በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ባዚሊካ፤ በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ባዚሊካ፤ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ችግረኛ ቤተሰቦችን የሚያግዝ መረዳጃ ማኅበር አቋቋሙ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ በማቋረጥ ችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለማገዝ የሚያስችል “መለኮታዊው ሠራተኛ ኢየሱስ” በሚል ስም የሚጠራ መረዳጃ ማኅበር ማቋቋማቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመረዳጃ ማኅበሩ አንድ ሚሊዮን ዩሮ የመጀምሪያ ዕርዳታ ማድረጋቸው ታውቋል። ዕርዳታው በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ሥራ በማቋረጣቸው ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ቤተሰቦችን ለማገዝ እንደሆነ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ዴ ዶናቲስ በላኩት መልዕክታቸው፣ በሮም ከተማ በችግር ውስጥ የሚገኙትን እናግዝ ብለው፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የዕርዳታ እጃቸውን በማስተባበር፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙትን በመርዳት መልሶ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የቫቲካን ዜና፤

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሮም ከተማ ውስጥ ለችግር የተጋለጡ በርካታቤተሰቦች መኖራቸው ይታወቃል። መልሶ የማቋቋም ሥራ የሚጀምረው ጉዳቱ የከፋባቸውን፣ የዕለት ቀለባቸውን አጥተው ዕርዳታ በመለመን ላይ የሚገኙትን፣ በማኅበረሰቡ መካከል ተረስተው ለቀሩት የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በማድረግ መሆኑ ታውቋል። የርካታ ቤተሰቦች የኑሮ ሁኔታ ያሳሰባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በድህረ ኮሮና ቫይረስ ውረርሽ ወቅት እርዳታን ለሚሹ ቤተሰቦች ዕርዳታን ለማዳረስ የሚያስችል የምክር ቤት ማቋቋማቸው ይታወሳል። በሮም ከተማ ውስጥ ዕርዳታን በመለመን ላይ የሚገኙ ቤተሰቦች መኖራቸውን የተገነዘቡት ቅዱስነታቸው አስቸኳይ እርዳታን ለማድረስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ዕርዳታው እጅግ ለተጎዱት ይሆናል፣

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለ“መለኮታዊው ሠራተኛ ኢየሱስ” መረዳጃ ማኅበሩ የተሰጠው የአንድ ሚሊዮን ዩሮ የመጀመሪያ ዙር እርዳታ፣ በሮም ከተማ ውስጥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቁት፣ በተለይም የቀን ሠራተኞች፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞች እና በጥቃቅን የጉልበት ሥራ የሚተዳደሩትን ለማገዝ የታቀደ መሆኑ ታውቋል። ሕጻናት ያሏቸውን በርካታ እናቶች እና አባቶች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ዴ ዶናቲስ በላኩት መልዕክታቸው፣ ልጆቻቸውን መመገብ ላልቻሉ ቤተሰቦች አቅም የፈቀደውን ፈጣን እርዳታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ እያንዳዱ ሰው የቻለውን እርዳታ በማድረግ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙትን ቤተሰቦች ለማገዝ ኅብረት መፍጠሩ ደስ የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

እገዛው ማኅበራዊ ጥቅም ያለው ይሆናል፣

ብዙ ሰዎች የእርዳታ እጃቸውን ለመዘርጋት እንደሚፈልጉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እርዳታው ደሆችን በማገልገል ላይ ላሉት፣ በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተይዘው በህመም ለሚሰቃዩት የህክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሞያዎች ጭምር እንደሚሆን ገልጸው ማንም ከማኅበረሰቡ መካከል ተነጥሎ እንዳይቀር ማድረግ ማኅበራዊ ጥቅም ያለው እንዲሆን አሳስበዋል።

ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊገኝለት ያስፈልጋል፣

የመረዳጃ ማኅበር  መመስረቱ ቤተክርስቲያን ለተቸገሩት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት መፈለጓን ያመልክታል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ከተቀሩት ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያው ተቋማት ጋር በመተባበር ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ታደርጋለች ብለዋል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ተቋማት ባለ አደራዎችን ያስታወስሱት ቅዱስነታቸው፣ ጽንሰ ሃሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝብን ጥያቄ መመልስ ያስፈልጋል ብለው በተለይም በማኅበረሰቡ መካከል ችግር ውስጥ የወደቁትን በመርዳት እና ከጎናቸው በመሆን ከደረሰባቸው ችግር ወጥተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የአንደነት መልካም ውጤት፣

የኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ ላስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት እያንዳንዱ ሰው የሚችለውን ማግረግ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኙ ካህናት በንቃት በመሳተፍ፣ ለመረዳጃ ማኅበሩ የአቅማቸውን ያህል ዕዳታ በማድረግ እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል።

የካርዲናል ዴ ዶናቲስ ምስጋና፣

በሮም ሀገረ ስብከት የመረዳጃ ማኅበርን በማቋቋማቸው ለር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን ያቀረቡት የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዴ ዶናቲስ፣ የላሲዮ አውራጃ እና የሮም ከተማ ነዋሪዎች በመተባበር፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች ራሳቸውን የሚያቋቁሙበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል። ካርዲና ዴ ዶናቲስ በመጨረሻም፣ የ“መለኮታዊው ሠራተኛ ኢየሱስ” የመረዳጃ ማኅበር ምስረታ፣ ዓርብ ሰኔ 5/2012 ዓ. ም. ከረፋዱ 5፡00 ላይ በብዙሃን መገናኛዎች በኩል ይፋ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።   

10 June 2020, 17:06