በዚያ ተስፋ ጥንካሬ ነው።

የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍን በማንበብ ለተገባለት ቃል ኪዳን ታማኝ በመሆን አዘውትሮ በሂደቱ እየታየ ለነበረው ለዚህ ቃል ቀጣይነት አብርሃም እንዴት እንደፀለየ እንገነዘባለን። በአጠቃላይ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ እምነት ታሪክ ሲሰራ መመልከት እንችላለን- እግዚአብሔር ከእንግዲህ እንዲያው በሕዋ ውስጥ የሚመላለስ ከእኛ እጅግ ርቆ የሚገኝ ሆኖ መታየቱ ይቀራል። የአብርሃምን አምላክ “የእኔ አምላኬ”፣ የግሌ ታሪክ አምላክ ፣ እርምጃዎቼን የሚመራ ፣ የማይተወኝን፣ የዘመኔ አምላክ፣ የቀኖቼ አምላክ፣ አብሮኝ የሚጓዝ አምላክ እና መለኮታዊ ጥበቃ የሚያደርግልኝ እግዚአብሔር መሆኑን ያረጋግጣል።

ይህ የአብርሃም ተሞክሮ በመንፈሳዊነት ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም የመጀመሪያ ከሆኑት ጽሑፎች በአንዱ ባሌዝ ፓስካል በተባለ ጸሐፊ የተመሰከረለት ነው። እንዲህ በማለት ይጀምራል- “የአብርሃም አምላክ ፣ የይስሐቅ አምላክ ፣ የያዕቆብ አምላክ በማለት ነው እንጂ የፍልስፍና እና የምሑራን አምላክ በማለት መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። እርግጠኛ መሆንን፣ ስሜትን፣ ደስታን፣ ሰላምን የሚሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው” በማለት ይናገራል። ይህ መታሰቢያ በትንሽዬ ወረቀት ላይ የተፃፈ እና ባሌዝ ፓስካል ከሞተ በኋላ በፈላስፋው ልብስ ውስጥ በድብቅ ተስፍቶ የተገኘ መልእክት ሲሆን ይህ አንድ ጥበበኛ የሆነ ሰው ስለ እግዚአብሔር ሊረዳው የሚችል የስነ-ልቦና መግለጫ ሳይሆን፣ ነገር ግን ህያው እና የእርሱን መገኘት የሚገልጽ ስሜት ነው። ፓስካል በመጨረሻም ያንን እውነት የተገናኘበትን ትክክለኛ ጊዜ ሲያስታውስ  እ.አ.አ ሕዳር 23/1654 ዓ.ም ምሽት ላይ እንደ ነበረ በወረቀቷ ላይ አስፍሮ ነበር።

“የአብርሃም ጸሎት በመጀመሪያ የሚገለጠው በተግባር ነው- አብርሃም ዝምተኛ የነበረ ሰው ሲሆን በእያንዳንዱ የጉዞ ምዕራፍ ላይ ለጌታው መሰውያ ይሰራል” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2570)። አብርሃም አንድ ቤተመቅደስ አልገነባም፣ ነገር ግን በእየመንገዱ ላይ ጉዞውን የሚያስታውስ መሰውያ እየሰራ ያልፍ ነበር። እግዚአብሔር አስገራሚ የሆነ አምልካ ነው፣ በሦስት እንግዶች አምሳያ ሲጎበኘው እርሱ እና ሣራ በደስታ ሲቀበሉ እና የልጃቸውን የይስሐቅ መወለድ ሲያበስር እንመለከታለን (ዘፍ 18.1-15)።

ስለዚህ አብርሃምን ከእግዚአብሔር ጋር ይተዋወቃል ፣ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የመከራከር ችሎታ ነበረው፣ ነገር ግን ሁል ጊዜም ታማኝ ነበር። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ይስሐቅን እንዲሠዋለት በጠየቀው ጊዜ እንኳን ታማኝ ነበረ።  እዚህ ላይ አብርሃም እምነቱን የኖረው በሌሊት ሰማይ ከዋክብት በሰማይ ላይ ሲያበሩ በሌሊት እንደ ሚጓዝ አንድ ድራማዊ የሆነ ጉዞ ነው። እግዚአብሔር አብርሃም ሙሉ በሙሉ ታማኝ መሆኑን በመገንዘቡ ልጁን ቀድሞውንም ቢሆን ለእግዚአብሔር ለመሰዋት ዝግጁ መሆኑን በመመልከቱ በልጁ ይሳቅ ላይ እጁን እንዳያነሳ እግዚአብሔር እጁን ይይዛል (ዘፍ 22 1-19)።

በእምነት መፀለይ ከአብርሃም እንማራለን -ማዳመጥ፣ መራመድ፣ እስከ መጨረሻው ድረስ መወያየት፣ ነገር ግን ሁል ጊዜም የእግዚአብሔርን ቃል ለመቀበል እና በተግባር ለማዋል ፈቃደኛ እንድንሆን አብርሃም ያስተምረናል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
03 June 2020, 13:21