“ከኢየሱስ ጋር ከሆኑ ፈተናዎችን ማሸነፍ እንደሚቻል ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስተምረውናል”።

ትናንት ግንቦት 10/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልደት መቶኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖላንድ፣ ለክራኮቪያ ወጣቶች የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለክራኮቪያ ወጣቶች በላኩት መልዕክታቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልደት መቶኛ ዓመት ከክራኮቪያ ወጣቶች ጋር ለመገናኘት መልካም አጋጣሚን እንደ ፈጠረላቸው ገልጸው፣ እንደ ጎርግሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2016 ዓ. ም. በፖላንድ አገር ክራኮቪያ ከተማ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫልን አስታውሰዋል።  

የቫቲካን ዜና፤

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመላዋ ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን እና ለፖላንድ አገር ልዩ የእግዚአብሔር ስጦታ ነበሩ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ምድራዊ ጉዞ በፖላንድ አገር፣ ቫዶቪች መንደር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በግንቦት 18/1920 ዓ. ም. ተጀምሮ፣ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በሮም ያከተመ፣ ለሕይወት ባለው ፍቅር፣ ለዓለም እና ለሰው ልጅ አስደናቂ የእግዚአብሔር ምስጢር የተገለጠበት ነበር ብለዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እንደ ታላቅ ምሕረት አስታውሳቸውዋለሁ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም ጋር አያይዘው “ምሕረት የበዛበት” የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክታችውን፣ የቅድስት ፎስቲና የቅድስና አዋጅን እና መለኮታዊ የምሕረት እሑድ ምስረታን አስታውሰዋል።  ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእግዚአብሔርን ፍቅራዊ ምሕረትን ከልብ ተረድተዋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም በተጨማሪ የሰዎችን ባሕላዊ እና ማኅበራዊ የኑሮ ሁኔታን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሕጻናትን፣ የወጣቶችን እና የአዋቂዎችን አስፈላጊነት የተረዱ መሆናቸውን የሴቶች እና የወንዶች ጥሪ ልዩ ውበት ያወቁ ናቸው ብለው ይህን ጥሪ ሁሉ ሰው ፣ እናንተ ወጣቶችም ቀምሳችሁ ማየት ትችላላችሁ ብለዋል። ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሕይወት ከኢንተርኔት በማንበብ መረዳት የሚችችሉ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ውድ ወጣቶች ሆይ! እያንዳንዳችሁ የወላጆቻችሁን የሕይወት ልምድ ከነ ስቃያቸው እና ደስታቸው ጋር በማድረግ ተሸክማችሁ ትጓዛላችሁ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቤተሰብ ፍቅር እና እንክብካቤ ዋና ተሰጥዖዋቸው ነው ብለው፣ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ አስተምህሮች በዚህ ዘመን ቤተሰብን ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች እና ፈተናዎች ተጨባጭ መፍትሄዎችን ለማግኘት የሚረዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“በግልም ሆነ በቤተሰብ ላይ የሚደርሱ ችግሮች በቅድስና መንገድ ላይ እንቅፋት ሊሆኑ አይችሉም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በልጅነት ዕድሜው እናቱን፣ ወንድሙን እና አባቱን በሞት ለተለያቸው ለወጣት ካሮል ዎይቲላ ወይም ለቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቅድስና ሕይወት እንቅፋት ያልፈጠሩባቸው መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በተማሪነት ዕድሜአቸው የናዚዎችን ግፍ እና ጭቆና በሚገባ ተገንዝበዋል ብለው፣ ብዙ ጓደኞቻቸውም በጦርነት ምክንያት በሞት ሲለዩአቸው ተመልክተዋል ብለዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከጦርነቱ በኋላም በክህነት እና በጵጵስና የአገልግሎት ዓመታት አምላክ የለሽ የኮሚኒስት ሥርዓትን የተጋፈጡ መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል።

ጠንከር ያሉ ችግሮች ለወጣትነት ዕድሜ እና ለእምነት ጎዳና ትልቅ ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ፈተናዎች ማሸነፍ የሚቻለው ሞትን አሸንፎ በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመበርከክ ነው ብለዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ሬደምቶር ኦሚኒስ”፣ ሲተረጎም “የሰው ልጅ አዳኝ” በሚለው የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ “ራሱን በሚገባ ማወቅ የሚፈልግ ማንም ሰው ከውስጥ መሸበር እና ጥርጣሬ ፣ ድክመት እና ኃጢአት ፣ ሕይወት እና ሞት ጋር ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ መቅረብ አለበት” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ውድ ወጣቶች ሆይ! ይህን ችሎታ ለእያንዳንዳችሁ እመኛለሁ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወጣቶች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲቀርቡ አደራ ብለው በማከልም “የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልደት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ፣ አሸናፊ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በድፍረት መጓዝ እንድትችሉ ኃይል ይሁናችሁ ብለዋል”። መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ሐዋርያት እጃቸውን አንስተው እንደ ተቀበሉት ሁሉ እግዚአብሔር የእያንዳንዳችን እጆች ለእርቅ፣ ለአንድነት እና ለሥራ እንዲነሱ፣ ታላቅ ተአምርን እንዲሠሩ፣ በሕይወታችሁ ለውጥን እንድታሳዩ ይፈልጋል” ብለዋል። የዛሬውን ዓለም በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነቡ እግዚአብሔር የወጣቶችን እጅ እንደሚፈልግ ገልጸው፣ በፖላንድ ለክራኮቪያ ወጣቶች በላኩት መልዕክታቸው፣ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አማላጅነት ለምነው ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን የላኩላቸው ሲሆን፣ ወጣቶች በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።   

19 May 2020, 08:57