ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለአውሮፓ ሕብረት አንድነት እና በአፍሪካ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት  02/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ህንጻ ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ በእለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና በተለይም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳበት የትንሳኤ በዓል ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ የሚደገመውን “የሰማይ ንግስት ሆይ ደስ ይበልሽ፣ እርሱ እንደ ተናገረው ከሙታን ተነስቷል” የሚለውን ጸሎት እኩለ ቀን ላይ ከደገሙ በኋላ እንደ ተለመደው ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልዕክት በአውሮፓ እና የአፍሪካ አህጉራት ላይ መሰረቱን ያደረገ መልዕክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“የዛሬ መልዕክቴ ሐሳብ ወደ አውሮፓ እና ወደ አፍሪካ ይሄዳል። ወደ አውሮፓ ምክንያቱም እ.አ.አ. ግንቦት 9 /1950 ዓ.ም ላይ የሹማን መግለጫ 70ኛ ዓመት መታሰቢያ ተከብሮ በማለፉ (ግንቦት 01/2012 ዓ.ም “የአውሮፓ ቀን” መከበሩ ይታወሳል። እ.ኤ.አ. ግንቦት 9 /1950 ዓ.ም የዛሬ 70 አመት ገደማ ማለት ነው በወቅቱ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሮበርት ሹማን የአውሮፓ አገራት የድንጋይ ከሰል እና የአልሙኒየም እቃዎችን በማምረት ሂደት ውስጥ አንድነትን እንዲፈጥሩ ሐሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል። ዓላማው በኢኮኖሚ እድገት ሂደት ውስጥ ያሉ አገራት ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን አንድ ላይ በማምጣት በአውሮፓ አገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንድነት እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸው ጽንሰ-ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለበት ወቅት ነበር። በዚህ መንገድ ነበር እንደ ፈረንሣይና ጀርመን ባሉ ታሪካዊ ተቀናቃኝ አገራት በነበሩ መካከል ይደረግ የነበረው ጦርነት የሮበርት ሹማንን ቃላት በመጥቀስ - እንኳን ለመተግበት ይቅርና ሊታሰብ የማይችል የነበረው ግጭት” ተወግዶ ሰላም እንዲፈጠር ተደረገ፤ ለአውሮፓ አህጉር ምስረታ ጥንስስ የተጠነሰሰበት አለት ነው) የአውሮፓ ሕብረት እንዲፈጠር ያነሳሳ ወቅት እነደ ነበረ በመልዕክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በአውሮፓ አህጉር የሚኖሩ ሕዝቦች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ የአህጉሪቱ ህዝብ እርቅ እንዲፈጥር እና የአውሮፓን ውህደት ሂደት ያነሳሳ ወቅት እንደ ነበረ፣ ዛሬ እያጣጣምነው የምንገኘው ሰላም የእዚያ ጥንስስ ውጤት ነው ብለዋል። የሹማን መግለጫ አጠቃላይ ሐሳብ በአሁኑ ወቅት የሚገኙትን የአውሮፓ አህጉር መሪዎች የአውሮፓን አህጉር ሕብረት ጠብቀው ወደ ፊት የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያንቀቃቃ ወቅት እንደ ሆነ በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በትብብር እና በመግባባት መንፈስ ለመቋቋም እንዲችሉ የሚያበረታታቸው ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሳምንታዊ መልዕካታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ዕይታቸውን በአፍሪካ አህጉር ላይ በማደረግ እ.አ.አ። በግንቦት 10/1980 ዓ.ም የዛሬ አርባ ዓመት በፊት ማለት ነው ቅዱስ ዩሐንስ ጳውሎስ በእዚያች በአፍሪካ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በሰሃራ በረሃ ሰርጥ ውስጥ የሚገኙ የሳህል አገራት (ሳሄል ምዕራባዊ እና ሰሜን-መካከለኛው አፍሪካ ከፊል-ከፊል ክልል ሲሆን ከሴኔጋል እስከ ምስራቅ አፍሪካ  እስከ ሱዳን የሚዘልቅ ክልል ነው። በደረቅ የሳሃራ (በረሃ) ወደ ሰሜን እና ደቡብ እርጥበት አዘል ወደ የሆኑ አከባቢዎችን ያጠቃልላል። ሳሄል ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ከምሥራቅ እስከ ሰሜን ሴኔጋል ፣ ደቡባዊ ሞሪታኒያ ፣ ማሊ ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ደቡብ ኒጀር ፣ ሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ፣ በደቡብ-መካከለኛው ቻድ እና እስከ ሱዳን ድረስ የሚዘልቅ ክልል ነው) በወቅቱ በድርቅ ምክንያት ሕዝቡ እየተጋፈጠ የነበረውን ሁኔታ ድምጻቸውን ከፍ ድግርገው ለዓለም እንዲሰማ ማደረጋቸው እንደ ሚታወስ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።   በላቲን ቋንቋ “Laudato Si” በአማርኛው “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክት አነሳሽነት በእዚህ በሳህል ቀጠና ዛፎችን በመትከል ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ያመሰገኑ ሲሆን ግቡ አንድ ሚልዮን የሚሆን ዛፎችን በመትከል “አረንጓዴ የሆነ ታላቁ አፍሪካ” መመስረት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው ብዙዎች የእነዚህን ወጣቶች የአንድነት ተምሳሌ እንደ ሚከተሉ ተስፋቸው እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“ዛሬ በብዙ አገሮች የእናቶች ቀን ይከበራል። የሰማይ ንግሥት እና እናታችን ማርያም እናቶችን እንድትጠብቅ በአደራ በመስጠት ሁሉንም እናቶች በምስጋና እና በፍቅር ለማስታወስ እፈልጋለሁ” በማለት መልዕክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ሐሳቤ በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሌሉ እናቶችንም ይመለከታል፣ በሰማይ ቤት አብረውን እንደ ሆነ ሁኖ ይሰማኛል፣ አንድ ጊዜ ዝም ብለን እያንዳንዳችን እናቶቻችንን እናስታውሳቸው” ካሉ በኋላ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሆን ዘንድ ለሁላችሁም እመኛለሁ፣ “እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ” ካሉ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጠተው ቅዱስነታቸው የእለቱን መልዕክት አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
10 May 2020, 21:00