ሴት ምዕመናን ቤተክርስቲያንን ለማገልገል መሃላ ሲገቡ፣ ሴት ምዕመናን ቤተክርስቲያንን ለማገልገል መሃላ ሲገቡ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሴቶች ቤተክርስቲያንን በምህረት እና በርህራሄ እንዲያገለግሉ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያንን በንጽህና ሕይወት ለማገልገል ሙሉ ሕይወታቸውን የሚሰጡ እህቶቻችንን አስመልክቶ የወጣው ደንብ ሃምሳኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግር፣ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ሕይወታቸውን የሚሰጡት ሴቶች በምህረትን እና በርህራሄ የተሞሉ፣ ለቤተክርስቲያን አንድነት የሚቆረቆሩ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእነዚህ እህቶቻችን መንፈሳዊ ጥሪ፣ የተስፋ ምልክት እና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት የሚገልጹበት መንገድ ነው ብለው፣ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን በንጽህና ሕይወት ለማገልገል የሚፈልጉ ሴቶቸውን በመክፈት ለአገልግሎት የሚያነሳሳቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

በሚኖሩበት አገር፣ ከሀገረ ስብከታቸው ጳጳሳት በሚሰጥ ድጋፍ በመታገዝ ቤተክርስቲያንን በንጽህና ሕይወት ለማገልገል ጥሪን የተቀበሉ እህቶቻችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህ መንፈሳዊ ጥሪያቸው ብርታትን የሚያገኘው ከቤተክርስቲያን አንድነት እና የእህትማማችነት መንፈስ ዘላቂ ሆኖ በግልጽ መታየት ሲችል ነው ብለዋል። ትንቢታዊ ባህርይ ያለበት የቤተክርስትያን አገልግሎት ጥሪ ማደግ አለበት ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለአገልግሎት የተጠሩትም ቤተክርስቲያንን እንዲመለከቱ በሚያስችላቸው በእግዚአብሔር ምህረት ስለ ተሞሉ ነው ብለዋል። 

በንጽሕና ህይወት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሙሉ ሕይወታቸውን የሚሰጡ እህቶቻችንን አስመልክቶ የወጣው ደንብ ሃምሳኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ስብከት፣ ለአገልግሎት የሚያበቃቸው ሃላፊነት ሁሉን ሰው እንዲወዱ፣ በተለይም በችግር እና በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ርህራሄን እንዲያሳዩ ይጋብዛል ካሉ በኋላ በንጽሕና ሕይወት ለማገልገል የሚገቡት ቃል ኪዳን፣ ቤተክርስቲያን ድሆችን እንድትወድ፣ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ድህነት ያጋጠማቸውን እንድትረዳቸው፣ የአካል እና የአዕምሮ ሕመም የደረሰባቸውን፣ አቅመ ደካሞችን እና ወጣቶችን፣ ከማኅበረሰቡ መካከል ለተገለሉት እርዳታን እንድታደርግላቸው ያግዛል ብለዋል። በንጽህና ሕይወት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ጥሪ የደረሳቸው ሴት ምዕመናን የምሕረት እና የርህራሄ ምልክት በመሆን፣ በፍቅር እና በርህራሄ የተሞላ ለውጥን የሚያመጡ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመካከላችን የሚታየውን የኑሮ አለመመጣጠን እንድናስወግድ ጥሩ ትምህርት ሆኖናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ቤተክርስቲያንን በንጽሕና ሕይወት ለማገልገል ጥሪን የተቀበሉት እህቶቻችን በሙሉ በዘመናችን በሰዎች ላይ የሚደርሱ ስቃዮችን ዓይናቸውን ከፍተው እንዲመለከቱ አሳስበው፣ ከዚህ ስቃይ ለማምለጥ ጥረት ከማድረግ ይልቅ የስቃዩ ተካፋይ በመሆን መፍትሄዎችን በማፈላለግ ዘወትር ጥረት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ ቤተክርስቲያንን በንጽሕና ሕይወት ለማገልገል ጥሪን የተቀበሉት እህቶቻችን ቤተክርስቲያንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ የሚያደረጋት የፍቅር፣ የእናትነት እና የንጽሕና ምልክት እንዲሆኑ አሳስበው፣ ለሰዎች በሙሉ እህቶች እና ወዳጆች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል። በዓለማችን የገነነውን ጥላቻ እና ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀምን ለመዋጋት በጥበብ የተሞሉ እንዲሆኑ አሳስበዋል። 

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በንጽሕና ሕይወት ለማገልገል ጥሪን የተቀበሉት እህቶች ያላገቡ፣ በንጽህና ሕይወት በመኖር ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለቤተክርስቲያን በመታዘዝ የሚኖሩ መሆናቸው ሲታወቅ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን በአምስቱም አህጉራት በቁጥር ከ5000 በላይ አባላት መኖራቸው ታውቋል።     

02 June 2020, 18:34