መለኮታዊ ምሕረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስል፣ መለኮታዊ ምሕረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስል፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት መለኮታዊ ምሕረትን ለምነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያለፈው ረቡዕ ሚያዚያ 07/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ከፖላንድ ለመጡ ምዕመናን ሰላምታቸውን ባቀረቡበት በኋላ፣ እሑድ ሚያዝያ 11/2012 ዓ. ም. የመለኮታዊ ምሕረት በዓል እንደሚከበር አስታውሰዋል። ከሃያ ዓመት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የፖላንድ አገር ተወላጅ የሆነች ፎስቲና ኮቫላስካ ቅድስናን ባወጁበት ዕለት፣ ሚያዝያ 11 ቀን የመለኮታዊ ምሕረት በዓል የሚከበርበት ዕለት እንዲሆን መወሰናቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ሁለት የብርሃን ጮራዎች፣

ሰዎች ወደ እኔ የምሕረት ምንጭ ካልቀረቡ በቀር ሰላምን ሊያገኙ አይችሉም፤ ለነፍሳት በሙሉ መጠጊያ እና መሸሸጊያ ይሆናቸዋል ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነገራት ፎስቲና በማስታውሻ ደብተሯ በ699ኛው ቁጥር ጽፋ ማስቀመጧ ተመልክቷል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2000 ዓ. ም. በተከበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ቀጥሎ በዋለው እሑድ የመለኮታዊ ምሕረት በዓለ የሚከበርበት እንዲሆን ከወሰኑ በኋላ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ሁለት የብርሃን ጮራዎች ሲፈልቁ ማየቷን እና አንደኛው የብርሃን ጮራ ደምን እና ሁለተኛው የብርሃን ጮራ ውሃን እንደሚያመለክት ኢየሱስ መናገሩን አስረድታለች ብለው ይህም ከኢየሱስ ልብ የሚፈሰው ታላቅ የምህረት ማዕበል እንደሆነ መግለጻችው ይታወሳል።

የቤተክርስቲያን እና የሰው ልጅ መሐሪ ወደ ሆነው ኢየሱስ እንጸልይ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 7/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ለተገኙት መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታቸውን ባቀረቡላቸው ጊዜ የምሕረት ምንጭ ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ጸሎታችንን በታማኝነት እናቅርብ ብለው በተለይም የኮሮና ቫይረስ ዓለምን በስጨነቅበት በዚህ ወቅት የኢየሱስን ምሕረት መለመን ያስፈልጋል ብለው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን ተስፋን እና እምነትን ያብዛልን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ሁለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመለኮታዊ ምሕረት አንድ ሆነዋል፣

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና የወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ወቅት መለኮታዊ ምሕረትን መለመናቸው ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በመጀመሪያዎች የሐዋርያዊ ሥልጣን ዓመታ ይህም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ኅዳር 30/1980 ዓ. ም. ስለ መለኮታዊ ምሕረት የሚናገር ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከታኅሳስ 8/2015 ዓ. ም. እስከ ኅዳር 20/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ ኢዮቤልዩ የምሕረት ዓመት ማወጃቸው ይታወሳል። ሁለቱም ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ማኅበራዊ ችግሮች በተስፋፉበት፣ ሰብዓዊ ክብር በሚጣስበት እና በስፋት የሚነሳውን የድሆች ጥያቄን በማስታወስ የመለኮታዊ ምሕረት ኃይል ለቤተክርስቲያን እና ለዓለም እንዲታወቅ አድርገዋል።

ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.ጎ.አ 1980 ዓ. ም. “የምሕረት ባለ ጸጋ” ቃለ ምዕዳን፣

ምሕረት ፍትህን ይበልጣል በማለት የገለጹት ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “እግዚአብሔር የምሕረት ባለ ጸጋ” በማለት ይፋ ባደረጉት ቃለ ምዕዳናቸው ስር “ፍትሕ በቃ ወይ?” በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ባቀረቡት ሃሳብ፣ ምሕረት በፍቅር ውስጥ የሚገኝ ፍትህ ከፍተኛ ደረጃ መሆኑን ገልጸው ቤተክርስቲያንም ይህን ምሕረት ለማወጅ የተጠራች መሆኗን አስረድተዋል።

የእህት ፎስቲና ቅድስና አዋጅ፣

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “የምሕረት ባለ ጸጋ” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ካደረጉ ከሃያ ዓመት በኋላ የእህት ፎስቲና ቅድስናን ማወጃቸው ይታወሳል። ማርያ ፎስቲና ኮቫልስካ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 5/1938 ዓ. ም. በተወለደችበት ከተማ ክራኮቪያ፣ በ33 ዓመት እድሜዋ ማረፏ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር መጋቢት 30/2000 ዓ. ም. የእህት ፎስቲናን ቅድስናን ባወጁበት ዕለት ከመዝ. 118:1 ላይ “ቸር ስለሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑት” የሚለውን ጥቅስ ማሰማታቸው ይታወሳል።

ከተሰበረው የኢየሱስ ልብ የሚፈልቅ የምሕረት ማዕበል፣

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ወንጌላዊው ዮሐ. 20: 22-23 ላይ እንደጻፈው፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ገብቶ በመካከላቸው ቆሞ “አብ እኔን እንደላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ። ይህን ካለ በኋላ እፍ አለባቸውና፣ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ እናንተ የሰውን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ይቅር አይባልላቸውም” ማለቱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስታውሰው፣ ይህን ከማስታወሳቸው አስቀድመው “ስላም ለእናንተ ይሁን!” ብሎ የእጁን እና የጎኑን የስቃይ ቁስል፣ ከሁሉም በላይ የልቡን መቁሰል ወይም ማዘን ለደቀ መዛሙርቱ መግለጹን ተናግረው ልቡም ምሕረት ማዕበል የሚወጣበት መሆኑን አስረድተዋል።

መለኮታዊ ምሕረት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ፣

ያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ መለኮታዊ ምሕረቱን ማስታወስ አይቻልም ያሉት ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የእግዚአብሔር ምሕረት መገለጥ መጠናቀቁን፣ የዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ፣ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገለጠው የምሕረት ስጦታ መሆኑን አስረድተዋል። የእግዚአብሔር የምሕረት መልዕክት በተዘረጋው እጁ በኩል በስቃይ ውስጥ ለሚገኝ የሰው ልጆች በሙሉ የሚደርስ መሆኑን አስረድተዋል።

ምሕረት የእግዚአብሔር ትልቁ መልዕክት ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቶሊካስዊ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው ከመመረጣቸው ከአራት ቀናት ቀደም ብሎ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር መጋቢት 17/2013 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኝ የቅድስት ሐና ቁምስና ውስጥ ምዕመናን የተካፈሉበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ ቀጥለውም በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ለካርዲናሎች የምስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸው ይታወሳል። ከዮሐንስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል፣ ስታመነዝር የተያዘች እና የሞት ፍርድ የተፈረደባትን ሴት ኢየሱስ እንዳዳናት የሚናገር መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይህን መሠረት በማድረግ እንደተናገሩት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከተናገራቸው መልዕቶች ትልቁ ምሕረት መሆኑን አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በማር. 2: 17 ላይ “እኔ የመጣሁት ኃጢ አተኞችን ወደ ንስሐ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሐ ለመጥራት አይደለም” ማለቱን አስታውሰው እግዚአብሔር ምሕረቱን መስጠት እንደማይሰለቸው፣ ይልቅስ ምሕረትን መጠየቅ የሚሰለቸን እኛ ነን በማለት አስረድተዋል።

እግዚአብሔር ልቡን ክፍት ያደረገበት የምሕረት ኢዮቤልዩ፣

የፍቅር አባት እግዚአብሔር ልቡ በምሕረት የተሞላ በመሆኑ ሁላችንን ዘወትር ይቅር ይለናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እኛም ከእርሱ በመማር የበደሉንን ይቅር ማለት ይገባል ብለዋል። ሰው በመሆን ወደ ዓለም የመጣውን የእግዚአብሔርን ምሕረት በእጆችዋ ወደ ታቀፈጭ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታችንን እናቅርብ ብለዋል። “ምህረትን መፈለግ” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢዮቤልዩ አስተምህሮአቸው ስለ እግዚአብሔር ምሕረት በሙላት የሚተነትን መሆኑ ታውቋል። በዚህ አስተምሮአቸው በኩል እግዚአብሔር የፍቅር ልቡን ለእኛ ለመክፈት ምንም ጊዜም የማይሰለቸው መሆኑን ገልጸው ሕይወቱንም ከእኛ ጋር ለመጋራት የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን የኢዮቤልዩ ስጦታ ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ርህራሄ እና ሀዘን” ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በቅዱስ የምሕረት ዓመት መጨረሻ ላይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን እንዲከበር በማለት መወሰናቸው ይታወሳል። “ርህራሄ እና ሐዘን” የሚለው መልዕክታቸው ቅድሱ አጎስጢኖስ የናገራቸው የነበረው ሁለት ቃላት ሲሆኑ፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአመንዝራይቱ ሴት ጋር ያደረገውን ንግግር የሚገልጽ ነው። ይህን ታሪክ በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ከኃጥአተኛ ሰው ጋር ሲገናኝ የሚያሳየውን ሁለት ነገሮች መኖራቸውን፣ እነርሱም ምስኪኑ ኃጢአተኛ እና አዛኙ እግዚአብሔር መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል።

የመጀመሪያዎቹ የእግዚአብሔር ምሕረት መገለጫዎች ነን፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆርጣጠር በታኅሳስ ወር 2020 ዓ. ም. ከፈረንሳይ የመጡ የመለኮታዊ ምሕረት ማሕበር ተወካዮች ጋር በተገናኙበት ጊዜ እንድተናገሩት እውነተኛ የምሕረት ሐዋርያት መሆን የምንችለው እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በኩል የምሕረት መገለጫዎች መሆናችንን ስንረዳ እና በዚህ ጸንተን ስንቆይ ነው ብለው፣ የሚከተለውን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መልዕክት ጠቅሰዋል፥

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “እውነተኛ ምሕረት የሚገለጠው እርስ በእርስ ምሕረት ስንደራረግ ነው”፣

“ምሕረት በተግባር እንዲገለጥ ከተፈለገ ሃሳባችንን እና ሥራችንን በዘላቂነት በመመርመር ማስተካከል ይኖርብናል፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በፍቅር የተሞላ ምሕረት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ የእኛ ምሕረት በሌላኛው ወገን ተቀባይነትን እንደሚያገኝ በጥልቀት ልንገነዘብ እንችላለን። ይህ የእርስ በእርስ ምሕረት መለዋወጥ የሚጎድል ከሆነ ሥራችን እውነተኛ ምሕረት የሚደረግበት ሊሆን አይችልም።”         

19 April 2020, 01:31