ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን መጋራት ያስፈልጋል አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ ለ54ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ሕዝቦች በጋራ ሆነው አንዱ ለሌላው ደህንነት በማሰብ ገንቢ የሆኑ መረጃዎችን በመለዋወጥ ታርክን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ፣ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በበኩላቸው፣ በመልካም የሚቀባበል እና እርስ በእርስ የሚደጋገፍ ማህበረሰብን መገንባት የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ቀዳሚ ዓላማ ነው ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ ማኅበራዊ መገናኛ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ብዙኅን መገናኛዎች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የሁለቱንም ወገን፣ የመልዕክት ላኪውን እና የመልዕክት ተቀባዩን ደህንነት ያገናዘቡ ፣ ለመጭው ጊዜ ተስፋን የሚሰጡ መሆን አለባቸው ብለዋል። የካቶሊካዊ ጋዜጠኞ ባልደረባ የሆነው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዴ ላሳል በዓል ተከብሮ በዋለበት በጥር 15/2012 ዓ. ም. ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የታሪክን ጭብጥ ለሌሎች መናገር” የሚለው የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የብዙሃን መገናኛ ቀን መሪ ቃል፣ እርስ በእርስ ጠቃሚ እና ገንቢ የሆኑ መረጃዎችን በመለዋወጥ፣ የጋራ ታሪካችንን አውቀን በወንድማማችነት መንፈስ ተቀራርበን የነገን መልካም ተስፋ እንድንመለከት ያግዛል ብለዋል።       

ማኅበራዊ መገናኛ አንድነትን እንጂ ልዩነትን የሚያመጣ መሆን የለበትም፣

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒም በበኩላቸው፣ ማኅበራዊ መገናኛ አንድነትን የሚፈጥር እንጂ ልዩነትን የሚያመጣ መሆን የለበትም ብለው፣ ዘንድሮ በተከበረው 54ኛ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀንን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ያስተነተኑት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የሚሰራጩ መልዕክቶች ግልጽ እና እውነት መሠረት ያደረጉ መሆን አላባቸው በማለት በፌስ ቡክ እና በዩ ቲዩብ ባስተላለፉት መልዕክት አስገንዝበዋል።    

አዲስ ታሪክ መልበስ

“እውነተኛ የታሪክ ጭብጥ ለሌሎች መናገር” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት የተመለከቱት፣ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ መልዕክትን መጋራት ስንል ከሁሉ በፊት የግል ታሪካችንን ከሌሎች ጋር መጋራት፣ የሌሎችንም ታሪክ ማድመጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ፣ እርስ በእርስ የሚደረግ የመልዕክት ልውውጥ ሌሎችን የሚጠቅም እና የሚያንጽ እንዲሆን ለማድረግ ከሁሉ በፊት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላክልንን የድነት መንገድ የተላበሰ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም “ሕይወታችንን ማደስ የምንችለው ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚመጣው የእውነት ቃል ነው” ማለታቸውን ዶ/ር ሩፊኒ አስታውሰዋል። አክለውም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለተረበሸው ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላክ የድነት ቃል ትክክለኛ አቅጣጫን በማመልከት መጽናናትን ሊያስገኝልን ይችላል ብለዋል። የዲጂታሉ ዓለም የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም በሕዝቦች መካከል ያለውን ርቀት በመቀነስ፣ ከዚህ በፊት የነበረውን የሰዎች አካላዊ ቅርበት ያስወገደ መሆኑን አስታውሰዋል።

ከእግዚአብሔር ጋር የመነጋገር ውበት፣

አንድነትን የሚያጠናክሩ ብዙ ተነሳሽነቶች ብናሳይም ​​“ቂም እና ጭፍን የጥላቻ አመለካከቶች እያደጉ መምጣታቸው ያሳዝናል” ያሉት ዶ/ር ሩፊኒ ፣  ይህን ማሸነፍ የሚቻለው የእርስ በእርስ ውይይት አስፈላጊነት በመገንዘብ ከእግዚአብሔር ጋር በግልጽ ተገናኝተን በመነጋገር ነው ብለው፣ እርስ በእርስ የመነጋገር ልማድ የማናሳድግ ከሆነ፣ ጥበብን እና እውቀትን የማንለዋወጥ ከሆነ የጋራ ታሪካችንን ልናጣው እንችላለን ብለዋል።     

ተስፋችን ምን ላይ ይሁን?

እርስ በእርስ የምንነጋገርበት ዋና ዓላማ መልካም ወይም ክፋ የሆኑ ነግሮችን ለይቶ ለማወቅ ነው ያሉት ዶ/ር ሩፊኒ፣ እምነትን ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ የብዙሃን መገናኛዎች ላይ መጣል እንደ ሌለብን እና ብዙሃን መገናኛዎች ትክክለኛ አቅጣጫን እንዲይዙ መንገድ ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል። በብዙሃን መገናኛዎች ላይ ሃላፊነት ሊኖረን ይገባል ያሉት ዶ/ር ሩፊኒ፣ ምን ጊዜም ቢሆን የሐሰት ወሬዎች መሣሪያ ሊንሆን አይገባም ብለው በኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ የተጎዳውን ማኅበራዊ አንድነት መልሰን ለመጠገን ጥበብ እና በጎ ፈቃደኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንግዳ ተቀባይ ማኅበረሰብ መገንባት ያስፈልጋል።

አዳዲስ ውስጣዊ አመለካከቶቻችን እውነትን እንድንመሰክር ያነሳሱናል ያሉት ዶ/ር ሩፊኒ፣ በወንዳማማችነት መንፈስ እርስ በእርስ በእንግድነት የሚቀባበል እና የሚደጋገፍ ማኅበረሰብ መገንባት ያስፈልጋል ብለው፣ ይህን ለማድረግ መልካም ፍሬን የሚያፈራ መልካም ዘር በመልካም እርሻ ላይ መዝራት ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 18/2012 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁሉ ሰው ጥሪውን ለይቶ የሚያውቅበትን መድረክ ማዘጋጀት፣ እርስ በእርስ በእንግድነት የሚቀባበሉበትን ወንድማማችነት መንፈስ ለማሳደግ መጠራታቸውን እንዲያውቁ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል ማለታቸውን እና ዲጂታል ማኅበራዊ መገናኛዎች ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ኅብረትን ለማሳደግ እንጂ ልዩነትን ለመፍጠር እንዳልሆነ ቅዱስነታቸው መናገራቸውን ዶ/ር ሩፊኒ አስታውሰዋል።                

25 May 2020, 18:16