ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “መንፈስ ቅዱስ በመንገዳችን ያበራልናል እንዲሁም ይደግፋል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  በግንቦት 09/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ በዕለቱ በተነበበውና “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሮአችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ። ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለ ሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ” (ዮሐንስ 14፡ 15-21) ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠ ተስፋ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “መንፈስ ቅዱስ በመንገዳችን ያበራልናል እንዲሁም ይደግፋል” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ

ኩቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮቻን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለተ ሰንበት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ 14፡15-21) ሁለት መሠረታዊ መልዕክቶችን ያቀርባል -ትዕዛዛቱን መጠበቅ እና የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ።

ኢየሱስ ለእርሱ ያለን ፍቅር ትዕዛዛቱን ከመጠብቅ ጋር ያገናኛል፣ እናም በዚህ የመሰናበቻ ንግግሩ ላይ “ብትወዱኝ ትዕዛዜን ትጠብቃላችሁ” (ዩሐንስ 14፡15) በማለት የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው። “ትዕዛዜን የሚቀበልና የሚጠብቀው እኔን ይወዳኛል” (ዮሐንስ 14፡ 21) በማለት አክሎ ይገልጻል። ኢየሱስ እንድንወደው ጠይቆናል ፣ ይህንን ጭብጥ በሚገባ ያብራራልናል፣ ይህ ፍቅር በእርሱ ፍላጎት ብቻ አይፈጸምም፣ ወይም በስሜት የሚፈጸም አይደለም፣ ነገር ግን የእርሱን መንገድ ማለትም የአባቱን ፈቃድ መፈጸምን ይጠይቃል። ይህ “እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ” በማለት ኢየሱስ በሰጠን የጋራ የፍቅር ትዕዛዝ ውስጥ ተገልጻል (ዮሐ 13፡34)። እርሱ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እንዲሁ እኔን ውደዱኝ” ብሎ አልተናገረም፣ ነገር ግን “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት ነበር የተናገረው። እኛ እርሱን መልሰን እንድንወደው ሳይሆን እርሱ እኛን እንዲሁ ይወደናል።  እናም የማይናወጥ ፍቅሩ በመካከላችን ተጨባጭ የህይወት ዓይነት እንዲሆን ይፈልጋል።

ደቀመዛሙርቱ በዚህ መንገድ እንዲጓዙ ለማገዝ፣ ኢየሱስ “ሌላ ጴራቂሊጦስ” ማለትም አፅናኝ ለመላክ ወደ አብ እንደሚፀልይ ቃል ገብቷል (ዮሐንስ 14፡16) በእርሱ ቦታ ሆኖ እነርሱን የሚከላከል እና እርሱን ማዳመጥ እንዲችሉ ልቦና የሚሰጣቸው እና የእርሱን ቃል በተግባር ላይ ማዋል እንዲችሉ ብርታት ይሰጣቸዋል። ወደ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚገባ የእግዚአብሔር ፍቅር ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ይህ ነው። ኢየሱስ ከሞተ እና ከሞት ከተነሳ በኋላ ፍቅሩ በእርሱ ለሚያምኑ እና በአብ ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም ለተጠመቁ ሁሉ ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ ራሱ ይመራቸዋል ፣ ያበራላቸዋል፣ ያጠናክራቸዋል፣ በዚህም እያንዳንዱ ሰው በሕይወቱ ውስጥም ቢሆን ፣ በመከራም እና በችግር ፣ በደስታ እና በሐዘን ውስጥ ፣ በእየሱስ መንገድ ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። ይህ እንዲፈጸም ለማድረግ ለመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተገዢ መሆን መጽናናትን ብቻ ሳይሆን የሚያስገኝልን፣ ነገር ግን የልብ መለወጥ፣ ወደ እውነት እና ፍቅር እንድናመራ ሊያደርገን ይችላል።

ሁላችንም የምንሠራውን የስህተት እና የኃጢአት ልምምድ ተገንዝቦ ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዳንሸነፍ ይረዳናል እናም የኢየሱስን ቃላት ትርጉም እንድንገነዘብ እና እንድንኖር ያደርገናል “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐንስ 14፡5) ይለናልና። ትእዛዛቶቹ እንደ አንድ መስታወት የእኛን ስህተቶች እና ክፉ ተግባራት ፍንትው አድርገው በማሳየት እንዲያንጸባርቁ ታስበው የተሰጡን አይደለም። እንዲ በፍጹም አይደለም! የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሕይወት ቃል ሆኖ ተሰጠን፣ እሱም ይለወጣል ፣ ያድሳል ፣ አይፈረድም ነገር ግን የሚፈውስ እና ዋና ዓላማው ይቅርታን ማድረግ ነው። ለእግራችን የሚያበራ ቃል ነው። እናም ይህ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው! እሱ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ፣ ነፃ ሰዎች እንድንሆን የሚረዳን ፣ እሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው፣ መውደድ እና መወደድ የምንፈልግ ሰዎች እንድንሆን፣ ሕይወት በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ጌታ ያደረገውን ድንቅ ሥራዎች የማወጅ ተልእኮ መሆኑን የተገነዘብን ሰዎች እንድንሆን ያደርገናል።

የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት ማዳመጥ እንደ ሚገባት ያወቀች እና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበለችሁ የቤተክርስቲያን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱስ ወንጌል በደስታ እንድንኖር ፣ ልብን የሚያሞቅ እና አካሄዳችንን የሚያበራል መለኮታዊ እሳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስ እንድንቀበል እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

17 May 2020, 17:59