ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክፋት ሕይወትን ምድረ በዳ ያደርጋል፣ ጽሎት የደረቀውን ያለመልማል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በግንቦት 19/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ ያደረጉት ሳምንታዊ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መተላለፉ ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ እና አራተኛ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዚሁ “የክርስቲያን ጸሎት” በሚል አርዕስት ቅዱስነታቸው በተከታታይ በማደረግ ላይ የሚገኙት የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ክፋት ሕይወትን ምድረ በዳ ያደርጋል፣ ጽሎት የደረቀውን ያለመልማል” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ስለጻድቅ ሰው ጽሎት እናወሳለን።

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው እቅድ እጅግ በጣም መልካም ነው፣ ነገር ግን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ክፉ ነገር መኖሩን እንመለከታለን። የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች በሰው ልጆች ሕይወት  ውስጥ ደረጃ በደረጃ ኃጢአት እየተስፋፋ መሄዱን ይገልፃሉ። አዳምና ሔዋን (ዘፍጥረት 3:3-7) የእግዚአብሔርን መልካም  የነበረ አሳብ በመጠራጠር እነሱ የተሻለ ደስታ ይሰጠናል ብለው ካሰቡት ቅናተኛ ከነበረው አካል ጋር ለመተባበር ያስባሉ። ስለሆነም አመጹ ፤ ከዚያን በኋላ የእነርሱን ደስታ በሚመኝው ለጋሽ በሆነው ፈጣሪ ማመን ያቆማሉ። ልባቸው ፣ ለክፋት ፈተና በመሸነፍ ፣ ሁሉን ቻይ እንደ ሆነው አምላክ ለመሆን ፈልገው “የዛፉን ፍሬ ከበላን እንደ እግዚአብሔር እንሆናለን” (ዘፍጥረት 3፡5) በማለት እንደ እርሱ ለመሆን ይመኛሉ። ነገር ግን ይህ ተሞክሮ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል። ዓይኖቻቸው ተከፍተው እርቃናቸውን መሆናቸውን ተገንዝበዋል (ዘፍጥረት 3፡7)።

ክፋት በሁለተኛው የሰው ልጅ ትውልድ ሕይወት ውስጥ የበለጠ የሚረብሽ ይሆናል - እሱ የቃየንና የአቤል ታሪክ ነው (ዘፍጥረት 4፡ 1-16)።  ቃየን በወንድሙ ይቀና ነበር፣ ምንም እንኳን የበኩር ልጅ ቢሆንም አቤልን እንደ ተቀናቃኝ አድርጎ ይመለከተው ነበር። በልቡ ውስጥ የክፋት መንፈስ ማንሰራራት ጀመረ፣ ቃየን ይህንን ሊቆጣጠረው አልቻለም። እናም የመጀመሪያዎቹ ወንድማማቾች ታሪክ የሚደመደመው በነፍስ ግዲያ ነው።

በቃየን የዘር ሐረግ ውስጥ እደ-ጥበባት እና ሥነ-ጥበባት እየጎለበተ የሄደ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዓመፅ እያደገ ሄዷል፣ ይህም የበቀል ስሜት በሚሰማው በላሜሕ  ግጥም ተገልጿል “አንድ ሰው ቢያቈስለኝ፣ ጒልማሳው ቢጐዳኝ፣ ገደልሁት፤ [...]  ቃየን ሰባት ጊዜ ቅጣት ይሰጠዋል፣ የላሜሕ ገዳይ ደግሞ ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ይጠብቀዋል” (ዘፍ. 4፡ 23-24) በማለት ይናገራል። እናም ክፋት ሙሉ ቅርጹን እስከሚይዝበት ጊዜ ድረስ እንደ ሰደድ እሳት ይሰራጫል፣ “እግዚአብሔር  አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ” (ዘፍጥረት 6፡5) ይለናል። በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተው የጥፋት ውሃ የሆነው የጎርፍ መጥለቅለቅ (ዘፍጥረት ምዕራፍ 6-7) እና የባቢሎን ግንብ መፍረስ (ዘፍጥረት ምዕ. 11) አዲስ የሆነ ፍጥረት ፣ በክርስቶስ ፍፃሜው እንደሚመጣ የሚያምን አዲስ ጅምር እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ።

ሆኖም  በነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች ውስጥ ፣ በጣም ጎልቶ የማይታይ፣ እጅግ በጣም ትሁት እና ትጉህ የሆነ ታሪክ ተገልጿል፣ ይህም እንደ ምንበዢ ተስፋ ማደረግን ይወክላል። ምንም እንኳን ሁሉም ሰው በጭካኔ የተሞላ ቢመስልም፣ ጥላቻን በማደጉ እና ይህም በሰው ልጆች ጉዳዮች ላይ ታላቅ የሆነ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን ቢቀጥልም የሰዎችን ዕጣ ፈንታ በተለየ መንገድ የመፃፍ ችሎታ ያላቸው ወደ እግዚአብሔር የሚጸልዩ ሰዎች ግን ነበሩ። አቤል ለእግዚአብሔር የበኩር መሥዋዕት አቀረበ። አቤል ከሞተ በኋላ አዳምና ሔዋን ሴት የሚባል ልጅ ወለዱ፣ ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው፣ የስሙ ትርጓሜ ሟች ማለት ነው። “በዚያን ጊዜ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ” (ዘፍጥረት 4፡26)። ከዚያ በኋላ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደርገ” እና ወደ ሰማይ የተነጠቀው፣ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም ያልተገኘው (ዘፍጥረት 5፣22.24) የሄኖክ ታሪክ ይገለጻል። በመጨረሻም  “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው የነበረ፣ በተጨማሪም አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ” (ዘፍጥረት 6፡9) እግዚአብሔር የሰውን ዘር የማጥፋት ዓላማውን ወደ ኋላ የቀለበሰ (ዘፍጥረት 6፣7-8) የኖኅ ታሪክ እናገኛለን።

እነዚህን ታሪኮች በማንበብ ፣ አንድ ሰው በዓለም ላይ እየተስፋፋ ከመጣው የክፋት ጎርፍ ጎን ለጎን ጸሎት መሳሪያ እና የሰው ልጅ መሸሸጊያ ነው የሚል ግንዛቤ ያገኛል። ራሳችን ከራሳችን ለማዳን መጸልይ ተገቢ እንደ ሆነ መመልከቱ በራሱ መልካም ነው። የመፅሃፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች ውስጥ የሚገኙ ጸሎቶች ለሰላም የሚሰሩ ሰዎች እንደ ነበሩ ያሳዩናል፣ በእውነቱ  ጸሎቱ እውነተኛ ከሆነ፣ ከዓመፅ ድርጊቶች ነፃ የሚያደግ እና የሰውን ልብ መንከባከብ ወደ ሚችለው ወደ እግዚአብሔር የሚያመልክት ሊሆን የገባዋል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ “የዚህ ዓይነቱ ጸሎት በሁልም ሐይማኖቶች በብዙ ጽድቃን ሰዎች ሲዘወተር ኖሮአል” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2569) ይለናል። የሰው ልጅ ጥላቻ ምድረ በዳ እንዲስፋፋ የማድረግ ችሎታ ያለው ሲሆን ጸሎት ደግሞ ምድረ በዳው ዳግም እንዲለመልም የማደረግ ብቃት አለው።

የእግዚአብሔር ጌትነት በዓለም ላይ ብዙውን ጊዜ በተሳሳተ ወይም በጥላቻ መንገድ ሰንሰለት ውስጥ በመራመድ ላይ በሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች ውስጥ የሚያልፈው ለዚህ ነው። ነገር ግን ዓለም የሚኖረው እና የሚያድገው ለእግዚአብሔር ኃይል ምስጋና ይግባውና እርሱን በጸሎት በማገልገል ላይ በሚገኙ አገልጋዮቹ ምክንያት ነው። እነሱ በቅደም ተከተል የተቀመጡ አይደሉም፣ እነሱ በአርዕስተ ዜናዎች ላይ እንብዛም የሚታዩ አይደሉም፣ በመተማመን ለአለም የሚጸልዩ ሰዎች ናቸው።

በእግዚአብሔር ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር መንገድ በእነሱ መካከል አልፏል፣ ታላቅ ከሆነው ሕግ ጋር ለማይስማማው፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ተዓምራቱን እንዲያከናውን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንዲለወጠው እና ረፍት እንዲሰጠው በጠየቀው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያልፋል፣ ድንጋይ የነበረውን ልብ፣ ስጋ ወደ ሆነ ልብ ለመለወጥ ያልፋል (ሕዝቄል 36፡26)።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 May 2020, 12:16