ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ጸሎት ለተስፋ በር ይከፍታል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በግንቦት 12/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ ያደረጉት ሳምንታዊ አስተምህሮ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መተላለፉ ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ እና ሦስተኛ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዚሁ “የክርስቲያን ጸሎት” በሚል አርዕስት ቅዱስነታቸው ያደረጉት አስተምህሮ “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው!” (መዝሙር 8፡3-4.10) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን “ጸሎት ለተስፋ በር ይከፍታል” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በፍጥረት ምስጢሮች ላይ በማሰላሰል ከዚህ ቀደም በጸሎት ላይ ዙሪያ ላይ የጀመርነውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬ እንቀጥላለን። ሕይወት  የእኛን የመኖር ሁኔታ በእውነት በመግለጽ የሰውን ልብ ለጸሎት ይከፍታል።

የመፅሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጽ ከታላቅ የምስጋና ግጥም ጋር ይመሳሰላል። የፍጥረት ታሪክ አሁን ያለው ነገር ሁሉ መልካምነት እና ውበት ቀጣይነት በሚረጋገጥበት መልኩ በመግለጽ ላይ የተደገፈ ነው። እግዚአብሄር በቃሉ ወደ ሕይወት ይጠራል፣ ሁሉም ነገር ሕልውናውን ያገኛል። በቃሉ ብርሃንን ከጨለማ ይለየዋል ፣ ቀንና ሌሊትን ተለዋጭ ያደርገዋል ፣ ወቅቶችን ይለውጣል ፣ የተለያዩ ዕፅዋትና እንስሳት በተለያዩ ቀለማት እንዲያሸበርቁ አድርጎ በመፍጠር ውብ የሆነ የቀለም ቤተ-ስዕል የመሰለ ነገር ይከፍታል። አለመግባባትን በፍጥነት በሚያሸንፍ በዚህ ጫካ ውስጥ ሰው በመጨረሻ ላይ ይታያል። እናም ይህ ግልጸት እርካታ እና ደስታን የሚያሰፋ ከመጠን በላይ የደስታ ስሜት ያስከትላል “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” (ዘፍ 1፡31)። ጥሩ ነገር ፣ ነገር ግን ደግሞ ቆንጆ: - የሁሉንም ፍጥረታት ውበት ማየት ይቻላል!

የፍጥረት ውበት እና ምስጢር ፀሎትን የሚቀሰቀስ የመጀመሪያውን እንቅስቃሴ በሰው ልብ ውስጥ ይፈጥራል (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2566)። በመጀመርያ የሰማነው ከመዝሙረ ዳዊት ስምንተኛው ምዕራፍ ላይ የተወሰደው ምንባብ እንዲህ ይላል: - “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?!” (8፡3-4) ይላል። የሚፀልይ ሰው በዙሪያው ያለውን ምስጢር ያሰላስላል ፣ ከከዋክብት በላይ ያለውን በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ያያል - በአሁኑ ወቅት የሚገኘው አስትሮፊዚክስ (የኳክብት ተመራማሪዎች) እጅግ ውብ መሆኑን ያሳየናል፣ ከዚህ የፍቅር ስዕል ከሚመስል የሰማይ ሥራ ጥበብ በስተጀርባ ያለው አስገራሚ ነገር ምንድነው! በጣም ኃያል ነው! ... እናም በዚህ ወሰን በሌለው ሰፊ ከሆነው ሰማይ ጋር ሲነጻጸር ሰው ምንድነው? “ሰው ከንቱ” (መዝሙር 89፡48) መሆኑን መዝሙረ ዳዊት ይናገራል፤ አንድ የተወለደ ፍጥረት ፣ የሚሞት ፍጡር ፣ እጅግ በጣም ደካማ ፍጡር ነው ሰው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሁሉ ፣ እንዲህ ያለው የውበት ንፅፅር ግንዛቤ ያለው ብቸኛው ፍጡር ሰው ነው። አንድ የተወለደ ትንሽዬ ፍጡር፣ የሚሞት፣ ዛሬ ያለ ነገ የማይኖር ትንሽዬ ፍጡር፤ ነገር ግን እርሱ ብቻ ነው ይህንን የሚያውቀው። እኛ ይህንን ውበት እናውቃለን።

የሰው ጸሎት ከመደነቅ ስሜት ጋር በቅርብት የተቆራኘ ነው። የሰው ልጅ የአጽናፈ ሰማይ መጠን ጋር ሲነፃፀር መጠኑ አነስተኛ ነው። የእሱ ታላላቅ ግኝቶች በጣም ትንሽ ይመስላሉ ... ነገር ግን ሰው ከንቱ አይደለም። በጸሎት የምህረት ስሜት ተረጋግጧል። በአጋጣሚ የተፈጠረ ምንም ነገር የለም - የአጽናፈ ዓለሙ ምስጢር አንድን ሰው በዓይናችን ውስጥ በሚገናኝበት መልካም እይታ ውስጥ ይገኛል። ዘማሪው ዳዊት እንደሚገልፀው “ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው” (መዝሙር 8፡ 6) በማለት ይናገራል።  ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት የሰውን ታላቅነት ይገልጻል፣ ዙፋን ይቀዳጃል። በተፈጥሮ እኛ ምንም አይደለንም ፣ ትንሽም ነን ፣ ዛሬ አለን ነገ ደግሞ የለንም፣ ይህም የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በጥሪ የታላቁ ንጉስ ልጆች ነን!

ብዙዎቻችን ያጋጠመን ተሞክሮ ነው። የህይወት ታሪክ ተግዳሮት ሲያገጥመን፣ ከሁሉም ከሚያጋጥመን ምሬት ጋር ተዳምሮ አንዳንድ ጊዜ በውስጣችን ያለው የጸሎት ስጦታ እንዲቀንስ የማደረግ አደጋ ይደቅናል፣ በዚህን ጊዜ በከዋክብት የተሞላ ሰማይን ማሰብ ፣ የፀሐይ መጥለቅን፣ የአንድ አበባ ውበትን መመልከት ... ወዘተ የምስጋና ስሜትን እንደገና ለመቀስቀስ በቂ ነው። ይህ ልምምድ ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጽ መነሻ ሊሆን ይችላል። ሰው ምንድነው።

ታላቁ የፍጥረት ታሪክ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባ ሲዘጋጅ ፣ የእስራኤል ህዝብ የደስታ ቀናት እያሳለፉ አልነበሩም። የጠላት ኃይል ምድራቸውን ተቆጣጥሮ ነበር፣ ብዙዎች ከምድራቸው ተባረዋል፣ ብዙዎች ደግሞ በባርነት ቀንበር ሥር ነበሩ። የትውልድ አገር፣ ቤተ መቅደስ ፣ ማህበራዊ እና ሀይማኖታዊ ሕይወት ፣ ምንም አልነበራቸውም ነበር።

ሆኖም ከፍጥረት ታላቅ ታሪክ ጀምሮ አንድ ሰው የምስጋና ምክንያቶች መፈለግ ይጀምራል፣ አንድ ሰው ስለተሰጠው ሕልውና እግዚአብሔርን ማመስገን ይጀምራል። ጸሎት የመጀመሪያው የተስፋ ኃይል ነው። ስትጸልይ ተስፋህ ይለመልማል፣ እያደገም ይሄዳል። ጸሎት ለተስፋ በር ይከፍታል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የጸሎት ሰዎች መሠረታዊ እውነቶችን ይጠብቃሉ ፣ እነሱ እራሳቸውን እና ከዚያም ለሌሎች በመጸለይ ይህ ሕይወት ምንም እንኳን ጥረቶች እና መከራዎች ቢኖሩትም ፣ ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቀናት ቢኖሩትም ፣ በሚያስደንቅ ፀጋ የተሞላ እንዲሆን ይጸልያሉ። እናም እንደዚያ ሁል ጊዜ መከላከል እና መጠበቅ አለበት።

የሚጸልዩ ወንዶች እና ሴቶች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ጠንካራ እንደሆኑ ያውቃሉ። ፍቅር ከሞት የበለጠ ኃያል ነው ብለው ያምናሉ ፣ እኛ በማናውቃቸው ጊዜያት እና መንገዶች እንኳን አንድ ቀን በእርግጥ መከራ ይሸነፋል ብለው ያምናሉ። የጸሎት ሰዎች በፊታቸው ላይ የብርሃን ነፀብራቅ ይታያል፣ ምክንያቱም በጣም ጨለማ በሚባሉ ቀናት እንኳ ሳይቀር ፀሐይ ብርሃኗን አታቋርጥም። ጸሎት ብሩህ እንድትሆን ያደርግሃል፣ ነፍስህን ያበራ፣ ልብህን ያበራ እናም ፊትህ እንኳን ሳይቀር እንዲበራ ያደርጋል። በጣም ጨለማ በሆኑ ጊዜያት፣ በጣም አሳዛኝ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ እንኳን ሳይቀር ያበራል።

ሁላችንም ለደስታ ነው የተጠራነው። ስለዚህ ጉዳይ አስባችሁ ታውቃላችሁ ውይ? ደስታ ሰጭ እንደሆንክ ታውቃለህ ወይ? ወይስ የሚያሳዝኑ መጥፎ ዜናዎችን ማምጣት ትመርጣለህ? ሁላችንም ደስታን የማምጣት ችሎታ አለን። ይህ ሕይወት የፈጠረን እግዚአብሔር የሰጠን ስጦታ ነው፣ እናም በሀዘን እና በብስጭት ውስጥ ስንገባ ይህንን ሕይወት በጣም እናሳጥረዋለን። እንዲህ ሁነን በመኖራችን ተደስተን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። እኛ ጽንፈ ዓለሙን እንመለከታለን ፣ ውበቶቹን እንመለከታለን፣ እንዲሁም መስቀሎቻቸውንንም እንቃኛለን እናም እኛ ግን “አንተ ነህ ይህንን ድንቅ ነገር ለእኛ አደረክልን” ብለን እናመሰግነዋለን። እናም እግዚአብሔርን ለማመስገን እና ለማወደስ ወደ ሚመራኝ የልብ መረጋጋት ስሜት እንዲሰማኝ ለማድረግ እኛ ፍጥረታት ሁሉ የእርሱ አሻራ ያረፈባቸውን ፍጥረታት ሁሉ በማየት የታለቁ ንጉሥ ልጆች መሆናችንን በማሰብ በጸሎት እርሱን ልናመሰግነው ይገባል። ጌታ ይህንን በጥልቀት መረዳት እንድንችል እና እርሱን “አመሰግንሃለሁ” ወደ ሚለው ውብ ጸሎት እንዲመራን በጸሎት ልንማጸነው ይገባል።

20 May 2020, 12:04